1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳን፤ ዳርፉርና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች

ሰኞ፣ ሰኔ 11 1999

ሱዳን ቅይጡን ሰላም አስከባሪ ለመቀበል ከተስማማች በኋላ በትናንትዉ ዕለት የተመድ የፀጥታዉ ምክር ቤት ልዑካን ካርቱም ገብተዉ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋ ተነጋግረዋል።

https://p.dw.com/p/E0av
የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኤል-በሺር
የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኤል-በሺርምስል AP
በአንፃሩ የሱዳን መንግስት በዳርፉር የጦር ወንጀል የተጠረጠሩ ሁለት ዜጎቹን በዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት ሳይሆን በአገሪቱ ፍርድ ቤት ይዳኛሉ ማለቱ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾችን ዉግዘት አስከትሏል።
የዓለም ዓቀፉ የወንጀል ችሎት የሱዳን መንግስት በዳርፉር የጦር ወንጀለኝነት የተጠረጠሩ አንዳለስልጣኑንና የሚሊሺያዎቹ መሪ የሆኑትን ግለሰብ እንዲያስረክብ ያቀረበዉ ጥያቄ ቀና ምላሽ አላገኘም። የሱዳን መንግስት አቋም ሰዉ በአገር ዉስጥ ፍርድ ቤት ጉዳያቸዉ ይታያል የሚል ነዉ። ይህን ደግሞ ካለፈዉ ተመክሮ በመነሳት Human Rights Watch አልተቀበለዉም። ሱዳን አሳልፋ ዜጎቿን ለዓለም አቀፉ የወንጀል ችሎት የማታቀርብ ከሆነ ተጠርጣሪዎቹ በአገር ዉስጥ ችሎት ቢዳኙ አያስኬድም ወይ? በርሊን የሚገኘዉ የHuman Rights Watch ፅህፈት ቤት ዳይሬክተር ማሬና ሆይቫገንን ምላሽ አላቸዉ፤
«የሱዳን መንግስት ባለፈዉ ጊዜ በዳርፉር የተፈፀሙ ወንጀሎችን ራሴ አጣራለሁ ብሏላል። ሆኖም ተከታትለን የደረስንበት እዉነታ ያሳየን ምንም ዓይነት ተያያዥ ጉዳይ ባለፉት ዓመታት በሱዳን መንግስት እንዳልተዳኘ ነዉ። የፍርድ አጣሪ ኮሚቴ አቋቋሙ፤ ያም ከአንድ መቶ በላይ ጉዳዮችን አወጣ ተባለ። ከዚያ መካከል አስሩ ብቻ ነዉ የታየዉ። በተጨማሪም ኮሚቴዉ ያካሄደዉ ምርመራ አንዱም ጉዳይ ፍርድ እንዲሰጥበት አላደረገም። የሱዳንመንግስት የራሱን ሃላፊነት እንኳን መጠበቅ የሚችል አይደለም። የዳርፉርን ወንጀል በተመለከተ ፍርድ እንደሚሰጥ ተናግሮ ነበር ያንን የሚያሳይ ተጨባጭ መረጃ አላየንም።»
የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች በተደጋጋሚ ይህን መሰሉ የሱዳን መንግስት አቋምና አካሄድ ሲያወግዙ ቆይተዋል። ድርጊቱንማዉገዝና እርምጃዉን አለመደገፍ ግን ያሳየዉ እርምት የለም። የአሁኑ Human Rights Watch ዉግዘት ሊያስከትል የሚችለዉ ጫና ይኖር ይሆን?
«የሱዳን መንግስት የራሱን ግዴታ መወጣት አለበት የሚል እምነት አለን። የዓለም ዓቀፍ የወንጀል ችሎት ምርመራ አንፈልግም ሲሉ ጉዳዩን በራሳችን ችሎት እንዳኛለን ነዉ ያሉት። ያንን ደግሞ የማድረግ ግዴታ አለባቸዉ። ይህን የሚያረጋግጥ አሳማኝ መረጃ ግን አላየንም። በዚያ ላይ በካርቱም የዳርፉር ልዩ ችሎት ባለፈዉ ዓመት ካከናወነዉ ይልቅ በዚህ ዓመት ከሰራዉ እጅግ ያነሰ ነዉ። ስለዚህ ሃላፊነታቸዉን መወጣት አለባቸዉ ያንን እያየን ባለመሆኑም ዓለም ዓቀፉ ህብረተሰብ እየተከታተላቸዉ መሆኑን እንዲያዉቁ እንፈልጋለን።
ሰሞኑን የሱዳን መንግስት ከረዥም ጊዜያት የዲፕሎማሲ ጥረት በኋላ ወደዳርፉር ቅይጡ የሰላም አስከባሪ ኃይል እንዲገባ መስማማቱ ተነግሯል። በጥያቄ የሚታየዉ ይህን መሰሉ የካርቱምመንግስት አቋም ምናልባት የዓለምን ትኩረት ከዳርፉር የጥር ወንጀል በተገናኘ ከተከሰሱት ወገኖችና በዚህ ሳቢያ ከሚከተለዉ ዓለም ዓቀፍ ግፊት ለማዞር ነዉ የሚሉ ወገኖች አሉ። ማሬነ ሆይቫገን ደግሞ ይህን ይላሉ፣
«የሱዳም መንግስት የተመድንና የአፍሪቃ ህብረትን ቅይጥ ጦር የመቀበሉ ነገር ከልብ ያመነበት ነዉ ብለን እናደርጋለን። ሆኖም አሁንም የሚሏት ነገር አለች፤ ያ ማለት የአፍሪቃ ህብረት አፍሪቃዊ ወታደሮች ብቻ እንዲሰማሩ የሚለዉ ዓይነት ሃሳብ። ግን እነዚህን ወታደሮች የአፍሪቃ ህብረት ከየት አምጥቶ ማሟላት ይችላል? እስኪ ቆየት ብለን የሚቀጥለዉን እንይ። ባለፈዉ ጊዜ ቃል ገብተዉ ያልፈፀሙት ተግባር ለዉ። አሁንም ቢሆን ተስፋ አንቆርጥም ሃላፊነታቸዉን ይወጣሉ ብለን እናስባለን።»
የፀጥታዉ ምክር ቤት አምባሳደሮች ወደካርቱም ከመጓዛቸዉ በፊት አዲስ አበባ ላይ ከአፍሪቃ ህብረት ባለስልጣናት ጋ ተገናኝተዉ የሱዳን መንግስት ስምምነትን አረጋግጠዉላቸዋል። ትናንት ካርቱም ሲደርሱም ከሚመለከታቸዉ ባለስልጣናት ጋ ከተነጋገሩ በኋላ ወደጋና አቅንተዋል። ልዑካኑ ጋና ላይ እንደተናገሩት ከሱዳን መንግስት ወገን የሚያበራታ ተስፋ አለ።