1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በመለስተኛ የብድር ፖሊሲ የብዙሃንን ድህነት ማለዘብ

ሐሙስ፣ ኅዳር 15 1998
https://p.dw.com/p/E0e7

ማይክሮ-ክሬዲት ወይም ማይክሮ-ፋይናንስ ዛሬ ብዙዎች የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ልማት ጠበብት ዓቢይ ትኩረት የሚሰጡት አማራጭ የዕድገት መንገድ ሆኗል። በቅርቡ ይሄው ፖሊሲ ሊስፋፋ በሚችልበት ሁኔታ ለመምከር ከመቶ የሚበልጡ ሃገራት ተጠሪዎች በተባበሩት መንግሥታት መቀመጫ በተከፈተ መድረክ ላይ ተሳታፊ ሆነው ነበር።

በተቀዳሚ በበጎ አድራጎት ላይ የተመሠረተው የመለስተኛ ብድር የማይክሮ-ክሬዲት ፖሊሲ ወደፊት ሌሎች የፊናንስ ምንጮችን በመሳብ ድሃ የሕብረተሰብ ወገኖች፣ መንግሥታትና ገንዘብ አቅራቢዎች ጭምር ይበልጥ ተጠቃሚ እየሆኑ እንዲሄዱ ለማድረግ ነው የሚታሰበው። “ዓለምአቀፍ የመለስተኛ ወይም አነስተኛ ብድር ዓመት 2005“ በሚል ኒውዮርክ ላይ ለሶሥት ቀናት በተካሄደው የመድረክ ውይይት የተባበሩት መንግሥታት የኤኮኖሚና የማሕበራዊ ጉዳይ ተቋም ምክትል ዋና ጸሐፊ ሆሴ-አንቶኒዮ-ኦካምፖ፣ የዓለም ባንክ ፕሬዚደንት ፓውል ዎልፎቪትስና ብዙዎች ቀደምት የፊናንስና የልማት ዘርፍ ባለሥልጣናት ተሳትፈዋል።

ፓውል ዎልፎቪትስ መለስተኛውን የፊናንስ ፖሊሲ ድህነትን ለመቀነስ የሚረዳ ሃያል መሣሪያ ነው ብለውታል። ሕዝብ በያለበት ገቢውን እንዲያሳድግ፣ ለቆጣቢነትና አደገኛ ሁኔታዎችን ለመቋቋም እንዲበቃ፤ እንዲሁም ከዕጅ ወደ አፍ ከሀነ ዕለታዊ ኑሮው ለወደፊት ማቀድ ወደሚያስችል አቅም እንዲሻገር የሚያደርግ ነው። መለስተኛው ብድር መደበኛ የፊናንስ አገልግሎት የማግኘት ዕድሉም ሆነ አቅሙ የሌለውን ሶሥት ቢሊዮን ገደማ የሚጠጋ የዓለም ሕዝብ እንዲያዳርስ ሆኖ እንዲስፋፋ የቀረበው ሐሣብ በኒውዮርኩ መድረክ ላይ ሰፊ ተቀባይነት ተሰጥቶታል።

በዚህ የተባበሩት መንግሥታት የመለስተኛ ብድር ዓመት ፖሊሲውን ቁጠባን፣ ማበደርን፣ መድሕንና፣ የገንዘብ ሽግግርን የጠቀለለ ወደሆነ አጠቃላይ የፊናንስ እንቅስቃሴ በማሳደጉ ጉዳይ ላይ ነው መድረኩ አተኩሮ የታየው። ይህም ያለ ምክንያት አይደለም። ዋናው መልዕክት በዓለም ዙሪያ የሚገኙ በቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ድሃ ሕዝቦች ከአቅማቸው የተጣጣመ የገንዘብ ምንጭ እንዲኖራቸው የፊናንስ ዘርፎችን የመጠቅለል ታላቅ ግፊት ወይም ፍላጎት አለ።

ማይክሮ-ክሬዲት በመሠረቱ ተበዳሪዎች ትናንሽ ንግዶችን በመክፈት ከድህነት እንዲላቀቁ ለማድረግ የሚሰጥ መለስተኛ ብድር ነው። ውስብስውነት የሌለበት ብድር ተመልሶ የሚከፈልበት ጊዜም በአብዛኛው ከስድሥት ወር እስከ አንድ ዓመት ለተበዳሪው ጊዜና ፋታን የሚሰጥ ነው። ይህን መለስተኛ ብድር ከመደበኞቹ ባንኮች ብድር መውሰድ አቅም ለሌላቸው ወገኖች የመስጥበት ፖሊሲ ማይክሮ-ክሬዲት በሥራ ላይ መዋል የጀመረው በባንግላዴሽ በ 70ኛዎቹ ዓመታት ነበር።
ከዚያን ወዲህ ዕድሉን በመጠቀም ከራስ አልፈው ቤተሰባቸውን ጭምር ለመጥቀም፤ እንዲያም ሲል ሌሎችን ቀጥሮ ለማሰራት የበቁት የዕቅዱ ተረጂዎች ብዙዎች ናቸው። ዛሬ ከባንግላዴሽ እስከ አፍጋሃኒስታን፤ ከላይቤሪያ እስከ ደቡብ አፍሪቃ በአንድ መቶ ዶላርና ከዚያም ከፍ ባለ ብድር ከችግር ያመለጡት ተረጂዎች ለፖሊሲው ጠቃሚነት በምሳሌነት የሚጠቀሱ ናቸው። በኒውዮርኩ መድረክ ላይ ቻይናን፣ ሕንድን፣ ላይቤሪያን፣ ማላዊንና ሢየራሌዎንን ጨምሮ በአርአያነት ዕርምጃ ያደረጉት ከክብር እንግዶች ከታዋቂ የኪነትና የፖለቲካ ሰዎችች ዕጅ ሽልማት ተቀብለዋል።

ብዙዎች ተናጋሪዎች በዚህ ዓለምአቀፍ የማይክሮ-ክሬዲት ዓመት የታየው ዕርምጃ ቀጣይና ወደፊት ሁሉም የሚያስፈልገውን የፊናንስ አገልግሎት ለማግኘት የሚበቃበት ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ነው ጽኑ ተሥፋቸውን የገለጹት። የተባበሩት መንግሥታት የልማት ዕቅድ ዘርፍ ባልደረባ ክሪስቲና ባሪኑ እንደሚሉት የመለስተኛው ብድር ዓመት ሰፊ የዕድገት በር ከፍቷል፤ በጉዳዩ የዓለም ሕብረተሰብ ንቃተ-ሕሊናም በመቶ ዕጅ ነው የጨመረው። እርግጥ ብዙዎች እንዳመለከቱት የግሉ የኤኮኖሚ ዘርፍ ተሳትፎ ገና እጅግ በጣም ይፈለጋል።

በቅርቡ የወጣ አንድ የዓለም ባን’ክ የልማት ዘገባ እንዳመለከተው በአብዛኛው በመንግሥታትና በለጋሾች ሲራመድ የቆየው የማይክሮ-ፋይናንስ ፕሮግራም ይበልጥ የግሉን የንግድ ዘርፍ ድጋፍ እንዲያገኝ የሚደረገው ጥረት ሲጠናከር ነው የሚታየው። የዓለም ባንክ ብድሩ የሚሰጥበትን ሁኔታ ማቃለሉ የበለጠ ገንዘብ ወደ ገጠር አካባቢዎች እንዲዘልቅ ለማድረግ ጠቃሚ መሆኑንም አመልክቷል። ይህ ደግሞ በተጨባጭ መረጃ የተደገፈ ነው። ለምሳሌ በባንግላዴሽ መለስተኛው ብድር ሊደርሰው ከቻለው ድሃ ቤተሰብ ግማሽ ገደማ የሚጠጋው የኑሮ ደረጃው ከዝቅተኛው የድህነት መስፈርት በላይ ሊያድግ ችሏል። የተባበሩት መንግሥታትን የሚሌኒዬም ዕቅድ ጭብጥ በሆነ መልክ መደገፉ በግልጽ የሚታይ ነው።

በዚህ የማይክሮ-ፊናንስ፤ የአነስተኛ ብድር አገልግሎት ዓመት የዓለም ባንክና ድሆችን ለማገዝ የተቋቋሙ አማካሪ ቡድኖች በዓለም ዙሪያ ከሚገኙ ብሄራዊ ኮሚቴዎች ጋር በመተባበር በያገሩ ፖሊሲውን ድህነትን ከመታገሉ ተግባር ጋር በማስተሳሰር ጉባዔዎች እንዲካሄዱ አድርገዋል። በዚሁ ጥረት የተካሄዱት ጉባዔዎችም ከሶሥት መቶ ይበልጣሉ። በየቦታው ከመቶ የሚበልጡ ብሄራዊ ኮሚቴዎች ሊፈጥሩም በቅተዋል።

በመለስተኛው ብድር ዓመት አንዱ ጥልቅ ዕርምጃ ሆኖ የሚቆጠረው ዕቅዱ ሴቶችን በሰፊው እያዳረሰ መምጣቱ ነው። በዚህም በመሠረቱ የተባበሩት መንግሥታት ተልዕኮ የሆነው የሴቶችን ሕብረተሰባዊ ይዞታ የማሻሻል ተግባር ሰፊ ትኩረት ሊያገኝ መቻሉ አልቀረም። ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሴቶች የፊናንሱ አገልግሎት ተጠቃሚዎች ለመሆን መብቃታቸው በቤተሰብና በሕብረተሰብ ውስጥ ተደማጭነታቸው እንዲጠነክሩ፤ እንዲያም ሲል በራስ መተማመንን እንዲያዳበሩ እያደረገ ነው።

ሴቶች ቤትና ንብረትን ጨምሮ ንብረት እንዲያፈሩ፤ በሕብረተሰብ የውሣኔ ሂደት ላይም ጠንካራ ሚና እንዲኖራችው ሂደቱ ገንቢ መሆኑ ነው በፖሊሲው አራማጆች የሚታመነው። የኒውዮርኩ መድረክ የብሄራዊና ዓለምአቀፍ ተቋማት፣ የዓለም ባንክ፣ የዓለምአቀፉ ምንዛሪ ተቋም IMF፣ የማዕከላዊ ባንኮችና የግሉ ኤኮኖሚ ዘርፍ ተጠሪዎች፤ እንዲሁም ራሳቸው የፖሊሲው ተጠቃሚዎች የተሳተፉበት ነበር። ይህም በአንድ ወገን በተቀመጠ ሃሣብ ከማተኮር ይልቅ ነጻ ክርክር የሚካሄድበት ስብሰባ እንዲሆን አድርጎታል።

የአውሮፓ ሕብረት የመጪው 2006 በጀት መጽደቅ መቻል-አለመቻል የያዝነው ዓመት ሊገባደድ በተቃረበበት በአሁኑ ወቅት አጠያያቂ ሆኖ እንደቀጠለ ነው። የአውሮፓ ም/ቤት በወቅቱ በየመንፈቁ የሚቀያየረውን የሕብረቱን ርዕስነት ይዛ የምትገኘው ብሪታኒያ በገንዘብ አወጣጥ ደረጃ በሚካሄደው ድርድር የምታሳየውን ግትርነቷን ካላቆመች በጀቱን ሊቃወመው እንደሚችል ከትናንት በስቲያ አስጠንቅቆ ነበር። ከአውሮፓ ም/ቤት ጋር በጉዳዩ የሚደረጉት ድርድሮች ለብሪታኒያ የርዕስነት ሚና ብርቱ መፈተሻ እንደሚሆን የሸንጎው የበጀት ኮሚቴ መሪ ያኑሽ ላቫዶቭስኪ ሳያስገነዝቡ አላለፉም።

የሚቀጥለው ዓመት በጀት ተቃውሞ ገጥሞት ሳይጸድቅ ቢቀር ተከታዩን ይበልጥ ክብደት የሚሰጠውን የ 2007-2013 የረጅም ጊዜ በጀት የመንግሥታት ንግግር ይበልጥ የሚያወሳስብና አጠቃላዩን የፊናንስ ዕቅድ ከንቱ የሚያደርግ ነው የሚሆነው። ብዞዎች እንደራሴዎች ብሪታኒያ ለአስታራቂ ሃሣብ ቅን ሆና አለመገኘቷን ለችግሩ ዋና መንስዔ ያደርጋሉ።

የሃያ አምሥቱ የሕብረቱ ዓባል መንግሥታት የፊናንስ ባለሥልጣናት በመጪው በጀት ረቂቅ በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ጊዜ ይመክራሉ። በዕለቱ ሂደት ርዕስነቱን የያዘችው የብሪታኒያ፣ የአውሮፓ ኮሚሢዮንና የም/ቤቱ ተጠሪዎች አስታራቂ መፍትሄ ለማግኘት ተገናኝተው እንደሚነጋገሩም ነው የሚጠበቀው። ታዲያ ክርክር የተያዘበት የበጀቱ ረቂቅ ተቀባይነት ቢያጣ የዚህን 2005 ዓ.ም. በጀት ከጊዜው የምንዛሪ ሁኔታ አጣጥሞ እንዳለ ወደሚቀጥለው ከማሻገር ሌላ ምርጫ አይኖርም።
ይህ ደግሞ በተለይ የሕብረቱ መንግሥታት በረጅም ጊዜ በጀታቸው ላይ ከስምምነት ካልደረሱ ለተከታታይ ዓመታት የዝቤት መሠረት እንደሚሆን ጨርሶ አያጠራጥርም። የሕብረቱ ዋነኛ ሥራ አስኪያጅ አካል፤ የአውሮፓው ኮሚሢዮን ሃሣብ ያቀረበው የመጪው ዓመት ወጪ 113 ቢሊዮን ኤውሮ ገደማ የሚጠጋ እንዲሆን ነው። በሌላ በኩል ብሪታኒያን ጨምሮ መላው ዓባል መንግሥታት በጀቱ በ 1,2 ቢሊዮን ዝቅ ያለ እንዲሆን ይፈልጋሉ።

ኮሚሢዮኑ በበኩሉ ያቀረበው የበጀት አሃዝ ማቆልቆል ከሕብረቱ ወደ ምሥራቅ መስፋፋት አንጻር አስፈላጊ የሆኑ አዳዲስ ሠራተኞችን ለመቅጠር እንዳይችል የሚያደርገው መሆኑን በማመልከት አቤቱታ ያሰማል። ባለፈው ዓመት በሠራተኛው እጥረት የተነሣ የምርምርና የልማት ፕሮዤዎችን መቀነስ መገደዱን፤ የውጭ ዕርዳታ አመዳደብን በተመለከተም ችግር ገጥሞት እንደነበር ነው የሚያስገነዝበው።

ሆኖም ብሪታኒያና ሌሎች ቀደምት የሕብረቱ ገንዘብ አቅራቢዎች ብዙዎቹ መንግሥታት ከፍተኛ የበጀት ኪሣራን በመታገል ላይ ባሉበት በአሁኑ ወቅት የበጀት ቁጠባ ግድ ነው ባዮች ናቸው። የአውሮፓ ም/ቤት በአንጻሩ ይህን ሃሣብ ሳይቀበለው ቆይቷል። እርግጥ በተቃውሞ ብቻም እተወሰነም። ሁኔታውን ለመለወጥ ድምጽ በመስጠት፤ እንዲያውም ተጨማሪ 2,8 ቢሊዮን ኤውሮ ወጪ ለምርምር፤ ለልማትና ለአካባቢዎች የዕርዳታ ዕቅድ እንዲሰጥ ወስኖ ነበር።

የአውሮፓ ሕብረት መንግሥታትና ም/ቤቱ በወጪ ጉዳይ የተለያየ ዝንባሌ ሲያሣዩ ይህ የአሁኑ ለነገሩ ለመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። የመጨረሻው እንደማይሆንም ዕሙን ነው። ግን እስካሁን ከአንድ አስታራቂ ሃሣብ ለመድረስ የተሣናቸው ጊዜም የለም። ይሁን እንጂ የአውሮፓ ም/ቤት እንደራሴዎች ዘንድሮ በተለየ የትግል ስሜት የተነሳሱ ነው የሚመስለው። የሕብረቱ ርዕስ ብሪታኒያ ለሃሣባቸው ተገቢውን ትኩረት አለመስጠቷ በቀላሉ ሊዋጥላቸው አልቻለም።

እርግጥ ብሪታኒያ በፊታችን ታሕሣስ የመጀመሪያ አጋማሽ ላይ በሚካሄድ ጉባዔ ለ 2007-2013 የረጅም ጊዜ በጀት ከአንድ አስታራቂ ስምምነት እንዲደረስ ትፈልጋለች። ሆኖም አዝጋሚ ወይም ተጎታች የድርድር ዘይቤዋ መሰናክል እንዳይፈጥር የሚሰጉት ብዙዎች ናቸው። በአጠቃላይ በፊታችን ታሕሣስ መጨረሻ ላይ የሚያበቃው የብሪታኒያ የርዕስነት ዘመንና ሚናዋ በበጀቱም ሆነ በሌሎች የጋራ ጉዳዮች ቀደም ካሉት ሁሉ ቢቀር እስካሁን የደበዘዘ ነው።