1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሶማልያ የስልጣን ሽኩቻ ያስከተለዉ ሥጋት

ረቡዕ፣ ጥቅምት 26 2007

በሶማልያ ፕሬዝደንት ሃሰን ሼኪ ሞሃመድ እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ አብዱዊሊ ሺካህ አህመድ መካከል የተፈጠረዉ የስልጣን ሽኩቻ ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በጦርነት ስትታመስ የቆየችዉን ሀገር ዳግም እንዳያንኮታኩታት ማስጋቱን የአዉሮጳ ሕብረት እና የተመድ አሳሰቡ።

https://p.dw.com/p/1Dggu
Somalia Straßenszene mit Frau in Mogadischu
ምስል picture-alliance/dpa/Tobin Jones

በሶማልያ የአዉሮጳዉ ሕብረት እና የተባበሩት መንግሥታት መልክተኞች ሽኩቻ ላይ የሚገኙት የሶማልያ ባለስልጣናት የፖለቲካ መሪነት ኃላፊነታቸዉን በአግባቡ እንዲወጡ ጠይቀዋል።

በሶማልያዉ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኪ ሞሃመድ እና በምክትል ሚኒስትሩ አብዱዊሊ ሺካህ አህመድ መካከል የተፈጠረዉ የስልጣን ሽኩቻ በጥልቅ ያሳሰባቸዉ መሆኑን የገለፁት በሶማልያ የአዉሮጳዉ ሕብረት መልክተኛ አሌክሳንደር ሮንዶስ፤ የሁለቱ ባለስልጣናት ይፋዊ ልዩነት የመንግሥት ተቋማት ሥራቸዉን በቅጡ እንዳያከናዉኑ እንቅፋት መሆኑን አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ በመንግስት የተጀመረዉን የሰላም ግንባታን የሚያደናቅፍ ብለዉታል። ሮንዶስ በተጨማሪ ሶማልያ ሰላም ትፈልጋለች፤ ለዚህ ደግሞ ኃላፊነት የሚሸከም የፖለቲካ መሪም ያስፈልጋታል ብለዋል። በአፍሪቃዉ ቀንድ ሃገራት የአዉሮጳ ሕብረት ልዩ መልክተኛ አሌክሳንደር ሮንዶስ የባለስልጣናቱ ሽኩቻ ምክንያት ምን እንደሆነ ባላዉቅም፤ ሊደረግ የታቀደዉን ምርጫ እዲፈፀም በብልሃትና በትጋት መሥራት አለባቸዉ
«ያለመግባባታቸዉ ዋና ምክንያት ምን እንደሆን ማወቅ ቢከብደኝም በሶማልያ በአሁኑ ወቅት እየተቃረበ ለመጣዉ ምርጫ ሰዎች ዝግጅት የሚደረግበት ወቅት ነዉ። በጎርጎረሳዊዉ 2016 ዓ,ም በሶማልያ ምርጫ ይደረጋል ብለን እናምናለን፤ ግን ይህን ምርጫ በጥንቃቄ እና በትልቅ ብልሃት ማካሄድ አለባቸዉ ምክንያቱም ሶማልያ አሁንም ቢሆን በፖለቲካዉ ሥርዓት ዉስጥ የሚካሄድን ግጭት ሊቋቋም እና ሊያራምድ የሚችል በቂ ተቋማት የሌላት ሀገር ናት። ስለዚህም መሪዎች ለምርጫዉ ዝግጅት በማድረጉ ሂደት ብልሃት መስራት ይጠበቅባቸዋል።»
ባለፈዉ ወር የሶማልያዉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብዱዊሊ ሺካህ አህመድ ለፕሬዚዳንቱ ቅርብ የሆኑ ባለስልጣናት ጨምሮ የካቢኔ ሚኒስትሮች የሹም ሽር ያደረጉበትን ርምጃ ያልተጠበቀ አስደንጋጭ ማለታቸዉ ይታወሳል። በሶማልያ የከፍተኛ ባለሥልጣናት የስልጣን ሽኩቻን በተመለከተ በሶማልያ የተመድ መልክተኛ ኒኮላስ ኬ በሃገሪቱ በመጭዉ ዓመት አዲስ ሕገ-መንግሥት ለማፅደቅ የሚደረገዉን ጥረት እንዲሁም በጎርጎረሳዉያኑ 2016 ዓ,ም ሊደረግ የታቀደዉን ምርጫ አደጋ ላይ ይጥለዋል ሲሉ ተናግረዋል። ሶማልያና ሶማልያዉያን የተሻለ ነገር ሊመጣላቸዉ ይገባል ያሉት ኒኮላስ ኬ በሶማልያ የሕግ - አርቃቂዎች ከአሁኑ ምርጫዉን በማጭበርበር ተግባር ጉቦን ተቀብለዋል የሚለዉ ዘገባንም አይተዉ ስጋት ላይ እንደገባቸዉ መናገራቸዉ ተገልፆአል። በአፍሪቃዉ ቀንድ ሃገራት የአዉሮጳ ሕብረት ልዩ መልክተኛ አሌክሳንደር ሮንዶስ ሃሳብም ይኸዉ ነዉ፤
«የባለስልጣናቱ የስልጣን ሽኩቻ ሶማልያ ዉስጥ በሁሉም አቅጣጫ የሚያስከትለዉ ተፅዕኖ ይኖራል። በመጀመርያ ደረጃ በሀገሪቱ ተገቢ የፀጥታ ሥርዓት እንዴት አስተማማኝ ማድረግ ይቻላል በሚለዉ ላይ አንድ ዓይነት ስምምነት ሊሰረግ ይገባል፤ ምን አይነት ወታደራዊ ኃይል መኖር ይኖርበታል በሚለዉና በመሳሰሉት ስምምነት ላይ መደረስ አለበት። ሥለዚህም ይህ የስልጣን ሽኩቻ ይህን የመሳሰሉ ዉይይቶችን እና ዉሳኔዎችን ያጓትታል። በሁለተኛ ደረጃ በሀገሪቱ የፖለቲካ ሂደት የፊደራል ሥርዓት ለመመስረት ዝግጅት በመኖሩ ሥራዉ በአስቸኳይ ለዉጥ ማሳየት ይኖርበታል። በሶስተኛ ደረጃ የሕገ-መንግስቱን ምስረታ ለማጠናቀቅ የሚያበቃዉን እጅግ አስፈላጊ የሆነዉን የፓርላማ ሥራ ያዘገያል። ስለዚህም የስልጣን ሽኩቻዉ በሕገ-መንግስቱ ምሥረታ፤ በፀጥታዉ ሁኔታ እንዲሁም በፖለቲካዉ ሂደት አኳያ መፈፀም የሚኖርባቸዉን እጅግ ወሳኝና አስፈላጊ ነጥቦች ሁሉ ያዘገያል።»
በጎርጎሮሳዊዉ 2012 ዓ,ም ሥልጣንን የተረከበዉ የወቅቱ መንግሥት በጎርጎሮሳዊዉ 1991 ዓ,ም የዚያድ ባሬ መግሥት ተንኮታኩቶ ሀገሪቱም ከሁለት አስርተ ዓመታት በላይ በጦርነት ከተዘፈቀች በኋላ በዓለም ላይ ለመጀመርያ ግዜ ተቀባይነት ያገኘ የሶማልያ መንግሥት ነዉ።
በሶማልያ የሽግግር መንግሥት ተመሥርቶ በሀገሪቱ እጅግ በከፍተኛ ሁኔታ የሚታየዉን ሙስና ለመቅረፍ እና ሰላም ለማምጣት የሚደረገዉ ጥረት ለሰላማዊዉ ትዉልድ አንድ ትልቅ እድልን ፈጥሮለታል።
እንዲያም ሆኖ የሶማልያም መንግሥት ባለስልጣናት መካከል የሚታየዉ የፖለቲካ ጭቅጭቅና ሙስናን በተመለከተ የሚወጡት ዘገቦች፤ እንደ ቀድሞዉ የሶማልያ አስተዳደር ሁሉ በሙስና በዉስጥ ለዉስጥ የሥልጣን ሽኩቻ ተከፋፍሎ ከአሸባብ የደቀነዉን ስጋት በጋራ ለመቋቋም ሳንክ ፈጥሮበታል። የአዉሮጳ ሕብረት ልዩ መልክተኛ አሌክሳንደር ሮንዶስ እንደሚሉት ጎረቤት ሃገራት፤ የምስራቅ አፍሪቃ በይነ መንግሥታት ማለትም ኢጋድ እና አዉሮጳዉ ሕብረት በሶማልያ በባለስልጣን መካከል የተፈጠረዉን ችግር ለመቅረፍ እየተሠራ ነዉ።
«የሶማልያ ጎረቤት የሆነ የትኛዉም ሃገር ሁኔታዉ የማይሻሻል ከሆነና እስካሁን የተጀመሩትን ጥሩ ተግባራት ሲቀጥሉ ካላየ መስጋቱ አይቀርም። እናም አሁንም በጣም ብዙ ስራ መስራት ያስፈልጋል። ጎረቤት ሃገራት ሶማልያ የተረጋጋች፤ በመረጋጋት ላይ ያለች፤ ሃገር ናት የሚለዉ ስሜት እንዲሰማቸዉ ያስፈልጋል። እንዲህ ያለዉ የስልጣን ሽኩቻ እና መጓተት ጎረቤት ሃገራት በሶማልያ ላይ ያላቸዉን እምነት ያላላል። በሌላ በኩል የኢትዮጵያ መንግስት እንዲሁም የምስራቅ አፍሪቃ በየነመንግሥታት «ኢጋድ» በሶማልያ የተከሰተዉን የፖለቲካ ልዩነት መፍትሄ ለማግኘት የተቻላቸዉን ሁሉ እያደረጉ እንደሆን አዉቃለሁ። በሶማልያ በአሁኑ ሰዓት ለተከሰተዉ የፖለቲካ ችግር መፍትሄ ለማግኘት ሁላችንም በጋራ እየሰራን ነዉ።»
የተመድ ዋና ፀሐፊ ባን ኪ ሙን ባለፈዉ ሳምንት መቃዲሾን በጎበኙበት ወቅት በሀገሪቱ የአስቸኳይ ርዳታ ካልደረሰ የረሃብ ሥጋት መደቀኑን ተናግረዋል። የዛሬ ሶስት ዓመት በሶማልያ በደረሰዉ ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ከ 250,00 በላይ ሰዎች መሞታቸዉ ይታወቃል። በአሁኑ ወቅት በሶማልያ ከሶስት ሚሊዮን ሕዝብ በላይ አስቸኳይ የምግብ ርዳታ ያስፈልገዋል።


አዜብ ታደሰ
ሸዋዬ ለገሰ

Türkei UN Somalia
የሶማልያዉ ምክትል ሚኒስትር አብዱዊሊ ሺካህ አህመድ፤ የተመድ ዋና ፀሐፊ ባንኪሙን እና የቱርኩ ጠቅላይ ሚኒስትር አህሜት ዳቩቱግሉምስል AP
UN Vollversammlung 26.09.2014 - Hassan Sheikh Mohamud
የሶማልያዉ ፕሬዚዳንት ሃሰን ሼኪ ሞሃመድምስል Reuters/Lucas Jackson
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ