በማሊ የቀጠለው ውዝግብ
ቅዳሜ፣ ነሐሴ 5 2004
ባካባቢው የሸሪዓ ሕግ ማወጃቸውን ያስታወቁት በምሕፃሩ ሙዣዎ የተባለው ለአንድነትና ጂሃድ ንቅናቄ ዓማፅያን ከሌኦች ቡድኖች ጋ ባንድነት ካለፈው ሚያዝያ ወዲህ ሰሜናዊውን ማሊ ተቆጣጥረዋል። ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ጎረቤት ሀገሮች ባማኮ የሚገኘው የማሊ መንግሥት በሀገሩ የቀጠለውን ውዝግብ ባስቸኳይ እንዲያበቃ ግፊት ያሳረፉ ሲሆን፡ ይህችኑ ምዕራብ አፍሪቃዊት ሀገር የጎበኙት የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ድርክ ኒብል አስቸኳይ መፍትሔ እንዲገኝ አሳስባለች። ይሁንና፡ በዚች ውዝግቡ በተካረረባትና መከፋፈል ባሰጋት ሀገር ውስጥ በቅርቡ ሰላም እንዴት ሊመለስ ይችላል ነው ጥያቄው።
ደቡባዊውን ማሊ የጎበኙት የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ድርክ ኒብል በሰሜናዊ ማሊ የሚታየው ሰብዓዊ ሁኔታ እጅግ አሳሳቢ ሆኖ ነው ያገኙት። ይሁንና፡ ሚንስቴራቸው በዚሁ አካባቢ ለሚኖረው ሕዝብ እንደሚፈለገው አስቸኳዩን ርዳታ ማቅረብ እንደማይችል ገልጸዋል።
« ያካባቢው ፀጥታ ሁኔታ ሲፈቅድ ብቻ በቀጥታ ሕዝቡን የሚጠቅም ርምጃ እንወስዳለን። ከዚችው ሀገር ጋ የልማት ትብብሩን የምንጀምረው ግን ሕገ መንግሥታዊው ሥርዓት እንደገና ሲሟላ ይሆናል። » እስከዚያ ድረስ ግን ጀርመን ለተቸገሩት የሰሜን ማሊ ነዋሪዎች ቢያንስ የምግብ ርዳታ እንደምታቀርብ አስታውቃለች።
በማሊ ሁኔታዎች እንዲስተካከሉ በዋነኝነት ጥረት የጀመረው የምዕራብ አፍሪቃ መንግሥታት የኤኮኖሚ ማህበረሰብ በምሕፃሩ ኤኮዋስ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ የማሊ የሽግግር መንግሥት በሀገሩ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲያቋቁም ግፊት ያሳረፈ ሲሆን፡ በሁለተኛነት ደግሞ ሰሜናዊውን የሀገሪቱን ከፊል ከተቆጣጠሩትና በመላ ማሊ የሸሪዓን ሕግ የማስተዋወቅ ዓላማ ይዘው ከተነሱት ሙሥሊም ፅንፈኞችም ጋ እየተደራደረ ነው፤ በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ በአንድ ዓለም አቀፍ አጥቂ ኃይል ጣልቃ ገብነት ሰሜናዊ ማሊን ከሙሥሊሞቹ ፅንፈኞች ለማስለቀቅ ርምጃ እንደሚወስድም ዝቶዋል።
ይህ ጥረቱ እስካሁን ውጤት አላስገኘም። ኤኮዋስ ለማሊ የሽግግር መንግሥት ብሔራዊ አንድነት መንግሥት እንዲያቋቁም ሰጥቶት የነበረው የጊዜ ገደብ ባለፈው ሐምሌ ወር ካለፈ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ ያስቀመጠለት ቀነ ቀጠሮ ማሊን በቅርቡ ሊያረጋጋ ይችል ይሆናል የተባለው መንግሥት ሳይቋቋም አልፎዋል።
የጀርመን የኤኮኖሚ ልማት ትብብር ሚኒስትር ድርክ ኒብል የብሔራዊው አንድነት መንግሥት በሚቀጥሉት ሁለት ሣምንታት እንደሚቋቋም ተስፋ አድርገዋል።
« አዲሱ የብሔራዊው አንድነት መንግሥት ባፋጣኝ መቋቋም ይኖርበታል። ከዚያ በኋላ ሀገሪቱን ሊያረጋጉ እና በተግባር ሊተረጎሙ የሚችሉ ግልፅ ዓላማዎችን የያዘ ዕቅድ ሊወጣ ይገባል። »
ለማሊ ቀውስ መፍትሔ አፈላላጊው የኤኮዋስ ዋነኛ ተደራዳሪ የቡርኪና ፋሶ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር ጂብሪል ባሶሌ ወደሰሜን ማሊ በመጓዝ ከተለያዩት የሙሥሊም ፅንፈኞች ቡድኖች፡ ከሙዦዋ ተጠሪዎች ጋ ጭምር ተገናኝተዋል። ዶይቸ ቬለ ያነጋገረው የማሊ ዜጋ የሆነው ጋዜጠኛው ድሪሳ ሳንጋሬ እንዳስረዳው ግን፡ ሌቦች የሚሉዋቸውን ግለሰቦች እጅ ከሚቆርጡ ፅንፈኞችና አክራሪ ሙሥሊሞች ጋ የተጀመረው ድርድር በሀገሪቱ ብዙ እያከራከረ ነው።
« ሁሉም አይደሉም ድርድሩን የሚደግፉት። ለምሳሌ ሙሥሊሞቹ ፅንፈኞች የተቆጣጠሩዋት የጎአ ከተማ ከንቲባ ይህን ዓይነቱን ድርድር ይቃወማሉ፤ ምክንያቱም እንደርሳቸው አባባል ሊታመን የሚችል ተደራዳሪ የለም። »
ያም ቢሆን ግን ኤኮዋስ በድርድሩ ለመቀጠል ነው የወሰነው፤ የሙሥሊሞቹ የረመዳን ፆም ከአሥር ቀናት ገደማ በኋላ ሲያበቃ ድርድሩን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቋል። ኤኮዋስ እንዳስታወቀው፡ ከ 3000 ወታደሮች በላይ የሚሰለፍበት አንድ አጥቂ ቡድን በማሊ ጣልቃ ይግባ አይግባ ስለሚለው ሀሳብም የጦር ጠበብት ካለፈው ሐሙስ ወዲህ በባማኮ ምክክራቸውን ቀጥለዋል። ግን እስካሁን የተመድ በማሊ ይህ ዓይነቱ አጥቂ ቡድን እንዲሰማራ ፈቃድ አልሰጠም። የማሊ የሽግግር መንግሥትም ቢሆን በዚህ ሀሳብ አኳያ እስካሁን ቁጥብነትን ነው ያሳየው።
አርያም ተክሌ
ማንተጋፍቶት ስለሺ