ማዕከላዊ ኢጣልያን የመታው የመሬት መንቀጥቀጥ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 18 2008
በአማትሪስ ብቻ 35 ሰዎች መሞታቸው ተነግሯል ።በመቶዎች የሚቆጠሩ የቆሰሉ ሲሆን በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጊዜያዊ መጠለያ ያስፈልጋቸዋል ። በአስኮሊፒቼኖ ክፍለ ሃገር ደግሞ የሞቱት ቁጥር 17 መድረሱ ተነግሯል ።በሬክተር መለኪያ 6 በተመዘገበው እና ሦስት ከተሞችን ወደ ፍርስራሽነት በቀየረው በዚሁ ርዕደ መሬት በተለይ ከከተማ ወጣ ባሉ አካባቢዎች የሞቱት እና የተጎዱት ቁጥር ሊጨምር እንደሚችል የዓይን ምስክሮች ተናግረዋል ። በ አማትሪስ እንዳልነበረች መሆንዋን ያሳወቁት የከተማይቱ ከንቲባ ሰርግዮ ፒሮዚ የአደጋው ሰለባዎች ቁጥር ይጨምራል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል ። የኢጣልያ የሲብል ጥበቃ መሥሪያ ቤት ሃላፊ ፋብሪዝዮ ኩርችዮ እንዳሉት በህይወት ያሉ ሰዎች ለማግኘት ፍለጋው ቀጥሏል ።
«በአሳሳቢ እና በአስቸኳይ ሁኔታ ላይ የሚገኙት ፣የአርኳታ አማትሪቼ እና አኩማሊ እንዲሁም ማርቼ አካባቢዎች መሆናቸውን ማረጋገጥ እንችላለን ። አሁን የምንናገረው ስለ ነፍስ አድን ዘመቻዎች ነው ።ጥሩው ዜና ከመንገዶች አብዛኛዎቹ እንደገና አገልግሎት መስጠት ጀምረዋል ። ስለዚህ እነዚህ አካባቢዎች ዘንድ የእሳት አደጋ ሠራተኞች በአሁኑ ጊዜ ሊደርሱ ይችላሉ ።በተጨማሪም ስለዚህ እዚያ የነፍስ አድን ሠራተኞች አሉን ፍለጋ የሚያካሂዱ እና ሰዎችን የሚታደጉ አነፍናፊ ውሾች አሉ ። ግልፅ ነው ሁሉም በበጎ ፈቃድ ሠራተኖች እገዛ ነው የሚካሄደው ። »
ላቲን የተባለችው ክፍለ ሃገር አስተዳደር ሃላፊ ብሩኖ ፍራታሲ እንደተናገሩት በአሁኑ ደረጃ የአደጋውን ሰለባዎች ቁጥር በትክክል ለመናገር አስቸጋሪ መሆኑን ያስረዳሉ ።
«ለጊዜው የተረጋገጠ ቁጥር የለንም ። ማረጋገጥ ያለብን የምናውቀውን ብቻ ነው ።የፈረሱ ህንፃዎች አሉ ። ስለዚህ ምናልባት በዚያ የአደጋው ሰለባዎች ሊኖሩ ይችላሉ ።ሆኖም ለአሁኑ በበርካታ ምክንያቶች የየአደጋውን ሰለባዎች ቁጥር ለማወቅ አይቻልም ።ምክንያቱም ያለው መረጃ በቂ አይደለም ።የሚገኘውም ዜና በሙሉ አልተረጋገጠም ። »
ትናንት ከለሊቱ 9 ሰዓት ከ36 ደቂቃ ላይ ማዕከላዊ ኢጣልያን የመታው ርዕደ መሬት ሮምን ነዝሯል ። የአድርያቲክ ባህር ዳርቻዎቹ የላዝዮ የኡምባርያ እና የሌማርቺ አካባቢዎች ድረስም ተሰምቷል ።
ኂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ