1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሱዳን የልማት ዕቅድና ሰላም ሃሳብ አልተገናኙም

ዓርብ፣ ጥር 20 1997

በካርቱም የሚገኙ የእርዳታ ሰራተኞች የሱዳን መንግስት የገባዉን የተኩስ አቁምና የሰላም ስምምነት ዉል በመጣስ የዳርፉርን ሰሜናዊ ክፍል በቦምብ መደብደቡን አስታወቁ። ድርጊቱን ዩናይትድ ስቴትስና ብሪታንያ አወገዙ።

https://p.dw.com/p/E0kV

የሱዳን መንግስት በበኩሉ አማፅያኑ በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ መንደሮችን በማቃጠል የበርካታ ሰዎችን ህይወት ለሞት የዳረገ ጥቃት አድርሰዋል ቢልም የአይን ምስክሮች እንደሚሉት ጥቃቱን የተፈፀመዉ በአዉሮፕላን ነዉ።
መጀመሪያ አዉሮፕላኖች ዝቅ ብለዉ በደቡብ ኤል ፋሸር ወደ አልማለም አካባቢ ሲበሩ አየን ከዚያም ከዚያዉ አቅጣጫ የፍንዳታ ድምፅ ሰማን ። ይህ ብቻም አይደለም የታጠቁት የአረብ ሚሊሻዎችም በመንደሩ ኗሪዎች ላይ ጥቃት በመሰንዘር ሶስት ሰዎችን ገድለዋል። የሚሊሺያዎቹም መሪ በቁጥጥር ስር ዉሏል በማለት የአይን ምስክሮች እማኝነታቸዉን ገልፀዋል።
በአካባቢዉ ለእርዳታ ተግባር የተሰማሩ ሰራተኞችን የአይን ምስክርነት ተከትሎም ይህ አሳፋሪ ተግባር መወገዝ እንዳለበት የብሪታንያ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር ጃክ ስትራዉ አሳስበዋል።
ይህ ተግባር ዳርፉርን አስመልክቶ በፀጥታዉ ምክር ቤት፤ በአፍሪካ ህብረትና በሱዳን መንግስት መካከል የተካሄደዉን የሰላም ዉይይት ዋጋ የሚያሳጣ አፍራሽ ድርጊት ነዉ።
የአፍሪካ ህብረት ኃይሎች ማክሰኞ ዕለት የአዉሮፕላን በረራ ከማየታቸዉ ሌላ ስለደረሰዉ ጉዳት ያረጋገጡት ነገር ባለመኖሩ ተከሰቷል የተባለዉን የቦምብ ጥቃት አስመልክቶ ክትትል እያደረጉ ነዉ። ስትራዉ በተጨማሪ የአማፅያኑ ቡድን በተደጋጋሚ እያደረሰ ያለዉን ጥቃትም ያወገዙ ሲሆን ድርጊቱ የወደፊቱን የፀጥታ ሁኔታና ቡድኑ እታገልላቸዋለሁ የሚላቸዉን ህዝቦች ሰላም የሚያደፈርስ መሆኑን ገልፀዋል።
ባለፈዉ ሚያዝያ ላይ ከተፈረመዉ የተኩስ አቁም ስምምነት ወዲህ በአካባቢዉ ወደ 100 የሚጠጉ ስምምነቱን የጣሱ ተግባራት የተፈፀሙ ሲሆን የሱዳን መንግስትም በበኩሉ ዉሉ በዳርፉር ያለዉን ሁኔታ ለመቆጣጠር አዉሮፕላኔን ወደስፍራዉ መላክን አያግደኝም ብሏል።
በሌላ በኩል በዚሁ ሳምንት መጀመሪያ አካባቢ የአዉሮፓ ህብረት 50 ሚሊዮን ዩሮ በዶላር ሲተመን 65 ሚሊዮን ዶላር የሚሆን እርዳታ የፈረመችዉን የሰላም ስምምነት በማክበር በልማት ዘርፍ ለዉጥ እንድታሳይ ለሱዳን ለመስጠት ተፈራርሟል።
ስምምነቱን የፈረሙት ከአዉሮፓ ህብረት በኩል የኮሚሽኑ ፕሬዝዳንት ጆሴ ማኑኤል ባሮሶና የልማት ኮሚሽነር ሉዊስ ሚሸል ሲሆኑ ከሱዳን ደግሞ ምክትል ፕሬዝዳንት አሊ ሶስማን ሞሃመድ ጠሃና የሱዳን ህዝቦች ነፃ አዉጪ ንቅናቄ የዉጪ ግንኙነት ኮሚሽነር ናሂል ዴንግ ናይ ናቸዉ።
የአዉሮፓ ኮሚሽንና የአዉሮፓ ህብረት ሃላፊ እንደተናገሩት ግማሹን ለደቡቡ ቀሪዉን ደግሞ ለሰሜኑ የሱዳን ክፍሎች የልማት ተግባር እንድታዉለዉ የታቀደ በቅርቡ የሚለቀቅላት በርከት ያለ የገንዘብ እርዳታ ይኖራል።
ህብረቱ ለሱዳን ሊሰጥ ካቀደዉ መካከል የመጀመሪያዉን አሁን ለመስጠት የፈለገበት ዋነኛ ምክንያት የደቡቡም ሆነ የሰሜኑ የሱዳን ህዝብ የሰላምን ዉጤት እንዲረዳዉ ለማድረግ ታስቦ ነዉ።
ሆኖም ግን ለሱዳን ሊሰጣት የታቀደዉ የገንዘብ ድጋፍ ቅድመ ሁኔታዎችን ያካተተ ነዉ።
በተለይ በምዕራባዊዉ የአገሪቱ ክፍል በዳርፉር እስካሁን ያልተረጋጋዉ የፀጥታ ሁኔታ የአገሪቱን የበላይ አካላት ተጨማሪ ጥረት የሚጠይቅ እንደመሆኑ መጠን በአካባቢዉ ሁኔታ ለዉጥ ማሳየት ይኖርበታል።
ኮሚሽነሩ እንደሚሉት በዳርፉር አካባቢ መሻሻል ከታየ እርዳታዉ ለአካባቢዉ ኗሪዎች የምግብ አቅርቦት፤ ለትምህርት፤ ተፈናቃዮቹን ለመደገፍና ለአገሪቱ ልዩ ልዩ ተቋሟት አስተዳደራዊ ተግባር መዋል ይችላል።
በህብረቱና በሱዳን ባለስልጣናት መካከል የተደረገዉ ይህ ስምምነት በሁለቱ ወገኖች መካከል ሊኖር ለሚችለዉ ጤናማ ግንኙነት የመጀመሪያ ደረጃ ቢሆንም ጠቃሚ እርምጃ መሆኑን ኮሚሽነር ሚሼል ለጋዜጠዎች ገልፀዋል።
በመሆኑም ኮሚሽነሩ እንዳሉት ህብረቱ ለሱዳን ከያዘዉ የ14 አመታት የልማት እርዳታ የጊዜ ገደብ ዉስጥ በመጪዎቹ ሶስት አመታት ዉስጥ የገንዘብ እርዳታዉን ለመስጠት ዝግጁ ነዉ።
በአለም ግምባር ቀደም እርዳታ ለጋሽ የሆነዉ የአዉሮፓ ህብረት ይህን አስመልክቶ ከሱዳን ጋር መተባበር ያቆመዉ እ.ኤ.አ. ከ1990 ዓ.ም, ወዲህ ሲሆን በ1999 ዓ.ም. ላይ የፓለቲካ ጉዳዮች ላይ ብቻ ከሱዳን ጋር ተወያይቶ ነበር።
በሱዳንና በአዉሮፓ ህብረት መካከል እንደገና የታደሰዉ ይህ የሞቀና የጠነከረ ግንኙነት ሱዳን በልማት ረገድ 400 ሚሊዮን ዩሮ ወይም 518 ሚሊዮን ዶላር ለማግኘት መንገዱን አቻችቶላታል።
ሆኖም ሱዳን ይህን ለማግኘት የተቀመጠላት ቅድመ ሁኔታ አንድ ብቻ ነዉ በቅርቡ የተፈራረመችዉን የሰላም ስምምነት ተግባራዊ ማድረግ።
በዳርፉር ያለዉ ግጭትና የደፈረሰዉ የሰላም ሁኔታ በዚህ ከቀጠለ ግን በሱዳን የታሰበዉ ልማትና የሰላም ዕቅድ ሁሉ ምኞት ብቻ ሆኖ ሊቀር ይችላል።