84 የነብርና አንድ የአዞ ቆዳ ተቃጠለ
ሰኞ፣ ነሐሴ 18 2012
በአማራ ክልል ህገወጥ የዱር እንስሳት አደን እየተስፋፋ መምጣቱን የአካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል፣ 14 ሚሊዮን ብር የሚገመት ህገወጥ የነብር ቆዳ ሰሞኑን መቃጠሉን የአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን አስታውቋል፡፡ በአማራ ክልል አካባቢ፣ ደንና ዱር እንስሳት ጥበቃና ልማት ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ጋሻው እሸቱ ለዶይቼ ቬለ አንዳሉት ህገወጥ የዱር እንስሳት አደን አሁን አሁን እየሰፋ መጥቷል፡፡ ሰሞኑን በተለያዩ ጊዜዎች በህገወጥ መንገድ ከሀገር ሊወጡ ሲሉ የተሰበሰቡ 14 ሚሊዮን ብር ማውጣት የሚችል 84 የነብርና አንድ የአዞ ቆዳ መቃጠላቸውን አቶ ጋሻው ተናግረዋል፡፡ ለምን ተቃጠሉ ለክልሉ ልማት መዋል አይችሉም ወይ ሲል ከዶይቼ ቬለ ተጠይቀው ዓለም አቀፍ ህጉ እንደማይፈቅድ አቶ ጋሻው ገልፀዋል፡፡ አደን ህገወጥ ቢሆንም አንዳንዴ የሚፈቀድበት ሁኔታ መኖሩን ጠቁመው ይህም የሚሆነው እንስሳቱ እድሜያቸው ሲያረጅ መሆኑን አስታውቀው ለውጪ አዳኞች የሚፈቀድበት ሁኔታ ይኖራል ብለዋል፡፡የምዕራብ ጎንደር ነዋሪው ሙሉጌታ ተመስገን ለዶይቼ ቬሌ በስልክ እንደተናገሩት ከአልጣሽ ብሔራዊ ፓርክ በርካታ የዱር እንስሳት በህገወጥ መንገድ ይታደናሉ፤አደን በስፋት በአካባቢው ይዘወተራል ብለዋል፡፡በሰሜን ብሔራዊ ፓርክም ተመሳሳይ የህገወጥ አደን መኖሩን የአካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል፡፡ በተለይ የነብር ቆዳ በስፋት በህገወጥ መንገድ እየተሸጠ በመሆኑ የእንስሳው ዝርያ እንዳይጠፋ ስጋታቸውን ገልፀዋል፡፡ችገሩን ለመከላከል ጥበቃ ማድረግ ብቻውን መፍትሔ እንዳልሆነ ያመለከቱት አቶ ጋሻው ህብረተሰቡ የዱር እንስሳትን ጠቀሜታ እንዲያውቅና እንዲንከባከብ የማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ እየተከናወነ እንደሆነም አስረድተዋል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ