1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርምር በምርታማ የሰብል አዝርእት ላይ፣

ረቡዕ፣ ሐምሌ 27 2003

ድርቅና ረሃብን ፤ የእህልን ምርት ከፍ በማድረግ ፤ ድርቅንና በሽታንም የሚቋቋሙ አዝርእትን ይበልጥ ለዘር በማዋል፣ ለምርምርና ለተሞክሮአዊም እውቀት ላቅ ያለ ግምት በመስጠት፤ ሰፊ ጥረት እስካልተደረገ ድረስ ፣የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ ያዳግታል ነው የሚባለው።

https://p.dw.com/p/Rdiy
ምርምር በሰብል አዝርእት ላይ፣
ስንዴምስል picture alliance/dpa

ባለፈው ሳምንት ድርቅን ለመቋቋም ረሃብንም ለመታገል፤ ለዘለቄታው አገር-በቀል የሰብል አዝርእትና ዕጽዋትን ጠቀሜታም ሆነ ድርሻ በተመለከተ ፤ በዚህ ዝግጅት የመጀመሪያ ክፍል ላይ ፤ ኢትዮጵያዊውን የአዝርእት ተፈጥሮ ተመራማሪና ፤ የአዝርእቱም ዘር እንዳይጠፋ ሰፊ አስተዋጽዖ ያደረጉትን ሳይንቲስት ዶ/ር መላኩ ወረደን በማነጋገር ማቅረባችን ይታወስ ይሆናል። ዛሬም ፤ ከአርሳቸው ጋር ቀጣዩን ሁለተኛ ክፍል ይዘንላችሁ የምንቀርብ ሲሆን፤አንድ ዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅም የሚሉትን አካተናል።

(ሙዚቃ)---------------

(ቃለ ምልልስ )---------

ድርቅን ለመሳሰሉ የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ መቅሰፍቶች፤ ለሌሎችም ቢሆን መላ በመሻቱ ረገድ፤ ባጠቃላይ አፍሪቃውያንም ሆኑ ኢትዮጵያውያን ሳይንቲስቶች፤ እስከምን ድረስ ይመክራሉ፦ ይዘክራሉ? አንድ ችግር ነበረ ፣ ሆኖም ያ ችግር እየተወገደ መጥቷል ሲሉ ዶ/ር መላኩ እንደሚከተለው ያብራራሉ።

(ድምፅ)------

የረጅም ዘመን ታሪክ ባላት ኢትዮጵያ፣ አርሶ-አደሮቿ በተመክሮ ያካባቱት ዕውቀት ሰፊ ግንዛቤ ሊያገኝ እንደሚገባ፤ ዶ/ር መላኩ ያሳስባሉ።በተመክሮ የዳበረ ዕውቀትን ከሳይንስ ጋር በማጣመር፣ ኢትዮጵያን ለመሰለ በብዝኀ-ህይወት ለታወቀች አገር ያለው ጠቀሜታ ከፍ ያለ መሆኑንም ነው በየጊዜው የሚገልጹት። ከራስ ግንዛቤ ችግር ባሻገር፤ ሌላም ከውጭ የሚሰነዘር ብርቱ ፈተና መኖሩን፣ በአዝርእት ተፈጥሮ ምርምር ረገድ የታወቁት ሳይንቲስት መግለጽ ብቻ ሳይሆን እርሱንም መቋቋሚያው ብልሃት እንደማይጠፋ በመተማመን እንዲህ ሲሉ ያብራራሉ---።

(ድምፅ) ------

(ሙዚቃ)---------

የአየር ንብረት ቢዛባም ፤ ረሃብን መቋቋሚያውና የምግብ ዋስትናን ማረጋገጫው ዘዴ፣

የተፈጥሮ አካባቢን እምብዛም ሳይጋፉ ፣ የዓለምን ረሃብና ድህነትን እንዲቀነስ ማብቃት፤ የተሰኘው መርኅ፤ ዋና ጽ/ቤቱ በሞንትፐልዬር ፣ ፈረንሳይ የሚገኘው Consultative Group on International Agricultutral Research በአኅጽሮት (CGIAR)የተሰኘው ዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ፤ የምክክር ቡድን የተሰኘው ድርጅት ተምኔታዊ ዓላማ ነው ። ድርቅና ረሃብ፤ በ 10 ሺ የሚቆጠሩ የአፍሪቃው ቀንድ ተወላጆችና ከገደለ ወዲህ፤ ይኸው ድርጅት ፤ በዓለም ዙሪያ የምግብ ዋስትናን ይበልጥ ማረጋገጥ ይቻል ዘንድ፣ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር የሚያስወጣ የምርምር እርምጃ አንቀሳቅሷል። የዶቸ ቨለዋ Irene Quaile የድርጅቱን ዋና የሥራ መሪ፤ Lloyd Le Page ን አናጋግራለች፤ ለእኛ ዝግጅት ይስማማ ዘንድ እንደሚከተለው ሰብሰብ አድርገን እናቀርበዋለን።

አሁን የተጠቀሰው በእንግሊዝኛው ምኅጻር CGIAR በመባል የታወቀው ድርጅት እ ጎ አ በ 1971 ዓ ም፤ ነበረ በሞቃትና መለስተኛ ሞቃት አገሮች፤ በምርምር ይበልጥ ምርታማ የሆኑ አዝርእትን በማስፋፋትና የተሻሉ የከብት ዝርዮችን በማሠማራት የምግብ እጥረትን ለመቋቋም ሲባል የተቋቋመው። ከ 40 ዓመት ወዲህ፣ ድርጅቱ፤ ወደ ዓለም አቀፍ መረብነት አድጎ፣ በ 4 ክፍላተ ዓለም፤ ከመንግሥታትና የመንግሥታት ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር ተባብረው የሚሠሩ 15 ጣቢያዎች አሉት። ባለፉት አያሌ ዓመታትም፤ ድርጅቱ፤ በተለያዩ አካባቢዎች፤ በሀገራዊ አዝርእት ላይ ብቻ ማትኮሩን ትቶ፣ ይበልጥ የተባበረ ተግባር እንዲካሄድ ፤ በዓለም ዙሪያ የሚገኙት ቡድኖቹም፤ የግብርናን ተግባር ከውሃ ፣ አፈር ፤ ብዝኀ-ህይወትና የአየር ንብረት ጋር አዛምደው እንዲይዙት የሚያደርግ ነው። አዲሱ ብዙ ሚሊዮን ዶላር የፈሰሰበት የምርምርና ሥራ እንቅስቃሴ፣ የመጀመሪያ ትኩረቱ ንቃተ ኅሊናን ከፍ ማድረግና አርሶ-አደሮች፤ የተሻለ አዝመራ እንዲሰበስቡ ወይም ምርታቸውን ከፍ እንዲያደርጉ ማብቃት ነው። ይሁንና እንደሚገመተው አንድ ቢሊዮን ህዝብ በመራብ ላይ በሚገኙበት ሁኔታ፤ ቁጥሩ እጅግ እየናረ የሄደውን ያለምን ህዝብ የመመገቡ ተግዳሮት ከምንጊዜውም የላቀ ነው። የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ--ሎይድ ለ ፔጅ--

1,«ቀደም አድርጎ ፣ ለየት ላሉ ቀውሶች ፍቱን አብነቱን በመሻት ፣ እርምጃ ለመውሰድ የሚያስችለን ዋና ምሳሌ፤ በአፍሪቃው ቀንድ ያጋጠመው ድርቅ ነው። ድርቅ የሚያጋጥመው በአየር ንብረት ለውጥ ነው። ረሃብ ግን የሚያጋጥመው ፣ በፖለቲካ አያያዝ ሳቢያ ነው። አስቀድሞ ተገቢውን ጥንቃቄና ዝግጅት ባለማድረግም ረሃብ ሊያጋጥም ይችላል።»

የግብርና ምርምር ፤ በሶማልያ የደረሰውን ዓይነት የፖለቲካና የፀጥታ ችግር አይፈታም። የአስቸኳይ ሁኔታ የምግብ እርዳታ እንዲቀርብ ግን መርዳት ይችላል። ያም ሆኖ ረዥም ሂደት ያለው ጣጣ ነው ይላሉ፣ ለ ፔጅ---

2,« ምርምር ብዙ ዓመታት የሚወስድ ተግባር ነው። ለአንዳንድ አካባቢዎች የሚስማሙ አዝርእትን ማፍራት ፤ በተወሰኑ አካባቢዎች ያለው ሁኔታ የሚያመቻቸውን ለማግኘት ጊዜና የምርምር ቁርጠኛነትን ይጠይቃል። ይህም ባለሙያዎችንና የገንዘብ ምንጭን ጭምር ያጠቃልላል። ባለፉት 10 እና 15 ዓመታት ያስተዋልነው ቢኖር ፤ በያመቱ ለጋሾች ለግብርና ምርምር የሚመድቡት በጀት እያሽቆለቆለ መምጣቱን ነው። ገበሬዎች፤ ድርቅን ፣ በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ የሚከሠት አዳዲስ የእህል ምችንም ይበልጥ የሚቋቋሙ ሰብሎችን ማምረት፤ ይችሉ ዘንድ፣ ይህ አዝማሚያ ሊቀለበስ ይገባል። ውሃ በበዛበት ሐሩርም ባየለበት ሌላም ሳንክ በሚያጋጥምበት ሁኔታ ተቋቁመው የሚገኙ የሰብል ዓይነቶች ያስፈልጋሉ።»

አዲሱ መርኀ-ግብር ፣ በዓለም ዙሪያ ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በድህነት የማቀቁ ወገኖች፤ በዓለም አቀፍ የፋይናንስ ቀውስ፤ በኃይል ምንጭ የዋጋ ንረት፤ የተፈጥሮ ሀብት አለቅጥ በመበዝበዙና በአየር ንብረት ለውጥ ሳቢያ ጭምር ፤ አሁን ፣ በይበልጥ በተፈጠረው የምግብ ቀውስ የተጎዱት ወገኖች ለሚኖሩባቸው አካባቢዎች ነው የላቀ ትኩረት የሰጠው።

የዓለም ህዝብ ከሚመገበው 1/5ኛውን የሚሸፍነው በአልሚ ምግብነትም፤ በአዳጊ አገሮችም ፤ የአንደኛነቱን ደረጃ የያዘው ስንዴ ነው። ታዲያ በረጅም እቅድ፤ የምግብ ዋስትና ለማስገኘት ፤ የሞንትፐልዬው ድርጅት ስንዴን ይበልጥ ለማስፋፋት የነደፈው መርኀ-ግብር እንደ አንድ ምሳሌ የሚታይ ነው ።

3,«በአሁኑ ጊዜ፣ እንደሚገመተው ከሆነ፣ የስንዴ ተፈላጊነት እ ጎ አ በ 2050 60% ይደርሳል። በዚያን ጊዜ ደግሞ የአየር ንብረት መዛባት፤ የስንዴ ምርት ከ 20-30% እንዲቀነስ ማስገደዱ እንደማይቀር ነው የሚተነበየው። ጥረት በማድረግ ላይ ያለነው፤ ይበልጥ ምርታማነት የሚታይባቸውን የስንዴ ዓይነቶች በምርምር ለማስገኘት ነው። በዓለም ዙሪያ ፣ አብዛኛው ስንዴ የሚመረተው ከበለጸጉት አገሮች ውጭ ነው ።ይህ ብዙዎችን ያስገርማል። የሚመረተውም፤ ከመለስተኛ ይዞታ እስከ አነስተኛ ማሳዎች ባሏቸው ገበሬዎች ነው። ስለሆነም፣ በተለይ፣ የስንዴን ምርት ለመጨመር ነው የምንፈልገው።»

ተክሌ የኋላ

አርያም ተክሌ