1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሱዳንና የቀጠለው ተቃውሞ፣

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 10 2004

ከአንድ ዓመት በፊት፤ በሰሜን አፍሪቃ የለውጥ እንቅሥቃሴ ከመቀጣጠሉ በፊት፤ በ 1964 እና በ1985 ዓ ም፤ ሱዳናውያን፤ «ወታደራዊ አገዛዞችን ያፈናቀለ፣ አኩሪ የህዝብ የተቃውሞ ታሪክ አለን!» በማለት ይኩራራሉ። በተጠቀሱት ዓመታት ፣ በተከሠቱ

https://p.dw.com/p/15Z8C
ምስል Mohammed Fiat

የአገዛዝ ለውጦችም ፣ ተማሪዎች ወሳኝ ሚና መጫወታቸው ነው የሚነገርላቸው። በሱዳን ፤ በተለይም በመዲናይቱ በካርቱም፣ ሰኔ 9 ቀን 2004 ፣ በመባልእት ዋጋ መናር፣ በአጠቃላይ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የተጀመረው የተቃውሞ ሰልፍ ፣ ሳይቋረጥ የቀጠለ ሲሆን፣የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም ብርቱ የኃይል እርምጃ ከመውሰድ እንዳልተቆጠቡ መገናኛ ብዙኀን አትተዋል። ባለፈው ዓርብ ፤ የካርቱም ዩንቨርስቲ ባለሥልጣናት አንድ ሳምንት ቀደም አድርገው ፣ በአመዛኙ ትምህርት የመስጠት ተግባራቸውን ያቋረጡ ሲሆን፤ አንድ የዩንቨርስቲው የዜና ምንጭ አንዳስታወቀው፤ ተማሪዎቹ፣ የፊታችን ዓርብ ከሚጀመረው የረማደን የአንድ ወር ጾም ማብቂያ በኋላ፣ ለፈተና ተዘጋጅተው እንዲመለሱ ነው የተነገራቸው። አንድ ወር በሆነው ተቃውሞ ፣ የዩንቨርስቲ ተማሪዎችም በትጋት መሳተፋቸው ነው የሚነገርላቸው። ስለሱዳኑ የተቃውሞ እንቅሥቃሴ ---ተክሌ የኋላ--

Sudan Khartoum Proteste
ምስል Mohammed Fiat

ባለሥልጣናቱ ምናልባት ከዚህ ውሳኔ የደረሱት፤ ተቃውሞው ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ፤ ባለፈው ረቡዕ የታየውን የመሰለ እጅግ ብርቱ ተቃውሞ ፣ዩንቨርስቲው አጋጥሞት እንደማያውቅ በመገንዘቡ ሳይሆን እንዳልቀረ ተመልክቷል። ተቃውሞውን ለመበተን ፖሊስ የሚያስለቅስ ጋዝ ነበረ የረጨው። ዛሬ አንድ ወር በሆነው ተከታታይ የተቃውሞ ሰልፍ ፤ ተቃዋሚዎች ያሰሙት የነበረው መፈክር በሰሜን አፍሪቃ በተቀጣጠለው የህዝብ መነሳሳት፤ ወጣቶች ያስተጋቡት የነበረውን ጥሪ የሚያስታውስ መሆኑን AFP ዘግቧል። ሌላው ተማሪዎቹን ያናደዳቸው ጉዳይ በዛ ያሉ ባልደረቦቻቸው ተይዘው መታሠራቸውና ፣ የትምህርት ጊዜአቸው የሚተጓጎልባቸው መሆኑ ነው።

ባለፉት ጥቂት ሳምንታት፤ ተቃውሞው ይበልጥ እየተጠናከረ ይስተጋባ የነበረው ዓርብ -ዓርብ በየመሥጊዱ ከሚደረግ ጸሎትና ሥግደት በኋላ ነበር። በዚህ ላይ በተለይ በካርቱም መንትያ ከተማ በዖምዱርማን ፣ ለተቃውሞው የዑማ ፓርቲ ደጋፊዎች ግንባር ቀደም ሆነው ነው የተገኙት። ተቃውሞው ፤እስከምን ድረስ ጠንካራ የሚባል ነው? የሱዳን መንግሥት ከፈተኛ ባለሥልጣናትንስ እስከምን ድረስ ነው ያሳሰበው?

Sudan Khartoum Proteste
ምስል Mohammed Fiat

የዶይቼ ቨለ የእንግሊዝኛው ክፍል ባልደረባ አይሳክ ሙጋቢ ያነጋገራቸው፤ የስምጥ ሸለቆው ተቋም የተሰኘው የምርምር ማዕከል አባል ማግዲ ኧል ጊዙሊ፣ እንዲህ ይላሉ።

«ተቃውሞው የቱን ያህል የከረረ እንደነበረ፤ በራሳቸው በፕሬዚዳንቱ ምላሽ መገንዘብ ይቻላል። እርሳቸውም መጠን ባለፈ ስሜትና አገላለጽ ነበረ የተቃውሞውን ሰልፍ የተቹት።

ሌሎች የገዥው NCP(ናሽናል ኮንግረስ ፓርቲ ) ባለሥልጣናትም በተመሳሳይ ቋንቋ ነው የተቹት። ሁኔታው ያሳሰባቸው ነው የሚመስሉት። ምንም እንኳ የተቃውሞው ሰልፍ ከሞላ ጎደል ጥቂት ሰዎችን ያሰባሰበ ቢሆንም፣ ቀጣይነት ያለው መሆኑን አሳይቷል። ተማሪዎቹም ከሞላ ጎደል በየዕለቱ ከካርቱም ዩንቨርስቲ ቅጽር ግቢ ውጭ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ከመጣር አልቦዘኑም። መንግሥት ፤ ከዚህ ቀደም ዐይቶት በማያውቀው ሁኔታ ነው በጽናት በመቃወም ላይ ያሉት። እ ጎ አ ከ 1995 ዓ ም ወዲህ፣ መንግሥት አጋጥሞት የማያውቀውን ፤ የአገሪቱን እምብርት ፤ መዲናይቱን ካርቱምን ያናወጠ ብርቱ ተቃውሞ ነው ያሳዩት።»

ዓማር አልበሺር ፣ ተቃውሞውን አስመልክተው የሚናገሩት ድንጋጤን ለመሸፈን ጥረት የተደረገበት፤ አሁንም ተወዳጅ መሪ መሆናቸውን የሚዘበዝብ ነው። እውን ተወዳጅ ናቸው? መግዲ ኧል ጊዙሊ --

A South Sudanese protester (C) faces Sudanese policemen during scuffles at a counter protest demanding self-determintation and independance for South Sudan in Khartoum, Sudan, 09 October 2010. According to local media reports, the protest was organized to counter another one the same day, by Sudanese government supporters calling for Sudan's unity in reference to the upcoming South Sudan referendum planned for 09 January 2011. The two protests come one day after the arrival of a UN delegation to Khartoum on 08 October. The referendum is to decide wether South Sudan will remain or not part of Sudan. EPA/STRINGER +++(c) dpa - Bildfunk+++
ምስል picture alliance/dpa

«እሁንም፤ የአንድ አካባቢ ተመራጭ ናቸው። ይህ እርግጥ ነው፤ ግን አገሪቱ ተከፋፍላለች። በአርሳቸው ላይ እየሰፋ የመጣ ተቃውሞ አለ። ይህ ተቃውሞ፣ እምነት ጥለውባቸው በነበሩ በአንዳንድ አካባቢዎች ጭምር ነው የተከሠተው። አዎ ፣ በተለይ በመዲናይቱ ተቀባይነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሰ ነው የመጣው። በይበልጥ በወጣቱ ትውልድ !»

በገዥው NCP ፓርቲ መካከል ያለው መከፋፈል፣ እስከምን ድረስ ኦማር ሐሰን ኧል በሺርን በሥልጣናቸው ተደላድለው ሱዳንን እንዳይገዙ ሳንክ ይሆናል? መግዲ ኧል ጋዙሊ ተጨማሪ ጥያቄ ቀርቦላቸው ነበር እርሳቸውም እንዲህ መልሰዋል።

«እርግጥ መንግሥት፤ ከማንኛውም በላይ በ NCP ውስጣዊ ክፍፍል ነው ተግሮቱ የሚያይልበት። ሁለት ጎራዎች አሉ። ህገ-መንግሥቱ በተሃድሶ እንዲሻሻል የሚጠይቁ ፣ የሚሹ ፣ አሉ። ይህም ሲሆን በተቃውሞው ጎራ ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ወደራስ በማምጣት ከሞላ ጎደል በጎዳናዎች ያለውን የተቃውሞ ቁጣ ማብረድ ይቻላል የሚሉ ወገኖች አሉ።

Sudan Präsident Umar Hasan Ahmad al-Baschir
ምስል Reuters

እንደሚመስለኝ ይኸኛው ስልት ውድቅ የሚሆን ነው፤ ምክንያቱም፣ የተቃውሞ ሰልፈኞቹ፤ አሁን ጎዳና ላይ ናቸው። ለፖለቲካ ፓርቲዎች ስሞታ አሁን ጊዜ ያላቸው አይመስልም። እነዚህ ፓርቲዎች፤ ከ NCP ጋር በሰፊው ለመጣመር ቢፈልጉም እንኳ የሚሠምር አይመስልኝም። እቅዱ የሚሠራ አይደለም። ሌላቅ ምላሽ፤ እርግጥ አየል ያለ ፣ በኃይል የማረቅ እርምጃ ነው የሚሆነው! ይህን ደግሞ፣ ራሳቸው ፕሬዚዳንቱ የሚደግፉት ነው የሚመስለው።»

ተክሌ የኋላ

ነጋሽ መሐመድ፣

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ