በኦሮሚያ ተቃውሞ ቢያንስ 75 ሰዎች ተገድለዋል
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 9 2008ማስታወቂያ
ከአዲስ አበባ 80 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው ጊንጪ ከተማ ተጀምሮ ወደ መላ ኦሮሚያ ለተስፋፋው ተቃውሞ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው ምላሽ በርካታ ሰዎች መገደላቸውን የተናገሩት የድርጅቱ የአፍሪቃ ክፍል ምክትል ኃላፊ ሌስሊ ሌፍኮው የከፋ ደም መፋሰስ ሊያስከትል እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። የኢትዮጵያ መንግስት በከተሞችና ከፍተኛ የትምርት ተቋማት የተዛመተው እና የአዲስ አበባ ከተማን ከአጎራባች አካባቢዎች ጋር ለማስተሳሰር የታቀደው ማስተር ፕላን ላይ በተነሳው ተቃውሞ የሞቱት ሰዎች ቁጥር አምስት ብቻ መሆናቸውን አስታውቋል።
የተቃዋሚ ፖለቲካ መሪ የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ ከመሬት መነቀልን ጨምሮ ለአመታት የተከማቸ ቅሬታ፤ የዴሞክራሲ እጦት፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እና አስከፊ ድህነት ለተቃውሞው ተጨማሪ ገፊ ምክንያቶች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌስሊ ሌፍኮው የኢትዮጵያ መንግስት ሰላማዊ ተቃዋሚዎችን «ሽብርተኛ» ሲል መፈረጁ እና ተቃውሞው በተስፋፋባቸው አካባቢዎች የጦር ኃይል ማሰማራቱ ሁኔታውን ሊያባብስ የሚችል አደገኛ ውሳኔ ሲሉ ወቅሰዋል።
እሸቴ በቀለ
ማንተጋፍቶት ስለሺ