1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ የካቲት 25 ቀን 2011

ሰኞ፣ የካቲት 25 2011

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በሳምንቱ መጨ በተለያዩ ሀገራት ድሎች አስመዝግበዋል። የአፍሪካ የብስክሌት ሻምፒዮና በመጪው መጋቢት ወር በባህር ዳር ከተማ እንደሚደረግ ባለፈው ቅዳሜ ተገልጿል። በሳምንቱ መጨረሻ በተከናወኑ የቡንደስሊጋ የእግር ኳስ ግጥሚያዎች ባየር ሙኒክ ድል ሲቀናው ቦሪሲያ ዶርቱሙንድ ተሸንፏል።

https://p.dw.com/p/3EQv2
USA 112. Millrose Games | Yomif Kejelcha aus Äthiopien
ምስል Reuters/USA TODAY Sports/K. Lee

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ 25.06.2011

በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በተሳተፉባቸው ውድድሮች ድሎችን ያስመዘገቡበት ብቻ ሳይሆን የዓለም ክብረ ወሰን የሰባበሩበት ሆኗል። ኢትዮጵያዊው ዮሚፍ ቀጀልቻ ትላንት በአሜሪካ ቦስተን ማሳቹስቴትስ ውስጥ በተደረገ የሩጫ ውድድር በአንድ ማይል ርቀት አዲስ የዓለም ክብረ ወሰን አስመዝግቧል። ዮሚፍ የትላንቱን የአንድ ማይል ሩጫ ያሸነፈው በሶስት ደቂቃ፣ ከ47 ሰከንድ፣ ከ04 ማይክሮ ሰከንድ በመግባት ነበር። ኢትዮጵያዊው አትሌት በትላንትናው ድሉ ላለፉት 22 ዓመታት በሞሮካዊው ሄካም ኤል ጉራዥ ተይዞ የነበረውን የሶስት ደቂቃ ከ48 ሰከንድ የ45 ማይክሮ ሰንድ የክብረ ወሰን ሰዓትን አንኮታኩቷል።  

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ትላንት በጃፓን ቶኪዮ የተደረገውን የማራቶን ውድድር በሁለቱም ጾታ በማሸነፍም የበላይነታቸውን አስመስክረዋል። በሴቶች ሩቲ አጋ ድልን ስትጎናጸፍ እና በወንዶች ብርሃኑ ለገሰ አሸንፏል። በሴቶቹ ምድብ የተወዳደሩት ሄለን ቶላ እና ሹሬ ደምሴ ሁለተኛ እና ሶስተኛ በመውጣት የኢትዮጵያውያንን ድል ከፍ አድርገውታል። 

ባለፈው ዓመት በተካሄደው የቶኪዮ ማራቶን በሁለተኛነት የጨረሰችው ሩቲ አጋ ዘንድሮ ድል መቀዳጀት ችላለች። ሩቲ የማራቶን ውድድሩን ያነፈችው በሁለት ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ40 ሰከንድ ነው። በአሸናፊዋ የሀገሯ ልጅ በ21 ሰከንዶች ብቻ የተበለጠችው ሄለን ቶላ ሁለተኛ ወጥታለች። ሌላኛዋ ኢትዮጵያዊት ሹሬ ደምሴ በሁለት ሰዓት ከ21 ደቂቃ ከ05 ሰከንድ በመግባት ኢትዮጵያውያኑ ራጮች በማራቶን ውድድሩ ላይ ሙሉ በሙሉ እንዲነግሱ አድርጋለች። በዳቱ ሂርጳ እና አባበል የሻነህም አምስተኛ እና ስድስተኛ በመውጣት በርቀቱ የኢትዮጵያውያንን ፍጹም የበላይነት አሳይተዋል።  ኢትዮጵያውያን ሴት አትሌቶች ካለፉት ስምንት ተመሳሳይ ውድድሮች በስድስቱ በማሸነፍም ታሪክ ሰርተዋል። 

በወንዶቹ ምድብ የተወዳደረው ኢትዮጵያዊው ብርሃኑ ለገሰም የሴቶቹን ድል ደግሟል። ሁለት ኬንያውያን አትሌቶችን ያስከተለው ብርሃኑ የማራቶን ውድድሩን በሁለት ሰዓት ከአራት ደቂቃ ከ48 ሰከንድ በማጠናቀቅ ነው ያሸነፈው። ያለፈው ዓመት የውድድሩ አሸናፊ የነበረው ኬንያዊው ዲክሰን ቹምባ ለሶስት ተከታታይ ዓመታት ድል ለማስመዝገብ የነበረው ዕቅድ በብርሃኑ ተጨናግፎበታል። ቹምባ የሀገሩን ልጅ ቤዳን ካሮኪን ተከትሎ ውድድሩን በሶስተኛነት ጨርሷል።

ወደ ብስክሌት ስፖርት ዜና ስንሻገር 14ኛው የአፍሪካ ብስክሌት ሻምፒዮን ውድድር በባሕር ዳር እንደሚካሄድ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን አስታውቋል። ውድድሩ ከመጋቢት 5 እስከ 10 ቀን 2011 ዓ. ም. የሚካሄድ ሲሆን ከ35 አገሮች የሚውጣጡ 400 ብስክሌት ተወዳዳሪዎች ይሳተፋሉ። ከተወዳዳሪዎቹ ውስጥ 40ዎቹ ኢትዮጵያውያን ናቸው። 

Äthiopien - Bahir Dar wird Austragungsort des 14th African Cycling Championship
ምስል DW/A. Mekonnen

ውድድሩን አስመልከቶ የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌደሬሽን እና የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን በባሕር ዳር ባለፈው ቅዳሜ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ አህጉር አቀፉ የብስክሌት ውድድር በኢትዮጵያ የሚካሄደው ለመጀመሪያ ጊዜ መሆኑን የተናገሩት የፌደሬሽኑ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ወርቁ ገዳ ውድድሩን እንዲያካሂዱ በአገሪቱ ለሚገኙ ታላላቅ ከተሞች ጥሪ የተደረገላቸው ቢሆንም ከመቀሌና ባህር ዳር ከተሞች ውጭ ውድድሩን ለማድረግ እንደማይችሉ በማሳወቃቸው የወጣውን መስፈርት አሟልታ በመገኘቷ ባሕር ዳር መመረጧን አስረድተዋል፡፡

የኤርትራ ብሔራዊ ብስክሌት ፌደሬሽን አንድ አለም አቀፍ ስልጠና የወሰደ የውድድር አስተባባሪ እና ሌላ የፎቶ ፊኒሽ ባለሙያ በነፃ እንደሚልክ ያስታወቁት አቶ ወርቁ እነዚህን ባለሙያዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ አወዳድሮ ለማምጣት ቢሞከር ኖሮ ለእንዳንዳቸው እስከ 450 ዩሮ ያስወጣ ነበርም ብለዋል፡፡

በውድድሩ የሰዓት ሙከራ፣ የሚክስድ ሪሌይ እና የዙር ውድድሮች የሚኖሩ ሲሆን ውድድሮቹ ከ50 ኪሎሜትር  እስከ 180 ኪሎሜትር እንደሚሸፍኑ ነው አቶ ወርቁ የተናገሩት፡፡ በውድድሩ በግላቸው ሚኒማ የሚያሻሽሉ የወርቅ ሜዳሊያ ተሸላሚ አትሌቶች ለቶኪዮ 2020 ኦሎምፒክ በቀጥታ አላፊ እንደሚሆንም አስረድተዋል፡፡

የአማራ ክልል ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ባዘዘው ጫኔ በበኩላቸው ለውድድሩ ከሚያስፈልገው 7 ሚሊዮን ብር ውስጥ የአማራ ብሔራዊ ክልል መንግስት 3 ሚሊዮን ብር መመደቡን ተናግረዋል። ውድድሩ ለመጀመሪያ ጊዜ በአገራችን በተለይም በባህር ዳር መካሄዱ እና የኤርትራ ብሔራዊ የብስክሌት ቡድን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ መወዳደሩ ለየት እንደሚያደርገው ገልጸዋል። 


ሃይማኖት ጥሩነህ/ አለምነው መኮንን
ተስፋለም ወልደየስ