ሥደተኞች እና የጀርመን ምርጫ
ማክሰኞ፣ ጳጉሜን 5 2005
የፊታችን መስከረም አጋማሽ ጀርመን በሚካሔደዉ ምርጫ ከአምስት ሚሊዮን የሚበልጡ ስደተኞች ወይም የዉጪ ዝርያ ያላቸዉ ጀርመናዉያን የመምረጥ መብት አላቸዉ።በምርጫዉ መሳተፍ አለመሳተፋቸዉ የሚወሰነዉ ግን በስደተኝነት ዳራቸዉ ማለት ለመምረጥ የሚያስችላቸዉን ሠነድ (ዜግነት) በማግኘት፥ አለማግኘታቸዉ ነዉ።ከዚሕም በተጨማሪ እድሜያቸዉ ለመምረጥ የሚበቃ መሆን አለበት፥ የመምረጥ መብታቸዉ በጤና ወይም በሌላ ሕጋዊ ምክንያት ያልተገፈፈ መሆኑም ሊረጋገጥ ይገባል።የመምረጥ ፍላጎቱም መታከል አለበት።ናኦሚ ኮንራድ የዘገበችዉን ነጋሽ መሐመድ እንደሚከተለዉ አጠናቅሮታል።
በርሊን የመጣበትን ምክንያት ሲጠየቅ፥ «ፍቅር» ይላል ዮአን ዲያትስ እየተፍለቀለቀ።በዘንቀ-ብዙ ነዋሪዎችዋ የተዥጎረጎረችዉን በርሊንንም (የሚያፈቅራትን ቆንጆ ያክል) ባይሆንም ለመዉደድ፥ ለመመልመድ ጊዜ አልፈጀበትም።ወላጆቹ ከኩባ ሚያሚ-ዩናይትድ ስቴትስ የተሰደዱ ኩባዉያን ናቸዉ።እሱ አሜሪካዊ።ቅይጥ-ማንነት።የዛሬ ሰባት ዓመት ግድም ሌላ ጨመረበት። ጀርመናዊነትን። ምክንያት?
«ምክንያቱም የመወሰን መብት እንዲኖረኝ በመፈለጌ ነዉ።መራሔ-መንግሥት ወይም የምክር ቤት እንደራሴ መምረጥ እፈልጋለሁ።በፊት አይፈቀድልኝም ነበር።»
የጀርመን መንግሥት የዛሬ ሁለት ዓመት ይፋ ባደረገዉ ጥናት መሠረት እንደ ዲያትስ ሁሉ ጀርመን ዉስጥ 16 ሚሊዮን ስደተኞች እና የስደተኛ ዝርያ ያላቸዉ ሰዎች አሉ።ለመምረጥ ወይም ለመመረጥ ግን አድም እድሜያቸዉ ባለመድረሱ፥ አለያም ጀርመናዊ ዜግነት ሥለሌላቸዉ አብዛኞቹ አይችሉም።መምረጥ የሚችለዉ የጀርመን ፓስፖርት ማለት ዜግነት ያለዉ ብቻ ነዉና
የአዉሮጳ ሕብረት አባል ሐገራት ዜጎች ግን ከሌሎቹ ለየት ያለ መብት አላቸዉ።ለከተማ መስተዳድር እና ለአዉሮጳ ምክር ቤት በሚደረገዉ ምርጫ ድምፅ የመስጠት መብት አላቸዉ።ለጀርመን ምክር ቤት ግን እነሱም ቢሆኑ መምረጥ አይችሉም።
ከተቀረዉ ከአስራ-ስድስት ሚሊዮኑ የመምረጥ-መመረጥ መብት ያለዉ አንድ አምስተኛ ያሕሉ ነዉ።ከነሱም መሐል ድምፁን የማይሰጥ አለ።አምና የተደረገ ጥናት እንዳመለከተዉ ከአራት ዓመት በፊት በተደረገዉ ምርጫ መምረጥ ከሚችለዉ ስደተኛ ድምፁን የሰጠዉ 72.3 በመቶዉ ነዉ።ከአጡራዉ ጀርመናዊ ግን 81.5 ከመቶዉ መርጧል።የዉጪ ዝርያ ያለዉ ወደ ምርጫ ጣቢያ የማይሔድበት ምክንያት የተለያየ ነዉ።ዋናዉ ግን አንድም የልምድ አለያም የፍላጎት ማነስ ነዉ።ዲያትስ ይሕን ሲሰማ ጭንቅላቱን ይነቀንቃል።«መሆን የለበትም» እንደማለት።
«አሜሪካ እንደሚሆነዉ በፖስታ ሳጥኔ ዉስጥ የድምፅ መስጪያ ካርድሕ ይኸዉልሕ፥ እና ምረጥ ሥባል ፌዝ ይመስለኛል።መምረጥ ዴሞክራሲያዊ መብትሕ ነዉ።አሜሪካ አሁንም ድረስ ለምርጫ በመመዘግብ ጉዳይ እየተወዛገብን ነዉ።እዚሕ በፍላጎት ነዉ።አሜሪካ ግን መንጃ ፍቃድ ለማገኘት ስታመለክት «ለምርጫ እንመዝግብሕ» እያሉ ይነዘንዙሐል።»
የፖለቲካ ፓርቲዎችን በመደገፉ ረገድ አብዛኞቹ ስደተኞች ከሁለቱ ትላልቅ ፓርቲዎች ከሶሻል ዴሞክራቲኩ ፓርቲ (SPD) እና ከክርስቲያን ዴሞክራቲክ ሕብረት አንዱን ይመርጣሉ።የጀርመን የምጣኔ ሐብት ጥናት ተቋም የስደተኞች ጉዳይ አጥኚ ኢንግሪድ ቱቺ እንደሚሉት ከሁለቱ አንዱን የመምረጡ ዝንቤላ ደግሞ በየፖለቲካ ፓርቲዎቹ መርሕ እና በየስደተኛዉ ዳራ ላይ የተመረተ ነዉ።
«ባጠቃላይ ሲታይ፥ ቀድሞ እንግዳ ሠራተኞች የመጡባቸዉ ሐገራት ተወላጆች በልማዱ ለሠራተኛዉ መደብ የቆመዉን SPDን ወደ መምረጡ ያዳላሉ።ዘግየት ብለዉ ከምሥራቅ አዉሮጳ ወደ ጀርመን የተመለሱ (የጥንት) ጀርመናዉያንና ከዚያ የፈለሱ ስደተኞች ባንፃሩ ወደ CDU ማዘንበሉን ይመርጣሉ።የዚሕ አይነት አቅጣጫ አለ።»
የአረንጓዴዎቹ ፓርቲም ተወዳጅ እየሆነ ነዉ።በተለይ የስደተኞቹ ሁለተኛ ትዉልድ ማለት ከስደተኞቹ ወይም ከፈላሾቹ ቤተ-ሰቦች ጀርመን ተወልደዉ ካደጉት አስራ-ሥምንት ከመቶ ያሕሉ ከትላልቆቹ ፓርቲዎች ይልቅ አረንጓዴዉን ይመርጣሉ።ያም ሆኖ ሁለቱ ትላልቅ ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ባጠቃላይ ከዉጪ ተወላጅ የአርባ ከመቶዉን ድጋፍ እንደያዙ ነዉ።
ነጋሽ መሐመድ
አርያም ተክሌ