1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሜርክል-በነበሩበት ፀኑ ቬስተርቬለ ሽቅብ ሲወጡ ሽታይንማየር ቁልቁል---

እሑድ፣ መስከረም 17 2002

«መራጮቹ ወስኑ።እና ዉጤቱ ለሶሻል ዲሞክራቶች ዕለቱን መራር አድርጎታል።

https://p.dw.com/p/JqJs
ሜርክልምስል AP

የጀርመን ሕዝብ የሐገሪቱን ወግ አጥባቂ የፖለቲካ ማሕበር CDU/CSUን በአብላጫ ድምፅ መረጠ።እስካሁን ድረስ በሥልጣን ላይ ያለዉን «ታላቁን» ተጣማሪ መንግሥት ከሶሻል ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ SPD ጋር የመሠረቱት እትማማች ፓርቲዎች CDU/ CSU ከአጠቃላዩ የምክር ቤት መቀመጫ 230 ዉን አግኝተዋል።በዚሕ ዉጤት መሠረት ከምርጫዉ ዘመቻ ጀምሮ በሰፊዉ እንደታመነዉ እትማማቾቹ ፓርቲዎች ከነፃ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (FDP) ጋር የወደፊቱን መንግሥት ይመሰርታሉ።መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል ለሚቀጥሉት አራት አመታት የመሪነቱን ሥልጣን እንደያዙ ይቀጥላሉ።ሜርክል ዛሬ ለድል ብሥራት ለታደሙ የፓርቲያቸዉ አባላትና ደጋፊዎች እንዳሉት የአንድ ፓርቲ ብቻ ሳይሆን የመላዉ ጀርመን መራሒተ-መንግሥት መሆን ነዉ-የሚሹት።
ድምፅ
«የምርጫ ግባችንን መምታቱ ተሳክቶልናል።CDU/CSU ከFDP ጋር ተጣማሪ መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችለን አስተማማኝ አብላጫ ድምፅ አግኝተናል።ይሕ ደግሞ ጥሩ ነዉ።---የእኔ እምነት የጀርመናዊያን በሙሉ መራሒተ መንግሥት መሆን ነበር።አሁንም የመላዉ ጀርመናዊያን መራሒተ-መንግሥት መሆን ነዉ-የምሻዉ።»

Deutschland Bundestagswahlen 2009 FDP Guido Westerwelle Flash-Galerie
ቬስተርቬለምስል AP

«የነጋዴ ወዳጅ» ተብሎ የሚጠራዉ የነፃ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ FDP ካጠቃላዩ መቀመጫ ዘጠና ሰባቱን አግኝቷል።ፓርቲዉ በታሪኩ ይሕን ያሕል ከፍተኛ ድምፅ አግኝቶ አያዉቅም።ሜርክል እንዳረጋገጡት FDP የወደፊቱ ተጣማሪ መንግሥት መሥራች ነዉ።በተጣማሪዉ መንግሥት ዉስጥ የምክትል መራሔ-መንግሥትነቱን ሥልጣን ከዉጪ ጉዳይ ሚንስትርነቱ ጋር ደርበዉ የሚይዙት የFDP መሪ ጉዪዶ ቬስተርቬለም ሥልጣን እንደሚጋሩ እርግጠኛ ናቸዉ።
ድምፅ
«በዚሕ ልዩ ዉጤት በጣም ተደስተናል።የዚያኑ ያክል ይሕ ማለት ከሁሉም በላይ ሐላፊነት መቀበል ማለት መሆኑን እናዉቃለን።ይሕን ሐላፊነት ለቀበል ደግሞ ዝግጁ ነን።ጀርመንን ከእንግዲሕ በጋራ መምራት እንፈልጋለን።---»

በዛሬዉ ምርጫ የሶሻል ዲሞክራቶቹ ፓርቲ (SPD) በታሪኩ የማያዉቀዉ ዉድቀት ነዉ-ያጋጠመዉ።ከምክር ቤቱ መቀመጫ 147 መቀመጫዎች ነዉ-ያገኘዉ።ፓርቲዉን ወክለዉ ለመራሔ-መንግሥትነት የተፎካከሩት ዉጪ ጉዳይ ሚንስትር ፍራንክ ቫልተር ሽታይን ማየር እንዳሉት ዉጤቱ ለፓርቲያቸዉ «መራር» ነዉ።
ድምፅ
«መራጮቹ ወስኑ።እና ዉጤቱ ለሶሻል ዲሞክራቶች ዕለቱን መራር አድርጎታል።መራርነቱ ምንም አያነጋግርም።በጣም በጣም ከፍተኛ፥ ከፍተኛ የምርጫ ዘመቻ ካደረግን በሕዋላ፥ በየመንገዱ፥ በየሥፍራዉ ጣም ብዙ፥ ብዙ ድጋፍ ከገኘሁ በሕዋላ እንዲሕ አይነት ዉጤት መምጣቱ መራር ሽንፈት ነዉ።»

Deutschland Bundestagswahlen 2009 SPD Pressekonferenz Frank-Walter Steinmeier
ሽታይንማየርምስል AP

የግራዎቹ ፓርቲ ካጠቃላዩ መቀመጫ ሰባ-ሰባት በማግኘት አራተኛዉ ጠንካራ ፓርቲ ለመሆን ሲበቃ አረንጓዴዎቹ ስልሳ-ሰባት መቀመጫዎችን አሸንፈዋል።