1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በኢትዮጵያ ጉዳይ የአምነስቲ አስተያየት

ዓርብ፣ ሰኔ 16 2009

በኢትዮጵያ  የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት እንደሚደርስ የታወቀ ቢሆንም በጉዳዩ ላይ የኢትዮጵያን መንግሥት ለመተቸት ዝግጁ የሆኑ የአፍሪቃ መሪዎች እንደሌሉ አምነስቲ ኢንተርናሽናል አስታወቀ። የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ሃላፊ ሳሊል ሼቲ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንዳሉት መሪዎቹ ጉዳዩን ለማንሳት አይፈልጉም።

https://p.dw.com/p/2fCB8
Salil Shetty (Secretary General, Amnesty International, India)
ምስል DW/K. Danetzki

Amnesty International on Ethiopia - MP3-Stereo

ቦበኑ የዓለም የመገናኛ ብዙሀን መድረክ ላይ የተሳተፉት የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዋና ፀሐፊ ሳሊል ሼቲ ለዶቼቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ ፣ በአሁኑ ወቅት በበርካታ ሀገራት የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት የተባባሰ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል። ሼቲ እንዳሉት በጎርጎሮሳው 2016፣ ከሀያ በሚበልጡ የአፍሪቃ ሀገራት ህዝባዊ ተቃውሞዎች ተካሂደዋል። በነዚህ አመጾችም በሰላማዊ መንገድ መብታቸውን የጠየቁ ህዝቦች ተገድለዋል። ህዝባዊ ተቃውሞ ከተካሄደባቸው ሀገራት አንዷ በሆነችው በኢትዮጵያም በርካቶች ተገድለዋል፤ታስረዋል። ሐገሪቱም ላለፉት 9 ወራት በአስቸኳይጊዜ አዋጅ ነው የምትተዳደረው። ሼቲ እንዳሉት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት አሁንም ትችቶች እንዲቀርቡባቸው አይፈልጉም።  ኢትዮጵያን የሚመለከት ባይሆንም በቅርቡ ድርጅታቸው በአዲስ አበባ ሊያካሂድ የነበረው ስብሰባ እንደታገደበት ሼቲ ገልጸዋል።
«ኢትዮጵያ ጥሩ አይደለችም።ባለፈው ወር አዲስ አበባ የአፍሪቃ ህብረት የሰላም እና የፀጥታ ተቋምን የሚመለከት ዘገባ ይፋ ለማድረግ ተዘግጅተን ተከልክለናል፤ በአዲስ አበባ ሂልተን ሆቴል ከመካሄድ የታገደው ስብሰባ ስለ ኢትዮጵያም አልነበረም፤ስለ አፍሪቃ ህብረት እንጂ።ሆኖም አገዱት። በየጊዜው የሚያራዝሙት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላቸው። ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩን አነጋግሬያቸው ነበር። ስለ ጉዳዩ አያውቁም ነበር። ሆኖም በሁሉም ደረጃ የሚገኙ የመንግሥት ባለሥልጣናት የትኛውንም ዓይነት ትችት አዘል አስተያየት መስማት አይፈልጉም። ያም ሆኖ ከባድ ችግሮች ቢኖሩም ፣ የድረ-ገጽ አምደኞች(ብሎገሮች) እና ጋዜጠኞች ድምጻቸውን ያሰማሉ ከባድ ነው ፤ ሰዉ ግን ይታገላል።»
በኢትዮጵያው ሁኔታዎች እየከበዱ መምጣታቸውን ለገለጹት ሼቲ  የአፍሪቃ ህብረት መቀመጫ በሆነችው በኢትዮጵያ ይህ ሲፈፀም በጉዳዩ ላይ ከአፍሪቃ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ጋር ተወያይታችኋል ወይ የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር። 
« በኢትዮጵያ የሚደረገውን ሁሉም ያውቃል። የተቃዋሚ ፓርቲዎች መሪዎች ወከባ ይፈጸምባቸዋል በኢትዮጵያ ፓርላማ አንድ ተቃዋሚ እንኳን የሌለበት መንግሥት እንዴት ሊኖር ይችላል? ይህ ተዓማኒ መንግሥት ነውን? ታውቃለህ ሰዉ አያውቅም ማለት አይደለም። በኢትዮጵያ ምን እንደሚሆን ሁሉም ያውቃል ። ግን ሊቃወሟቸው አይፈልጉም። ሙሴቬኒ  ካጋሜ እና ሙጋቤ ዙማም ቢሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያምን ለመተችት ዝግጁ ናቸው ወይ? አይመስለኝም። »
በኢትዮጵያ ሲካሄድ ስለቆየው ህዝባዊ አመፅ አስተያየታቸውን የሰጡት የአምነስቲ ሃላፊ ሳሊል ሼቲ በተቃውሞው ወቅት ሕዝቡ ያነሳቸው የመብት ጥያቄዎች ተገቢ እንደነበሩ ተናግረዋል። በሀገሪቱ ህገ መንግሥት ላይ የተቀመጠው መብት በተግባር መተርጎም አለመቻሉ መሆኑን ዋናው ችግር እንደሆነ አስታውቀዋል።
« በኦሮሞ ተቃውሞ ጉዳይ ላይ በጣም ጠቃሚ ዘገባ አዘጋጅተናል። ብዙ መግለጫዎችንም ሰጥተናል። ይህ አዲስ አይደለም ስናደርገው የቆየነው ጉዳይ ነው። የኦሮሞውን ተቃውሞ እንዲሁም የሌሎች ብሄሮችን ጥያቄ ስንመለከት ከተነሱት ውስጥ ትክክለኛ ጉዳዮች ነበሩ። ኢትዮጵያ ሥልጣን መጋራት የሚያስችል በጣም ዘመናይ እና የወደፊቱን ያገናዘበ  ህገ መንግሥት አላት። በተግባር ግን የማናቸውንም ታቃዋሚ ድምጽ እንዲሰማ አይፈቅዱም። በልማት ረገድ ጥሩ የሚባል የሚስብ ሥራ ተሰርቷል እንዳለመታደል ሆኖ ግን የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች ጉዳይ በጣም ኋላ ቀር ነው።»

Äthiopien Protesten der Oromo in Bishoftu
ምስል REUTERS/File Photo/T. Negeri

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ