1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በቀጣይ አምስት ዓመት የደን መራቆትን መግታት

ማክሰኞ፣ መስከረም 18 2008

በጎርጎሪዮሳዊዉ 2020ዓ,ም ማለትም ከአምስት ዓመታት በኋላ የደን መራቆትን መግታት ዘላቂነት ያለዉ የተመድ የልማት ግብ እቅድ ነዉ።

https://p.dw.com/p/1Gfdd
Sambia Bwumba Wald Regenwald Abholzung
ምስል picture-alliance/Balance/Photoshot

ከአምዓቱ የልማት ግቦች በእንግሊዝኛዉ ምህጻር MDGs ወደዘላቂ የልማት ግቦች ማለትም በእንግሊዝኛዉ ምህፃር SDGs የተሻገረዉ የተመድ የልማት እቅድ ያካተታቸዉ 17 ነጥቦችን ባጠቃላይ እስከመጪዉ 2030 ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ወይም የዛሬ 15 ዓመት ድረስ ለማሳካት ነዉ ያቀደዉ።

እንግዲህ የተመድ አባል ሃገራቱን በማስተባበር በዚህ እቅዱ ድህነትን ፈፅሞ ለማጥፋት፤ እንዲሁም ምድራችንን ከተጋረጠባት አደጋ ለመከላከል እና ሁሉም እንዲበለፅግ አልሟል። በእቅዱ ዉስጥ በ15ኛ ተራ ቁጥር እንደተጠቀሰዉ አሉ ከሚባሉት ዘጠኙ ፕላኔቶች ለሰዉል ልጅ መኖሪያ ተስማሚነቷ የተረጋገጠዉን የመሬትን ስነምህዳሮች ለመጠበቅ፣ ያላትን ሃብት በተገቢዉ መንገድ እና ለነገም እያሰቡ በጥንቃቄ መጠቀም አይነተኛ መፍትሄ መሆኑን በማስገንዘብ የደን መራቆትን ለመግታት ታቅዷል። ምንም እንኳን እነዚህ ዝርዝር ዘላቂ የልማት ግቦች ከጎርጎሪዮሳዊዉ 2030ዓ,ም አስቀድሞ ሊሳኩ ይችላል ተብሎ ባይገመትም፤ በቀጣይ አምስት ዓመታት ዉስጥ የደንን መራቆት ለመግታት መታለሙ በራሱ ለአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች እንደትልቅ ድል ነዉ የተቆጠረዉ። የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎቹ ግን የተባለዉ እጅግም ያስደሰታቸዉ አይመስልም። እንደዉም ያተረጓጎም ስህተት እንዳለ በማመላከት የዛፎች በየሜዳዉ መገጥገጥ ብቻዉን የተፈጥሮ አካባቢን ከጉዳት እንደማያድን በመግለፅ በይፋ ትችት ሰንዝረዋል። አንድ ሶስተኛዉ የመሬት አካል በደን የተሸፈነ ነዉ ስለሚባል በተመድ ዘላቂነት ያለዉ የልማት እቅድ ትኩረት ማግኘቱ ብዙም ላያስደንቅ ይችላል። የደን ሀብትን መንከባከቡ ዘላቂነት ላለዉ ልማት ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳለዉ ግን ብዙዎች ያምናሉ። ከእነዚህ አንዷ የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ባልደረባ ኤፋ ሙለር እንዲህ ይላሉ።

Symbolbild Abholzung Holzhandel CAR Zentralafrikanische Republik
ምስል picture-alliance/dpa/G. Pourtier

« ባላቸዉ ዘርፈ ብዙ ሚና ዘላቂነት ላለዉ የልማት ግብ በርከት ያለ አስተዋፅኦ ያበረክታሉ። ለአየር ንብረቱ እና ለአፈሩ፤ እንዲሁም የዉኃ ፍሰት እንዲቀጥል ጠቃሚዎች ናቸዉ። በዚያም ላይ በገቢ ምንጭነት እና በመሳሰሉት ከፍተኛ ድርሻ አላቸዉ።»

የዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት FAO እንደሚለዉ ደኖችን ለመከላከል እስካሁን ትርጉም ያለዉ ርምጃ ተወስዷል። በቅርቡድርጅቱ ይፋ ባደረገዉ ዘገባ መሠረትም ከጎርጎሪሳዊዉ 2009 ወዲህ የደኖች መራቆት ፍጥነት በከፊል ቀንሷል። 110 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይም አዲስ በተተከሉ ዛፎች ተሸፍኖ ሰዉ ሰራሽ ደን መፈጠሩን FAO አመልክቷል። ይህ ማለትም ከዓለም የደን ሽፋን ሰባት በመቶዉን ይይዛል።

Iran KW23 Abholzung
ምስል Tasnim

እንዲያም ሆኖ ይህ እንቅስቃሴ ለአካባቢ ተፈጥሮ መጠበቅ ለሚሟገቱ ወገኖች የሚያረካ ርምጃ አልሆነም። እንደዉም የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አይደልም የሚል ትችት ነዉ ያስከተለዉ። ሰማንያ የሚሆኑ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ያካተተዉ የዓለም ዓቀፉ የደን ጥምረት አባል ኢሲስ አልቫሬዝ FAO ያቀረበዉ አይነቱ ዘገባ የተዛባ መልዕክት ያስተላልፋል ባይናቸዉ። እርግጥ ነዉ በወረቀት ላይ ሲታይ ጥሩ ሊመስል ይችላል ሲሉም ይሞግታሉ።

«ለዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ያቀረቡት ዘገባን መሠረት አድርጎ ሲታሰብ ምናልባትም ያንን ደን ብለዉ ቆጥረዉታል። ነገር ግን ከስነተፈጥሮ አኳያ ጉዳዩን በዝርዝር ለተመለከተዉ ይህ በጣም አስቸጋሪ ጉዳይ ነዉ። አንድ ዓይነት የዛፍ ዘር መትከሉ በራሱ በአካባቢዉ ለሚኖረዉ ኅብረተሰብም ሆነ የደንን ሀብት ለመጠበቅ በራሱ ትልቅ ጉዳት እና አስቸጋሪ ነገር ነዉ።»

የተጋለጡ ቦታዎችን በደን ለማልበስ በሚደረገዉ ጥረት የሚተከሉ ተመሳሳይ የዛፍ አይነቶች የአፈሩን ለምነት የመቀነስ እና በተባዮችም የመጠቃት አደጋ ያስከትላል። ይህ እንዳለ ሆኖ ደግሞ የሚገኘዉ የብዝሃ ህይወት ስብጥር እጅግ ዉሱን እንዲሆን ያደርጋል። ይህን ከግምት በማስገባት አልቫሬዝ እንደሚሉት በዚህ መልኩ የሚገኘዉ ደን ስብጥሩ እንደተጠበቀ እና እንደተፈጥሮ ደን መታየት የለበትም።

Malaysia Regenwald
ምስል AP

«ነገር ግን ለዓለም የምግብ እና የእርሻ ድርጅት ይህ ምንም ለዉጥ የሚያመጣ አይመስልም። እናም የደን መራቆትን በግማሽ ቀነስነዉ ሊል ይችላል። ይህ ግን እዉነት አይደለም።»

በአንፃሩ ዘላቂ የልማት ግቦቹ ዉስጥ የደን መራቆት እንደዋነኛ ነጥብ ጎልቶ መዉጣቱ አንድ ነገር ነዉ በሚል ያደነቁት ወገኖች በበኩላቸዉ የልማት ግቡን ተግባራዊ ለማድረግ ግን ግልፅ ብያኔዎች እንደሚያስፈልጉ ነዉ የሚያሳስቡት። ደን የሚለዉ ፅንሰ ሃሳብ እንዲቀየርም ሆነ አንድ ዓይነት የዛፍ ዘርን መትከልን የማይደግፉ በርካታ ድርጅቶች ለዚህ ለዉጥ ትኩረት እንዲሰጥ የተቀናጀ ዘመቻ ጀምረዋል። በጀርመን የልማት ተቋም ተመራማሪ የሆኑት ዮናስ ሃይን እንዲህ ባሉ ጉዳዮች ላይ ክፍተት መኖር እንደሌለበት ያሳስባሉ።

«ምን ዓይነት ቀዳዳ መፈጠር አይኖርበትም። በጀርመን ዝቅተኛ ተራሮች ላይ ተመሳሳይ ዝርያ ያላቸዉ ዛፎችን በየደረጃዉ ብንተክል ይህን ዘላቂ የደን አስተዳደር ማለት ይቻላል?»

ሲሉም ይጠይቃሉ። ከዚህም ሌላ ሃይን ከ17ቱ የልማት ግቦ ጋር ተያያዥ ስጋት ያነሳሉ። እንደእሳቸዉ ጥቆማም የተለያዩ ኅብረተሰቦች ስብስብ በልማት እቅዱ ላይ የተጠቀሰዉ ከሕገ ወጥ አደን ጋር በተገናኘ ብቻ መሆኑ አሳሳቢ ነዉ። በእሳቸዉ እምነትም መልካም የሆነ የደን አያያዝና አስተዳደር እንዲኖር ከተፈለገ በየአካባቢዉ የሚገኘዉ ማኅበረሰብ ቁuleፍ ሚና ይኖረዋል። ይህ ሃሳብም በዘላቂ የልማት ግቦቹ ዉስጥ ጉልህ ስፍራ ሊሰጠዉ ይገባል።

«የተጠበቀ የደን አካባቢን ለማስፋት ታስቦ የአካባቢዉ ማኅበረሰብ በዚህ እንዲሳተፍ ካልተደረገ፤ ለመጠበቅ የታቀደዉን አካባቢ በእርግጥ እንዲጠበቅ የማድረጉ ሥራ ተግባራዊ ሊሆን አይችልም።»

UNESCO Weltkulturerbe Sundarbans
ምስል DW/M. Mamun

ለመሆኑ በቀጣይ አምስት ዓመት ዉስጥ ደኖችን የመመንጠር ርምጃን መግታት ይቻላል የሚለዉ እቅድ ከቀቢጸ ተስፋ አይዘልም ሲባል ምን ማለት ይሆን? እርግጥ ነዉ በአራት ዓመት ከመንፈቅ ደን ፈፅሞ እንዳይመነጠር ማድረግ ከወዲሁ ሲታሰብ የሚቻል አይመስልም። እንደጀርመናዊዉ ተመራማሪ ሃይን ግምት ከሆነ ራሱን ደኑን የገቢ ምንጭ ማድረጉ መፍትሄ ሊሆን ይችላል። ደኖችን በየአካባቢዉ በመፍጠር የየአካባቢዉ ኗሪ ያን በማድረጉ ገቢ የሚያገኝ ከሆነ ብቻ ነዉ እቅዱ እዉን ሊሆን የሚችለዉ ሲሉም ይሞግታሉ።

«ለምሳሌ ደኑ የማገዶ እንጨት ሊያስገኝ፤ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥም የፍራፍሬ ዛፎች ሊኖሩት ይችላል፤ በተጨማሪም ለገበያ የሚሆን የቡና ተክል እንዲሁም ካካኦ ሊኖሩት ይችላሉ።»

ምን እንኳን በአጭር ጊዜ ዉስጥ የደንን መራቆት ፈፅሞ የማስቆሙ እቅድ ሙሉ ለሙሉ ዉጤታማ ይሆናል ብለዉ ባያምኑንም ሃይን ሆኑ አልቫሬዝ ጉዳዩ በሃሳብ ደረጃ በወረቀት ሰፍሮ ማየታቸዉ ብቻ አስደስቷቸዋል። እቅዱ በራሱ ሕዝብን ለማንቀሳቀስና በዚህ ረገድ ለዉጥ እንዲያመጡ መንግሥታት ላይም ግፊት ለማድረግም ጠቃሚ መሆኑን ይናገራሉ። ምክንያቱም ምንም ዓይነት አስገዳጅ ዉል በሌለበት ዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የሕዝብ ግፊት ዋነኛ መሣሪያ መሆኑን የአካባቢ ተፈጥሮ ተቆርቋሪዎች ያምኑበታል።

ሩዝ ክራዉዘ/ ሸዋዬ ለገሠ

አርያም ተክሌ