ሶሪያ: የዉጊያ፥ምርጫና ሥጋት ምድር
ረቡዕ፣ ግንቦት 1 2004
09 05 12
የሶሪያ መንግሥት ጦርና በመንግሥት ላይ ያመፁት ታጣቂዎች ተኩስ ለማቆም የገቡትን ቃል ጥሰዉ በየአካባቢዉ የሚያደርጉት ግጭትና ዉጊያ እንደቀጠለ ነዉ።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የአረብ ሊግ ልዩ መልክተኛ ኮፊ አናን ያደራደሩት የተኩስ አቁም መጣሱ በሚያነጋግርበት መሐል ሶሪያ ዉስጥ የምክር ቤት አባላት ምርጫ ተደርጓል።ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ የምርጫዉን አላማና ሒደት ሲያደንቁ፥ ተቃዋሚዎቻቸዉ አጣጥለዉ ነቅፈዉታል፥ ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ በበኩላቸዉ ሶሪያ ወደ ሙሉ የርስ በርስ ጦርነት ትገባለች ብለዉ እንደሚሰጉ አስጠንቅቀዋል።ነጋሽ መሐመድ አጭር ዘገባ አጠናቅሯል።
ገሚሱ ይመርጣል-ይመረጣል።ሌላዉ በየቤቱ አድፍጧል።የተቀረዉ ያምፃል፥ ወይም ይዋጋል። መንግሥት የሚቆጣጠረዉ ቴሌቪዥን ጣቢያ የምክር ቤት እንደራሴዎቹን ለመምረጥ በየድምፅ መስጪያ ጣቢያዉ የተሰለፈዉን ሕዝብ ብዛት፥ የድምፅ አሰጣቱን ሒደት፥ የተፎካካሪዎችን መልዕክት ያንቆረቁራል፥-ሰኞ አንድ፥ ዛሬ ሰወስተኛ ቀኑ።
የአማፂያን ቪዲዮዎች ደግሞ ኦና ቤት-ሠፈሮች፥የቤት-ሕንፃ ፍርስራሽ የተከመረባቸዉ አረዳ-መደብሮች፥ የጎማ፥ ቃጠሎ-ጢስ ጠለስ እና ተኩስ፥ ዉጊያ ትርምስን ሲያሳዩ ነዉ ከሰኞ- ዛሬ የደረሱት።ሶሪያና ሶሪያዎች።ፖለቲከኞቻቸዉም እንደዚያዉ።
«አዉራ-መንገድ የማይወጡት፥ ሕግ የማይጥሱት ወይም የማይገድሉት አብዛኞቹ ሶሪያዉን የተሐድሶ ለዉጥ ይፈልጋሉ።»
ፕሬዝዳት በሽር አል-አሰድ።ለሳቸዉ የሰኞዉ ምርጫ የተሐድሶ ለዉጣቸዉ አካል፥ ለሶሪያዊዉ ፖለቲካዊ ጥያቄ መልስ ሰጪ ነዉ።ከዚሕ ቀደም በዘጠና ከመቶ ድምፅ ፀደቀ በተባለዉ ሕገ-መንግሥት መሠረት እስካሁን በሥልጣን ላይ ያለዉ የባዓዝ ፓርቲ በሚቆጣጠረዉ ምክር ቤት ተቋዋሚዎችም ይገባሉ።
በዚሕም መሠረት ሁለት መቶ ሐምሳ መቀመጫ ላለዉ ምክር ቤት አባልነት በሐገር ዉስጥ ያሉ የአንዳድ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ እጩዎች ተወዳድረዋል።የፕሬዝዳት አሳድ መንግሥት መወገድ አለበት የሚሉት ሐይላት ግን ገሚስ ሶሪያ በደም አበላ እየራሰች የምን ምርጫ ባይ ናቸዉ።«የሶሪያ ብሔራዊ ምክር» የተሰኘዉ የተቃዋሚዎች ስብስብ ቃል-አቀባይ ሎይ ሳፊ ደግሞ የምን ምርጫ-ይላሉ።
«አሳፋሪ ነዉ።ማለቴ ገሚስ ሐገሪቱ ጦርነት ላይ እያለች፥ ጦሩ ከተሞችን እያጠፋ እንዴት ምርጫ ሊደረግ ይቻላል።»
ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን የሸመገሉት ስምምነት ዘጠኝ ሺሕ ያሕል ሰዉ የገደለ፥ ብዙ ሺዎችን ያቆሰለ፥ ያሰደደዉን ዉጊያ ጦርነት ለማስቆም ያለመ ነበር።ሥምምነቱ ከፀደቀ ወዲሕ ጦርነቱ መቀነሱ አልቀረም።ሥምምነቱ ወር ሊደፍን ዕለታት ሲቀሩት ትናንት ልዩ መልዕክተኛ ኮፊ አናን ለፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት እንደነገሩት ግን ሶሪያ ከለየለት የርስ በርስ ጦርነት እንዳትዘፈቅ ያሰጋል።
«ሐገሪቱ ወደ ሙሉ የርስ በርስ ጦርነት ትገባለች የሚል ተጨባጭ ሥጋት አለ።የዚሕ እንድምታ ደግሞ አስፈሪ ነዉ።ይሕ እንዲሆን ልንፈቅድ አንችልም።ወታደራዊ እንቅስቃሴዉ በሆነ ደረጃ ቀንሷል።ግጭቱን ለማስቆም የተደረገዉ ሥምምነት ግን በተደጋጋሚ እየተጣሰ ነዉ።የግጭቱ መጠንና ስምነቱን የማወኩ ደረጃ ተቀባይነት የለዉም።»
አናን ይሕን ቢሉም የሠላም ሥምምነቱን የሚታዘቡ ሐይላት ወደ ሶሪያ መዝመታቸዉን እንደቀጠሉ ነዉ።ከሰወስት መቶዉ ታዛቢዎች እስከ ዛሬ ሰባዎቹ ደማስቆ ገብተዋል።ተቃዋሚዎች የአሰድ-ሥርዓትን «ለመቀባባት» ያለመ ያሉት ምርጫ ዉጤትና ፋይዳ እስከ ዛሬ አልታወቀም።የሶሪያ ጉዳይ ግን ልክ እንደ ሶሪያዎች ሁሉ ሐያላኑንም በሩቅ-ርቀት እንዳቃረነ ነዉ።
በተባበሩት መንግሥታት የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ሱዛን ራይስ፥-«ዩናይትድ ስቴትስ፥ የአሳድ ሥርዓትና አሳድ ራሳቸዉ እንዲወገዱ የሚደረግባቸዉን ግፊት በማጠናከሩ ላይ እንዳተኮረች ነዉ» ብለዋል ትናንት። ሩሲያዊዉ አቻቸዉ ቪታሊ ቹርኪን ግን የሶሪያ እዉነታ ሌላ ነዉ-ባይ ናቸዉ። ችግር ቢኖርም ሶሪያ በተገቢዉ አቅጣጫ እየተጓዘች ነዉ።እንደ ቹርኪን።
ነጋሽ መሐመድ
ሸዋዬ ለገሠ