1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

መጨረሻዋ ምን ይሆን?

ሰኞ፣ ሚያዝያ 15 2010

ሩሲያዎች የሶሪያ መንግስትን፤ አሜሪካ እና ተከታዮችዋ የመንግሥት ተቃዋሚዎች እና ሸማቂዎችን ደግፈዉ የሶሪያን ሕዝብ ሲያጨርሱ ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም፤ የተቀሩት የድርጅቱ አባል ሐገራትም ከዳር ቆመዉ ከማየት በስተቀር ያሉት፤ሊሉ የሚችሉት ነገርም በርግጥ አልነበረም።

https://p.dw.com/p/2wX7u
Niederlande Eingang der OPCW
ምስል Getty Images/AFP/J. Thys

ማኅደረ-ዜና፦ሶሪያ ወድማ የማታልቅ ምድር

አሜሪካኖች፤ ብሪታኒያዎች፤ ፈረንሳዮች፤ እስራኤሎች፤ ሌሎች የምዕራብ ተባባሪዎቻቸዉ ሲሻቸዉ አንድ ሆነዉ እንደ አንድ ኃይል፤ ሲያሰኛቸዉ ብዙ  መስለዉ ለየብቻቸዉ በቦምብ ሚሳዬል ያጋዩታል።ሳዑዲ አረቢያዎች፤ ዮርዳኖሶች፤ ግብፆች ሲቻላቸዉ በቀጥታ፤ ሲያቅታቸዉ የምዕራብ የበላዮቻቸዉን ተከትለዉ ያነድዋታል።ጋይታ፤ ነድዳ የማታልቅ ምድር።ቱርኮች ለብቻቸዉም፤ ከምብራብ ወዳጆቻቸዉም ጋር ሆነዉ ያደቅቋታል።ሩሲያዎች እና ኢራኖች በጋራም በተናጥልም ከአየር-ከምድርም ያወድሟታል።በሞስኮ-ቴሕራኖች የሚደገፉት የደማስቆ ገዢዎች እና በዋሽግተን፤ ለንደን ፓሪስ፤ ሪያድ የሚደራጁት ተቃዋሚዎች ይጨፋጨፉባታል።በሁሉም የሚጠሉት ታጣቂዎች ያሸብሯታል።ደቅቃ፤ ልማ ወድማ የማታልቅ ሐገር።ስምንተኛ ዓመቷ።ጥንት-ለቬንት፤ በመሐሉ አ-ሻም ኃላ ሶሪያም እየጠፋች፤ አንሰራርታለች፤ እየወደመች፤ አቀጥቅጣለች።አሁንስ? ላፍታ አብረን እንጠየቅ።

                                                    

የቀድሞዉ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀኃፊ ፓን ጊ ሙን ሶሪያን ከጥፋት፤ ህዝቧን ከእልቂት ማዳን የሚቻለዉ ተፋላሚዎች በድርድር ሰላም ሲያወርዱ ብቻ ነዉ ያላሉበት ጊዜ አልነበረም።ፓን የድርድርን አስፈላጊነት ከተናገሩባቸዉ በርካታ መድረኮች አንዱ ሞትረ-ስዊዘርላንድ ዉስጥ ተሰየሞ የነበረዉ የሶሪያ ተፋላሚ ኃይላት እና የየተባባሪዎቻቸዉ ተወካዮች ጉባኤ ነበር።ጥር 2014 (ዘመኑ በሙሉ እንደ ጎርጎሪያኑ አቆጣጠር ነዉ።)

                  

«እዚሕ ነጥብ (ሰላም) ላይ ለመድረስ በጣም ከባድ እንደሆነ ሁላችንም እናዉቀዋለን።ብዙ ዉድ ጊዜ እና በርካታ ሕይወት አጥተናል።እናንተንም ሆነ እኛን የሚገጥሙን ፈተናዎች ጠንካሮች ናቸዉ።ያም ሆኖ የናንተ እዚሕ መገኘት ተስፋ ይጭራል።»

በልማዱ፤ በትክክለኛ ትርጓሜዉም ድርድር ጠበኞችን እኩል የሚያሸማግል እንጂ ከጠበኞች መሐል የሚጠሉትን ጥሎ፤ የሚወዱትን አንጠልጥሎ ሊደረግ አይችልም።የዓለም ትልቅ ድርጅት መሪም ይሕን አላሉም።የትልቁ ድርጅት መስራች፤ታላቅ ዘዋሪ፤ የዓለም ልዕለ ኃያል የያኔ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ግን ነባሩን የማደራደር ልምድ እና ትርጉምን፤ የግዙፉ ድርጅት ዋና ፀሐፊን መልዕክትም እዚያዉ መድረክ ላይ ለማጣጣል ዲፕሎማሲያዊ ቃላት እንኳን ለመምረጥ አልተጨነቁም።የዩናይትድ ስቴትሱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ጆን ኬሪ።

Syrien Zerstörung in Duma
ምስል Getty Images/AFP/L. Beshara

  «እዉነታዉን መቀበል አለብን።እዚሕ ያመጣን የጋራ ሥጋት ነዉ።የሚመሰረተዉ የሽግግር መንግሥት ባንዱ ወይም በሌላዉ ኃይል በሚጠላ ወገን ሊመሰረት አይችልም።ይሕ ማለት በሽር አል-አሰድ የዚያ ሽግግር መንግስት አካል ሊሆን አይገባም።»

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ፤ የዩናይትድ ስቴትስ፤የተባባሪ እና ተከታዮችዋ መሪዎች ሥለሶሪያ  ሠላም የሚሉ-የሚያደርጉት ተቃርኖ ዓለምን ግራ ያጋባበት ያ ወቅት ቱጃሩ አሜሪካዊ ነጋዴ ወደ ፖለቲከኝነት የተቀየሩበት  ነበር።ዶናልድ ትራምፕ።ትራምፕ የትልቂቱን ሐገር ትልቅ ሥልጣን ለመቆጣጠር ያላሉ፤ያለደረጉት፤ ያልገቡት ቃል፤ የኦባማን መስተዳድርን ለመጥላላት ያልሰነዘሩት ትችት አልነበረም።በዩናይትድ ስቴትስ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዲሞክራቲኩ ፓርቲ መሪ ናንሲ ፔሎሲ ትራምፕ ያኔ ካሉት አንዱን በቀደም አስታወሱ።

 « እንደ እዉነቱ ከሆነ፤ ኦባማ (ሶሪያን ለመምታት) የምክር ቤቱን ዉሳኔ ማግኘት አለባቸዉ ብለዉ ነበር።ይሕን ያሉት ነሐሴ 29 2013 ነበር።ይኸ ሁሉ ሲሆን፤ በማግስቱም ፕሬዝደንቱ ሶሪያን ከማጥቃታቸዉ በፊት የምክር ቤቱን ይሁንታ ምግኘት አለባቸዉ አሉ።ደግሞ በተቃራኒዉ ሶሪያን ማጥቃት የለብንም፤ ዩናይትድ ስቴትስን መጠገን ነዉ ያለብን ብለዉም ነበር።»

ፓን ኪሙን እንደ ሰዉ ካጀት፤ እንደ ዲፕሎማት ካንገት ለሶሪያ ጦርነት  አብነቱ  ሠላማዊ ድርድር ነዉ እንዳሉ፤ ለአደራዳሪነት ኮፊ አናንን፤ ላሕዳር ብራሒሚን፤ ስቴፋን ደ ሚስቱራን ሾመዉ በበቃኝ ሲያሰናብቱ ዓመታት አስቆጥረዉ እራሳቸዉም ከስልጣን ተሰናበቱ።ኦባማ፤ ጆን ኬሪ እና ተባባሪዎቻቸዉ የሶሪያን መሪ ለማጥፋት እንደፎከሩ በትራምፕ ተተኩ።

Syrien Armee nimmt Dumair ein
ምስል picture-alliance/Photoshot/A. Safarjalani

አል አሰድ ዛሬም በነበሩበት አሉ።ጦርነቱም ቀጠለ።ስምተኛ ዓመቱ።ጦርነቱ ከ110 ሺሕ በላይ ሰላማዊ ሕዝብ ፈጅቷል።12 ሚሊዮን ሕዝብ አንድም አሰድዷል ወይም አፈናቅሏል።ከሰባ ሺሕ በላይ የሶሪያ መንግሥት ወታደሮች፤ ከ80 ሺሕ የሚበልጡ የተለያዩ ታጣቂ ቡድናት ባልደረቦች፤ 50 ሺሕ የሚሆኑ የአሸባሪ ቡድን አባላት አልቀዋል።በሺሕ የሚቆጠሩ የሌሎች አረብ ሐገራት ተወላጆች፤ የኢራን፤ የሒዝቡላሕ፤ የሩሲያ፤ የቱርክ፤ የምዕራባዉያን ሐገራት ዜጎች ተገድለዋል።በቢሊዮን የሚገመት ሐብት ንብረት ወድሟል።

አሸናፊም ተሸናፊም የለም።ሠላምም እሩቅ ነዉ።ፓን ጊ ሙንን የተኩት አንቶኒዮ  ጉቴሬሽ  ልክ እንደ ቀዳሚያቸዉ ሁሉ ጦርነቱን ለማስቆም ከሰላማዊ ድርድር ሌላ መፍትሔ የለም ይሉ ገቡ።ባለፈዉ ሳምንትም ደገሙት።

                                 

«ለሶሪያዉ ጦርነት ወታደራዊ እርምጃ መፍትሔ አይሆንም።መፍትሔዉ ፖለቲካዊ ነዉ።ከፖለቲካዊ መፍትሔ ላይ የሚደረስበትን መንገድ እናዉቃለን።የፀጥታዉ ጥበቃ ምክር ቤት ዉሳኔ ነዉ።የዉሳኔዉ ቁጥር 22-54 ነዉ።ጄኔቭ ላይ በወጣዉ መግለጫ የተብራራዉ።አሁን ያለዉን ችግር ማስወገድ የምንችለዉ በሶሪያዎች መካከል ማለት በመንግሥት እና በተቃዋሚዎች መካከል በሚደረግ ድርድር ነዉ።»

ጉቴረሽ የሚሉትን  እስካሁን ገቢር ያደረገ አይደለም ለማድረግ የሞከረ ኃያል-ሐብታም ዓለም የለም።ያለዉ ጦርነት ነዉ።የዛሬ ዓምስት ዓመት ግድም የያኔዉን የአሜሪካ አስተዳደር ሲወቅሱ የነበሩት ወገኖች በጦርነቱ አንዱን ወገን ከመደገፍ አልፈዉ ሶሪያን በቀጥታ ማስደብደባቸዉ ነዉ እዉነቱ።ግንባር ቀደሙ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራም ናቸዉ።ምክንያታቸዉ የሶሪያ መንግሥት  በኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ዜጎቹን ገድሏል የሚል ነዉ።

አምና ሚያዚያ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ባወነጨፈዉ ሚሳዬል ሻሪያት በሚባለዉ ሥፍራ የሚገኘዉን የሶሪያ ዓየር ኃይል ሠፈር አዉድሞታል።የአሜሪካ ጦር ከተኮሳቸዉ ሐምሳ ስምንት ሚሳዬሎች ዒላማቸዉን የመቱት ጥቂት ቢሆኑም፤ ጥቃቱ የሶሪያ ዓየር ኃይልን የመዋጋት አቅም ክፉኛ መጉዳቱ አላጠያየቀም።

ፕሬዝደንት ትራምፕ በምርጫ ዘመቻቸዉ ወቅት የገቡትን ቃል አጥፈዉ ሶሪያን መደብደባቸዉ ለዓለም ይሆን ለአሜሪካ ፖለቲከኞች ለመነጋገሪያነት እንኳ የበቃ ርዕሥ ዓይደለም።ኬሚካዊ ጥቃቱ ዘንድሮም ተደገመ።ዶዉማ በተባለችዉ ከተማ አቅራቢያ ተተኮሰ በተባለዉ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ አርባ ሰዎች መገደላቸዉን የሶሪያ መንግሥት ተቃዋሚ ኃይላት አስታዉቀዋል።ኬሚካሉን የተኮሰዉ ወገን ማንነት በግልፅ አልታወቀም።

የዩናይትድ ስቴትስ፤ የብሪታንያ እና የፈረንሳይ መሪዎች ግን ወትሮም ከስልጣን እንዲወገድ ተቃዋሚዎቹን የሚያደራጁበትን  የፕሬዝደንት በሽር አልአሰድን ለመወንጀል አላመነቱም።እንደከሳሽ ወነጀሉ፤ እንደ ዳኛ ፈረዱ፤ እና እንደ ፖሊስ ቀጡ።ዘንድሮም ሚያዚያ ነዉ።

                          

«አሜሪካዉያን ወገኖቼ ሆይ፤ የዩናይትድ ስቴትስ ጦር ኃይል፤ ከሶሪያዉ አምባገነን ከበሽር አልሰድ ኬሚካዊ የጦር መሳሪያ ማምረቻ ጋር ግንኙነት ያላቸዉን ተቋማት ነጥሎ እንዲመታ ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት አዝዣለሁ።ከፈረንሳይ እና ከብሪታንያ ጦር ኃይል ጋር የተቀናጀ ዘመቻ በመደረግ ላይ ነዉ።ሁለቱንም እናመሰግናለን።ዛሬ ማታ ለእናንተ መንገር የፈለግሁት ይሕን እርምጃ ለምን እንደወሰድን ነዉ።ካንድ ዓመት በፊት አሰድ የገዛ የዋሕ ወገናቸዉን በኬሚካዊ መሳሪያ አጥቅተዋል።ዩናይትድ ስቴትስ በከፈተችዉ አፀፋ ጥቃት በ58 ሚሳዬሎች፤ከሶሪያን ዓየር ኃይል 20 በመቶዉን አዉድማለች።ባለፈዉ ቅዳሜ ደግሞ የአሰድ ሥርዓት በየዋሕ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ኬሚካዊ ጦር መሳሪያ ተኩሷል።ያሁኑ ጥቃት የተፈፀመዉ ዶዉማ ከተማ ላይ ነዉ።»

በሕዝብ የተመረጡት የሰወስቱ ሐገራት መሪዎች ለየጦራቸዉ የሰጡትን ትዕዛዝ ለየዝባቸዉ የተናገሩት  የሶሪያ ተቋማት መዉደም ከጀመሩ በኋላ ወይም በሚወድሙበት መሐል ነዉ።ጦርነትን በሌላ ጦርነት ማቆም እንደማይቻል የሚገነዘበዉ ሕዝብ የየመንግስቱን እርምጃ ባደባባይ ሰልፍ መቃወሙ አልቀረም።

የብሪታንያ ዜጎች መሪዎቻቸዉን እና ዉሳኔያቸዉን በአደባባይ ሰልፍ አወገዙ።

Karte Syrien kontrollierte Gebiete 15. April 2018 ENG

                          

«እንዲሕ አይነቱ ድብደባ ለሶሪያ ይጠቅማል ብዬ አላስብም።ተጨማሪ ሰዎች ለመግደል ተጨማሪ ቦምብ አስፈላጊ አይደለም።»

አሜሪካኖችም ቀጠሉ።«ሕገ ወጥ ነዉ።የጦር ወንጀል ነዉ።ኬሚካዊ ጦር መሳሪያዎች መኖራቸዉ ቢረጋገጥ እንኳ እንዲሕ አይነት ጥቃት እንዲፈፀም የሚያዝ ዓለም አቀፍ ሕግ የለም።የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ላይ ቀርቦ እዚያ ክርክር ሊደረግበት ይገባ ነበር።»

ሩሲያዎች የሶሪያ መንግስትን፤ አሜሪካ እና ተከታዮችዋ የመንግሥት ተቃዋሚዎች እና ሸማቂዎችን ደግፈዉ የሶሪያን ሕዝብ ሲያጨርሱ ግን የተባበሩት መንግስታት ድርጅትም፤ የተቀሩት የድርጅቱ አባል ሐገራትም ከዳር ቆመዉ ከማየት በስተቀር ያሉት፤ሊሉ የሚችሉት ነገርም በርግጥ አልነበረም።ያሁኑንም የሚሳዬል ጥቃት ከሩሲያ እና ከራሱ ከሶሪያ መንግሥት በስተቀር የተቃወመ  ካለ የአሜሪካ እና የብሪታንያ ሕዝብ ብቻ ነዉ።

ምዕራብ አዉሮጳ እንዳለ እና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት ሰወስቱ ሐገራት ሶሪያን መደብደባቸዉን ደግፈዉታል።የሰወስቱ ሐገራት ጦር ሶሪያን በአንድ መቶ አምስት ሚሳዬል ደብድቧል።የኬሚካል ማምረቻ ወይም ማከማቻ ነበሩ የተባሉ ሰወስት ተቋማት ወድመዋል።የሩሲያ ጦር አዛዦች እንዳስታቁት ከተተኮሱት ሚሳዬሎች 71ዱን የሶሪያ የሚሳዬል መከላከያ ጦር አክሽፎታል።

የዋሽግተን፤የለንደን እና የፓሪስ መሪዎች መርማሪም፤ ፈራጅም፤ ፍርድ አስፈጻሚም ሆነዉ የሚችሉትን ካደረጉ በኋላ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉዳዩን የሚያጣራ የባለሙያዎች ቡድን መላኩ ነዉ-ፌዝ የሚመስለዉ ግን የዓለም ፖለቲካዊ ሐቅ።

የምርመራዉ ዉጤት የሞስኮ-ዋሽግተኖችን ልዩነት ለማጥበብ፤ የሶሪያን ዉድመት ለማስቀረት የሚፈይደዉ ነገር መኖሩ ሲበዛ አጠያያቂ ነዉ።ዩናይትድ ስቴትስ እና ተባባሪዎችዋ ያደረሱት ድብደባም ስምተኛ ዓመቱን የያዘዉን ጦርነት ለማስዎም የፈየደዉ የለም።

 

ሠዓታት ለወሰደዉ ድብደባ አንዲት ዩናይትድ ስቴትስ ብቻ ከአንድ መቶ ሚሊዮን ዶላር በላይ አዉጥታለች።እርግጥ ነዉ ፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ከዚሕ ቀደም እንዳሉት ሐገራቸዉ ሶሪያን ለመደብደብ ይሁን የሶሪያ መንግሥትን ለማሰልጠን እና ለማስታጠቅ የምታወጣዉን ገንዘብ ሳዑዲ አረቢያን የመሳሰሉ የዓረብ ሐገራት መክፈላቸዉ የማይቀር ነዉ። የሳዑዲ አረቢያ ነገስታት የዋሽግተኖችን ትዕዛዝ ማክበራቸዉ እንደማይቀር የሐገሪቱ ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር አድል አል-ጀባር ባለፈዉ ማክሰኞ አረጋግጠዋል።

                                                     

« የገንዘብ መዋጮን በተመለከተ፤ ሳዑዲ አረቢያ ሸክሙን ለመጋራት ሁልጊዜም ዝግጁ ነች።በ1990 የተደረገዉን (የፋርስ ባሕረ ሰላጤ) ጦርነትን ብታስታዉሶ፤ ኩዌትን ነፃ ለማዉጣት ሳዑዲ አረቢያ የዩናይትድ ስቴትስ ሙሉ ተባባሪ ነበረች።»

Syrien Luftabwehrraketen abgeschossen in Damaskus
ምስል picture-alliance/dpa/H. Amma

እዉነት ነዉ። በአሜሪካ እና ተባባሪዎችዋ ወረራ፤ በሳዑዲ አረቢያ እና በተሻራኪዎችዋ  ድጋፍ  ኢራቅ ፈርሳለች።ሊቢያ ከሐብታም ሐገርነት ወደ ሽፍቶች መፈንጪያነት፤ ከመሸጋገሪያነት ወደ ስደተኞች ማለቂያነት ተበትናለች።ተረኛዋ ሶሪያ ናት።ከዘር፤-አረቦችን፤ ግሪኮችን፤አርመኖችን፤አሲሪያዎችን፤ ሲርካሲያዎችን፤ ማንዲኖችን፤ ቱርኮችን፤ ኩርዶችን  አሰባጥራ የያዘችዉ፤ ከኃይማኖት ሙስሊሞችን-ክርስቲያኖችን፤ያዚዶችን  አይሁድን የምታኖረዉ የስልጣኔ ቀንዲል፤ ጥንታዊ፤ ዉብ ምድር የመቶ ሺዎች መርገፋ፤የጦር መሳሪያ መፈተሺያ ሆናለች።መጨረሻዋ ነዉ ናፋቂዉ።ነጋሽ መሐመድ ነኝ ቸር ያሰማን።

ነጋሽ መሐመድ 

ሸዋዬ ለገሰ