1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ስፖርት፤ ታኅሣሥ 16 ቀን፣ 2010 ዓ.ም.

ሰኞ፣ ታኅሣሥ 16 2010

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በስፔን ፖሊስ የምርመራ ክስ ተከፈተባቸው። ፖሊስ ምርመራ የጀመረው «የጥላቻ ጀርም» ሲል የፈረጀው የካታሎንያ የመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔን ደግፈዋል በሚል ነው። እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው «ኤል ክላሲኮ» ሪያል ማድሪድ 3 ለ0 ቢሸነፍም፤ አሰልጣኙ ዚነዲን ዚዳን «ደጋፊዎች ልትኮሩ ይገባል» ብለዋል።

https://p.dw.com/p/2pw1R
	
Spanien Real Madrid vs FC Barcelona
ምስል picture-alliance/AP Photo/F. Seco

ሣምንታዊ የስፖርት ዘገባ

የማንቸስተር ሲቲው አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በስፔን ፖሊስ የምርመራ ክስ ተከፈተባቸው። ፖሊስ አሠልጣኙ ላይ ምርመራ የጀመረው «የጥላቻ ጀርም» ሲል የፈረጀው የካታሎንያ የመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔን ደግፈዋል በሚል ነው። አሠልጣኙ «እስኪ የሚኾነውን እናያለን» ብለዋል። እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ በነበረው የሪያል ማድሪድ ባርሴሎና «ኤል ክላሲኮ» ፍልሚያ ሪያል ማድሪድ 3 ለ0 ቢሸነፍም፤ አሰልጣኙ ዚነዲን ዚዳን «ደጋፊዎች ልትኮሩ ይገባል» ብለዋል። በሜዳ ቴኒስ የዓለማችን ቊጥር አንድ ኮከብ ተጨዋች ሴሬና ዊሊያምስ ቅዳሜ አቡዳቢ ውስጥ በሙባደላ የዓለም ቴኒስ ሻምፒዮን እንደምትወዳደር ይፋ አድርጋለች። ሴሬና ልጅ ከወለደች ገና አራት ወርም አላለፋት። 

ስፔናዊው የማንቸስተር ሲቲ አሰልጫኝ ፔፕ ጓርዲዮላ በስፔን ፖሊስ ምርመራ ተከፈተባቸው። የስፔን ፖሊስ የቀድሞው የባርሴሎና እና የባየር ሙይንሽን አሰልጣኝ ላይ ምርመራ የከፈተው የካታሎንያ ግዛት የምርጫ ውጤትን አወድሰው በመናገራቸው ነው። ሐሙስ እለት በተከናወነው ድንገተኛ ምርጫ ከስፔን መገንጠል የሚፈልጉት የካታሎንያ ተገንጣዮች አብላጫ ወንበር ዳግም አግኝተዋል።

ትውልዳቸው ከካታሎንያ የኾነው አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ፦ «ካታሎንያውያን የሚፈልጉትን ትናንት አሳይተዋል። እናም አኹን ቀሪው ስፔን ዕውነታውን ሊረዳ ይገባል» ሲሉ መገንጠል ደጋፊዎች ባካሄዱት ሰልፍ ላይ ተናግረዋል።  የስፔን ፖሊስ የካታሎንያ መራጮች ሕገወጥ የመገንጠል ሕዝበ-ውሳኔ እንዲያደርጉ ገፋፍተዋል ያላቸውን አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላን ጨምሮ ሌሎች ስም ያላቸው ዜጎች ላይ ምርመራ መክፈቱን አስታውቋል። 

የካታሎንያ ምርጫ የተጠራው በስፔን ጠቅላይ ሚንሥትር ማሪያኖ ራሆይ ነበር። ጠቅላይ ሚንሥትሩ ምርጫውን የጠሩት የግዛቲቱ መንግሥት ጥቅምት ወር ላይ ከስፔን መገንጠሉን ማወጁን ተከትሎ በሀገሪቱ የፖለቲካ ትኩሳቱ ለሣምንታት በመጨመሩ ነበር ።  በወቅቱ የስፔን መንግሥት የካታሎንያ የመገንጠል ውሳኔን ሕገ-መንግሥቱን የጣሰ በሚል በርካታ ሕግ አውጪዎችን እና ፖለቲከኞችን እስር ቤት መወርወሩ አይዘነጋም።

Fußball Gestik Trainer Pep Guardiola
ምስል picture-alliance/empics/A. Devlin

አሠልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ፖሊስ ምርመራ ከከፈተባቸው ሰዎች አንዱ መኾናቸው ያሰጋቸው እንደኾን ተጠይቀው ሲመልሱ፦ «እስኪ የሚኾነውን እናያለን» ብለዋል። በሰኔ ወር መግቢያ ላይ ፔፕ ጓርዲዮላ ከሀገር ከኮበለሉት የካታሎንያ መሪ ካርሌ ፑጅሞን ጋር በመኾን ባርሴሎና ከተማ ውስጥ በተደረገው ሰልፍ የካታሎንያ መገንጠል ደጋፊ መኾናቸውን ገልጠው ነበር።

ፔፕ ጓርዲዮላ የተሳተፉበት አይነት ሰልፎችን በአጠቃላይ የስፔን ፖሊስ «በግዛቲቱ ላይ ያነጣጠረ የጥላቻ ጀርም» ሲል ፈርጆታል። የስፔን ፖሊስ በአሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ ላይ ውጤቱን ይመራል ተብሏል። ምርመራውን  እንዳጠናቀቀ ወደ ሀገሪቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ፓብሎ ሊየሬን

ከዛው ከስፔን ሳንወጣ የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት ፍሎሬንቲኖ ፔሬዝ ምንም እንኳን ቡድናቸው በባርሴሎና ከትናንት በስትያ 3 ለ 0 ቢረታም ደጋፊዎች ሊኮሩ ይገባል ብለዋል። በስፔን ላሊጋ እጅግ በጉጉት ሲጠበቅ የቆየው የባርሴሎና እና የሪያል ማድሪድ የቅዳሜ እለት የ«ኤል ክላሲኮ» ፍልሚያ 80.000 ተመልካቾች ፊት በባርሴሎና ድል ነው የተቋጨው። እንዲያም ኾኖ የሪያል ማድሪድ ፕሬዚዳንት የቡድናቸውን ደጋፊዎች ሲያጽናኑ ሪያል ማድሪድ የተጎናጸፋቸው ድሎችን ዘርዝረዋል። በላሊጋው ዘንድሮ ከመሪው ባርሴሎና በ14 ነጥብ የተበለጠው ሪያል ማድሪድ ባለፈው የጨዋታ ዘመን የሻምፒዮንስ ሊግ እና የላሊጋ ዋንጫዎችን ማንሳት ችሎ ነበር። ከዚያም በኋላ ሪያል ማድሪድ የቡድኖች የዓለም ዋንጫን፤ የአውሮጳ እና የስፔን ሱፐር ካፕ ዋንጫዎችን በመጨመር ኃያልነቱን አስመስክሯል። ቅዳሜ እለት ግን ሊዮኔል ሜሲ እና ጓደኞቹ ጉድ አድርገውታል።

በቅዳሜው የኤል ክላሲኮ ፍልሚያ 80.000 ተመልካቾች በታደሙበት የሣንቲያጎ በርናባው ስታዲየም ሉዊስ ሱዋሬዝ የመጀመሪያዋን ግብ ያስቆጠረው በ54ኛው ደቂቃ ላይ ነው። የእለቱ ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ በ64ኛው ደቂቃ በፍጹም ቅጣት ምት ኹለተኛውን ግብ ከመረብ አሳርፏል። የማሳረጊያዋን ሦስተኛ ግብ ያመቻቸው ይኸው የኳስ ጠቢቡ ሊዮኔል ሜሲ ነው። መደበኛው የጨዋታ ጊዜ ተጠናቆ በጭማሪው 3ኛ ደቂቃ ላይ ሦስተኛዋ ግብ ያስቆጠረው አሌክሲስ ቪዳል ነው።

የሪያል ማድሪዱ አሠልጣኝ የ45 ዓመቱ ፈረንሣዊ ዚነዲን ዚዳን የቅዳሜውን ሽንፈት አስመልክቶ በእለቱ ሲናገር፦ «ነገ አናት አናቴን ነው የሚሉኝ። ያ ኳስ ነው እንዴት እንደማስብ እና ምን እንደማደርግ ግን የሚቀየር አይደለም» ብሏል። «አሠልጣኙ እኔ ነኝ፤ እናም እዚህ እስካለኹ ድረስ በዚህ መልኩ እቀጥላለሁ።» ያለው ዚዳን «የመጀመሪያው ግብ የተቆጠረብን በራሳችን ስህተት ነው፤ እናም ተጨዋቹ በቀይ መውጣቱ የጨዋታውን ውስብስብነት ሙሉ ለሙሉ ቀይሮታል» ሲል አክሏል። ዚነዲን ዚዳን ከኹለት ዓመት በፊት ሪያል ማድሪድን በአሠልጣኝነት ከተረከበበት ጊዜ አንስቶ በዋነኛ ተቀናቃኙ ባርሴሎና ከትናንት በስትያ 3 ለ0 የደረሰበት ሽንፈት ከባዱ ነው።

Spanien Madrid CF vs FC Barcelona | Messi
ምስል Getty Images/AFP/O. del Pozo

ከሪያል ማድሪድ ውጪ አትሌቲኮ ማድሪድን እና ቫለንሺያን ያደባየው ባርሴሎና ላ ሊጋውን በ9 ነጥብ ይመራል። ሪያል ማድሪድ በ31 ነጥብ ወደ አራተኛ ደረጃ ዝቅ ብሏል። ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አትሌቲኮ ማድሪድ 36 ነጥብ አለው። ቫለንሺያ 34 ነጥብ ይዞ በሦስተኛነት ይከተላል።

ቡንደስ ሊጋ

በቡንደስሊጋው ላይፕሲሽ እና ባየር ሌቨርኩሰን ነጥብ መጣላቸው ለቦሩስያ ዶርትሙንድ መልካም አጋጣሚ ነው የኾነለት። ቅዳሜ እለት ሆፈንሃይምን 2 ለ1 ያሸነፈው ቦሩስያ ዶርትሙንድ  ላይፕሲሽ እና ባየር ሌቨርኩሰንን በተመሳሳይ 28 ነጥብ ኾኖም በግብ በልጦ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። ባየር ሌቨርኩሰን ትናንት ከሐኖቨር ጋር ባደረገው ጨዋታ 4 ለ 4 በመውጣት ነጥብ ተጋርቷል። ላይፕሲሽ አንድ ተጨዋቹ በቀይ በተሰናበተበት ሔርታ ቤርሊን ነበር ትናንት 3 ለ2 ድል የተደረገው። 30 ነጥብ ይዞ ኹለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሻልከ ቅዳሜ እለት ከአይንትራኅት ፍርናክፉርት ጋር ኹለት እኩል አቻ ወጥቷል።  አይንትራኅት ፍርናክፉርት በ26 ነጥብ ስምንተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ፕሬሚየር ሊግ

በእንግሊዝ ፕሬሚየር ሊግ ማንቸስተር ዩናይትድ ከበርንሌይ፤ ሊቨርፑል ከስዋንሲ ሲቲ እንዲሁም  ቸልሲ ከብሪንግቶን ጋር ነገ የሚያደርጉት ጨዋታ ይጠበቃል። 42 ነጥብ ያለው ማንቸስተር ዩናይትድ የነገውን ጨዋታ ቢያሸንፍ እንኳ መሪው ማንቸስተር ሲቲ ላይ ለመድረስ ግን ገና ብዙ ይቀረዋል። ማንቸስተር ሲቲ በ55 ነጥብ ለብቻው በመሪነት እየገሰገሰ ነው። 35 ነጥብ ያለው ሊቨርፑል በቸልሲ በ4 ነጥብ ተበልጦ አራተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል። በ13 ነጥቡ ብቻ ተወስኖ የደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ 20 ላይ የሚገኘው ስዋንሲ ሲቲን ሊቨርፑል በቀላለሉ ያሸንፋል ተብሎ ይጠበቃል። ቸልሲም ቢኾን በ12ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ብሪንግቶንን ማሸነፍ የሚከብደው አይመስልም። ስለዚህ የደረጃ ሰንጠረዡ ለውጥ ላይኖረው ይችላል።

የዝውውር ዜና

የእንግሊዝ ፕሬሚየ ር ሊግ ተጨዋቾች ዝውውርን እናስቀድም። ሊቨርፑል  የ27 ዓመቱ የፓሪስ ሳን ጀርሜይን ግብ ጠባቂ ኬቪን ትራፕን በሚቀጥሉት ጥቂት ሳምንታት ለማስፈረም ዕድል መስጠቱን ሜትሮ ዘግቧል። ቶትንሀም ኹለት ተጨዋቾችን በቅርቡ ሊያስፈርም ተሰናድቷል። የኤቨርተኑ አማካዩ የ24 ዓመቱ ሮስ በርክሌይ እና የ22 ዓመቱ የማንቸስተር ዩናይትድ የኋላ ተመላላሽ ሉክ ሻው ናቸው የቶትናም ዐይን ውስጥ የገቡት እንደ ሰንደይ ኤክስፕረስ ዘገባ።

DFB Pokal Borussia Mönchengladbach - Bayer 04 Leverkusen
ምስል imago/Jan Huebner

ማንቸስተር ዩናይትድ ለአሰልጣኙ ሆዜ ሞሪኝሆ አዲስ ውል ሳያስፈርማቸው ሒደቱን ማራዘሙን ሚረር አትቷል። የ30 ዓመቱ ፈረንሣዊ የአርሰናል አጥቂ  ኦሊቨር ጂሩ መጻዒ ዕድል ላይ ለመምከር ወኪሉ ለንደን ውስጥ እንደሚገኙም ይኸው ጋዜጣ አስነብቧል። የማንቸስተር ሲቲ አሰልጣኝ ፔፕ ጓርዲዮላ የ24 ዓመቱ ወጣት አማካይ ፍሬድ ቀልባቸውን ስቦታል።  አሠልጣኙ የሻካታር ዶኒዬትስኩ አማካይ ፍሬድን በበጋ ወራት የተጨዋቾች ዝውውር ወደ ማንቸስተር ሲቲ ለማስመጣት ማቀዳቸውን ሜይል ኦን ሰንደይ ጽፏል።

በጀርመን ቡንደስ ሊጋ የተጨዋቾች ዝውውር ዜና ደግሞ የብሔራዊ ቡድኑ ተሰላፊው ዛንድሮ ቫግነር የባየር ሙይንሽን ቡድንን ተቀላቅሏል። የሆፈንሀይሙ አጥቂ ዛንድሮ ቫግነር ወደ ልጅነት ቡድኑ የተመለሰው በ14.25 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መኾኑ ተዘግቧል።  ዛንድሮ ወደ ባየርን ቡድን መመለሱን አስመልክቶ ሲናገር፦ «ወደ ቤቴ ተመልሻለሁ» ብሏል። የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አጥቂው ዛንድሮ በሆፈንሀይም የኹለት ዓመት ቆይታው 18 ግቦችን ከመረብ ማሳረፍ ችሏል። ዛንድሮ የቀድሞ ቡድኑ ሆፈንሀይም ወደ አውሮጳ ሊግ ግጥሚያ እንዲያልፍም ቊልፍ ሚና የተጫወተ ወሳኝ አጥቂ ነው።

ሌላኛው አንጋፋ የብሔራዊ ቡድኑ ተጨዋች ማሪዮ ጎሜዝም ወደ ሽቱትጋርት ቡድን ተመልሷል። የማሪዮ ጎሜዝ ክፍያ ግን ከዛንድሮ ቫግነር በአምስት እጥፍ ያነሰ ነው። ለማሪዮ ጎሜዝ የተከፈለው 3 ሚሊዮን ዩሮ ግድም መኾኑ ተዘግቧል። ማሪዮ ጎሜዝ ወደ ሽቱትጋርት ሲመለስ በውሰት ሽቱትጋርት የቆየው የ19 ዓመቱ አጥቂ ጆሲፕ ብሬክሎ ውል ደግሞ ተቋርጧል። ጆሲፕ ወደ ቮልፍስቡርግ ይመለሳል።

ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ (IOC) ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር ተጠቅመዋል ያላቸው 11 የሩስያ አትሌቶች በኦሎምፒክ ውድድሮች እንዳይሳተፉ የእድሜ ልክ ገደብ ቅጣት ሰሞኑን ጥሎባቸዋል። ቅጣቱ የተላለፈው የዛሬ ሦስት ዓመት በሶቺ ኦሎምፒክ ወቅት ለተፈጸመ ጥፋት ነው። በወቅቱ በሩስያ መንግሥት ዕውቅና በርካታ አትሌቶች በተቀናጀ መልኩ አበረታች ንጥረ-ነገር ይወስዱ እንደነበር ተዘግቦ ነበር።

Tennis-Spielerin Serena Williams  2017 Australian Open in Melbourne
ምስል Imago/Schreyer

እንደ ዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ጠባይ ተመልካች መምሪያ ከኾነ አትሌቶቹ ቀደም ሲል ያገኟቸው የሜዳሊያ ሽልማቶች የተገፈፈባቸው ሲኾን ከእንግዲህ በኦሎምፒክ ውድሮች አይሳተፉም። እገዳው ከተጣለባቸው አትሌቶች መካከል የኹለት ጊዜያት የኦሎምፒክ ሜዳሊያ ያገኘው ፈጣን የበረዶ ላይ ተንሸራታቹ ኢቫን ስኮብሬቭ እና በሶቺ ኦሎምፒክ የብር ሜዳሊያ ተሸላሚዋ ታቲያና ኢቫኖቫ ይገኙበታል።

ውሳኔው የተላለፈው ከጸረ ኃይል ሰጪ ንጥረነገር ኩባንያ ምርመራ እና ከዓለም አቀፉ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ማረጋገጪያ በኋላ ነው። የሩስያ አትሌቶች በፒዮንግያንጉ የኦሎምፒክ ጨዋታዎች በሩስያ ባንዲራ ተጠልለው መሰለፍ አይችሉም ተብሏል። ኾኖም የኃይል ሰጪ ንጥረነገር ንክኪ የሌለባቸው አትሌቶች በኦሎምፒኩ መወዳደር ከፈለጉ በግላቸው መሳተፍ ይችላሉ። የፒዮንግያንጉ የ2018 የክረምት ኦሎምፒክ ጨዋታዎች ከየካቲት 2 እስከ የካቲት 18 ድረስ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ ይከናወናል።

የሜዳ ቴኒስ

ልጅ ከወለደች ገና 4 ወራትም ያልሞላት አሜሪካዊቷ የሜዳ ቴኒስ ኮከብ ሴሬና ዊሊያምስ የፊታችን ቅዳሜ ለዓለም ቴኒስ ሻምፒዮን ትጋጠማለች። የ36 ዓመቷ ሴሬና  ከ5 ቀናት በኋላ አቡዳቢ ውስጥ የምትገጥመው ሌላኛዋ የዓለማችን ምርጥ የሜዳ ቴኒስ ተጨዋች ዬሌና ሶስታፔንኮ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ