በአውሮፕላን አደጋ ለሞቱ የሐዘን ሥነ-ሥርዓት ተካሔደ
እሑድ፣ መጋቢት 8 2011ከሳምንት በፊት ከቢሾፍቱ አቅራቢያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አውሮፕላን በመከስከሱ ሕይወታቸውን ያጡ መንገደኞች የሐዘን ሥነ-ሥርዓት አዲስ አበባ በሚገኘው ቅድስት ስላሴ ካቴድራል ተካሔደ። በሥነ-ሥርዓቱ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ የለበሱ 17 ባዶ የሬሳ ሳጥኖች በመታሰቢያነት ቀርበዋል። በመርሐ ግብሩ የሟች ቤተሰቦች በከፍተኛ ሐዘን ተውጠው ታይተዋል። የሐዘን ሥነ-ሥርዓቱ የተካሔደው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሟች ቤተሰቦች ለ157ቱ መንገደኞች ቤተሰቦች አፈር መስጠት ከጀመረ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። አየር መንገዱ አውሮፕላኑ ከወደቀበት ቦታ በከረጢት የታሸገ አንድ ኪሎ አፈር ለመስጠት የተገደደው የሟቾቹን ማንነት የመለየቱ ሥራ ረዥም ጊዜ ስለሚወስድ ነው።
በቅድስት ስላሴ ካቴድራል ቤተ ክርስቲያን በተከናወነው የሐዘን ሥነ-ሥርዓት የሟቾች ቤተሰቦች፣ የስራ ባልደረቦች፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው በብዛት ተገኝተው እርማቸውን አውጥተዋል። የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች እና አመራሮች በአደጋው ሕይወታቸውን ያጡ ባልደረቦቻቸውን ለማሰብ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ተመሳሳይ የሐዘን ሥነ-ሥርዓት አካሒደዋል።
የመንገደኞች ቤተሰቦች ካናዳን ከመሳሰሉ አገሮች ወደ ኢትዮጵያ በመጓዝ ላይ ናቸው። የፈረንሳይ የበረራ ደኅንነት ምርመራ ባለሥልጣን በትናንትናው ዕለት ከተከሰከሰው አውሮፕላን የመረጃ ማጠራቀሚያ ሳጥን አስፈላጊ ሰነዶች በተሳካ መንገድ ማውጣታቸውን አስታውቀዋል።
ባለሥልጣኑ መረጃው ለኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሥልጣናት ማስረከቡን አስታውቋል። በተለምዶ ጥቁር ሳጥን (ብላክ ቦክስ) ተብሎ በሚጠራው የመረጃ ማጠራቀሚያ ሳጥን የሚገኙ የድምፅ ሰነዶች በፈረንሳይ የበረራ ደኅንነት ምርመራ ባለሥልጣን አለመደመጣቸውም ተገልጿል።
እሸቴ በቀለ