1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማልያ የቀጠለው ውጊያ

ማክሰኞ፣ ነሐሴ 18 2002

የአክራሪው የአል ሸባብ ሚሊሺያዎች በሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ በአንድ ሆቴል ውስጥ በጣሉት ጥቃት ከሰላሳ የሚበልጥ ሰው ተገደለ።

https://p.dw.com/p/Ouz0
የአል ሸባብ ጥቃት ሰለባምስል AP

ስድስት የምክር ቤት እንደራሴዎችም ከተገደሉት መካከል ይገኙባቸዋል። በሞቃዲሾ ባለፉት ሀያ አራት ሰዓታት በሽግግሩ መንግስት ወታደሮችና በአል ሸባብ መካከል በተካሄደው ውጊያ ቢያንስ አርባ ሰዎች ተገድለው ከአንድ መቶ ሰላሳ የሚበልጡ ቆስለዋል።
በሶማልያ የአክራሪው የአል ሸባብ ሚሊሺያዎች በሶማልያ መዲና ሞቃዲሾ በሚገኘው የሙና ሆቴል ተኩስ ከፍተው ቢያንስ ሰላሳ ሁለት ሰዎች መግደላቸው ተገለጸ። ከተገደሉት መካከል ስድስቱ የምክር ቤት እንደራሴዎች ሲሆኑ፡ አምስት የመንግስት ሰራተኞችም እንደሚገኙባቸው መሳይ መኮንን ያነጋገረው በሞቃዲሾ የሚኖረው ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሀጂ አብዲ ኑር አስታውቋል።
« ዛሬ ጥዋት ጥቃቱ በተፈጸመበት ሆቴል ስድስት የምክር ቤት እንደራሴዎች ተገድለዋል። አሁን ለጊዜው ሁኔታው ተረጋግቶዋል። የሶማልያ ጸጥታ ኃይላት የሆቴሉን አካባቢ አጥረው እየጠበቁ ነው። እና ሰዎች ወደሆቴሉ እንይጠጉ እየከለከሉ ነው። »
የሶማልያ ጸጥታ ኃይላት መለያ ለብሰው በብዛት የሀገሪቱ መንግስት ባለስልጣናት ይገኙበት በነበረው ሆቴል ጥቃት የጣሉት ሁለቱ የአልሸባብ ሚሊሺያዎች ከእስራት ለማምለጥ ሲሉ ራሳቸውን በቦምብ ባነጎዱበት ጊዜ ነበር ብዙዎቹ ሲቪሎች የተገደሉት። አል ሸባብ ኃላፊነት የወሰደበት ጥቃት የተጣለው በሶማልያ የተሰማራው የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ የህብረቱ የሶማልያ ጉዳይ ተመልካች ልዩ ተወካይ ዋፉላ ዋሙኒዪኒዪ በናይሮቢ ኬንያ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አክራሪዎቹን ሚሊሺያዎች ጓዱ ከሞቃዲሾ ገፍቶ ለማስወጣት ዕቅድ እንዳለው ከተናገሩ ከአንድ ቀን በኋላ ነው። አል ሸባብ በሚላቸው የሶማልያን የሽግግር መንግስት በሚረዱት የጓዱ የዩጋንዳ እና የቡሩንዲ ወታደሮች አንጻር በትናንቱ ዕለት ሙሉ ጦርነት ካወጀ በኋላ፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ ሁኔታዎች ቢረጋጉም፡ በተለያዩ የከተማይቱ ሰፈሮች በተቀናቃኞቹ ወገኖች ውጊያ መካሄዱን ጋዜጠኛ ሙስጠፋ ሀጂ አብዲ ኑር ገልጾዋል።
« ውጊያው ገና አላቆመም። አሁንም ባንዳንድ የከተማይቱ ሰፈሮች፡ በተለይም በኤዲያ ና በበርሙዳ ሰፈሮች አልፎ አልፎ በመድፍና ሞርታር፡ እንዲሁም በመትረየስ ውጊያ ይካሄዳል። እና ውጊያው ጨርሶ አላቆመም። ግን፡ ዛሬ ጥዋት እንደነበረው አይደለም። »

Somalia Shebab Miliz Angriff auf Hotel in Mogadischu
የሞቃዲሾው ሙና ሆቴልምስል AP

በመዲናይቱ ሞቃዲሾ የሚገኝ የአንድ ሀኪም ቤት የጤና ባለሙያዎች እንዳስታወቁት፡ የአፍሪቃ ህብረት ሰላም አስከባሪ ጓድ በሚረዳው የሶማልያ የሽግግር መንግስት ወታደሮች እና በአል ሸባብ መካከል ባለፉት ሀያ አራት ሰዓታት በተካሄደ ውጊያ እስካሁን ከአርባ የሚበልጥ ሰው ሲገደል፡ ከአንድ መቶ ሰላሳ የሚበልጥ ቆስሎዋል።

አርያም ተክሌ
ሂሩት መለሰ