ማሊ-ጥቃት በቲምቡክቱ ከተማ ላይ
ሰኞ፣ ሰኔ 25 2004የተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ተወካዮች ቅዳሜ ዕለት ተሰባስበው የትኛው ቦታ በባህል ቅርጽነት መዘርዝራቸው ውስጥ እንደሚመዘገብ ሲወያዩ አንድ አሳዛኝ ዜና ደረሳቸው። አሳዛኙ ዜና እኢአ ከ1988 ዓም አንስቶ በዓለም ቅርስነት ጥበቃ የሚደረግላት የማሊዋ የቲምቡክቱ ከተማ ላይ ጥቃት መድረሱን ነበር።
አንሣር-ዲን በመባል የሚታወቀው አማፂ ቡድን ከአል-ቃኢዳ ጋ የተሳሰረ አክራሪ ቡድን ነው። የቡድኑ ታጣቂዎች የጥንት ታዋቂ መቃብሮች እና ሐውልቶችን በመጥረቢያ እንዳፈረሱ የዓይን ምሥክሮች ተናግረዋል። እንዲሁም ቡድኑ 16 የቅዱሳን መቃብሮች እና ሐውልቾቻቸውን በሙሉ ለመውደም መዛታቸው ተነግሯል። በርካታ በደቡብ ማሊ የሚኖሩ ዜጎች በሰሜን ላሉ ቤተሰብና ዘመዶቻቸው ተጨንቀዋል። አንድ ተቃዋሚ ሰልፈኛ ለዶይቸ ቬለ እንደገለፀው፤ « የማሊ መንግስት ያለበትን ኋላፊነት እንዲወጣ እንፈልጋለን። መንግስት ወደ ጦርነት እንድንዘምት መሳሪያ ሊያስታጥቀን ይገባል። አንድ ራሱን የቻለ የሲቪል ቡድን በማደራጀት ላይ እንገኛለን። በሰሜን ያሉ ወንድሞቻችን በባዶ እጃቸው እየታገሉ ነው ። ዱላ እና ድንጋይ ይዘው ከካላሺንኮፍ መሳሪያ ጋ»
የቲምቡክቱ ከተማ «የበረሀ ዕንቁ» በመባልም ትታወቃለች። ከተማዋ በተባበሩት መንግስታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) በቅርስነት እኢአ 1988 ተመዝግባለች። በውስጧ ያሉት ጥንታዊ መስጊዶች እና አብያተ-መፅሐፍት
ሳይቀሩ ስለ ቲምቡክቱ ታሪካዊነት ይመሰክራሉ። ይህም ስፍራ የአገር ጎብኝዎች መስብ ነበር። አሁን ግን የቱዓሬግ አማፂያን እና አንሣር-ዲን የተባለው እስላማዊ አክራሪ ቡድን ከተማይቱን በቁጥጥር ስር አውለዋታል።
የዩኔስኮ ዋና ኃላፊ ኢሪና ቦኮቫ «በባህል ቅርሱ ላይ ለደረሰው ጥቃት ምንም አይነት ነገር ምክንያት ሊሆን አይችልም። የደረሰው ውድመት ይህ ነው የሚባል አይደለም። አንሣር ዲን ጥቃቱን በፍጥነት ማቆም አለበት» ሲሉ አሳስበዋል።
በመዲና ባማኮ የተመሰረተው የሽግግር መንግስት ለመጠናከር ጥረት በሚያደርግበት በአሁኑ ወቅት በሰሜናዊው ማሊ የቱዓሬግ አማፂያን ጥቃታቸውን ቀጥለዋል። አላማቸው፤
«አዛዋድ» በሚል መጠሪያ እራሷን የቻለች አገር መመስረት ነው። የአክራሪ ሙስሊሞቹ ቡድን ከቱዋሬግ ዓማጺያን ጋር አሁን የሰሜን ማሊን ሁለት-ሶሥተኛ ግዛት ተቆጣጥሯል።
ሜቲው ጊውዴር በጄነቭ ዮንቨርሲት የሳህል ጉዳዮች አጥኚ ናቸው። በሲቪሉ ህዝብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት በፍጥነት መፍትሄ ሊያገኝ ይገባል ይላሉ። ካለበለዚያ የርስ በርስ ጦርነት መከፈቱ አይቀሬ ነው።
« ሁሉም አሁን ስለጦርነት እና ስለበቀል የሚናገሩት ሁሉ የስካሁኑ ጦርነቱ ካስከተለው በላይ ሰዎችን ለስደትና ለጉዳት እያጋለጡ ነው። የሚሰደዱ እና የሚጎዱ ሰዎች ይጠብቋቸዋል። ሰሜኑን የሃገሪቱን ክፍል ከያዙት ቡድኖች ጋ በመጀመሪያ ፖለቲካዊ ድርድር ማካሄድ የሚችል የተረጋጋ እና ጠንካራ የሆነ መንግስት ባማኮ ላይ ያስፈልገናል። እንዲህ አይነት መንግስት እስካሁን የለንም። መዲናይቱ ባማኮ እስካልተጠናከረች ድረስ
በአሁኑ ሰዓት ወደ ሰሜን ሄዶ በወታደራዊ ኃይል መፍትሄ መሻቱ አደገኛ ውጤት ሊያስከትል ይችላል። »
ጠንካራ የማሊ መንግስት ስለሌለ በብዙ የቲምቡክቱ ነዋሪዎች አለም አቀፉ ማህበረሰብ ነው ተስፋቸው። በሰሜናዊ ማሊ በተባባሰው ግጭት እና ወንጀል ምክንያት የተባበሩት መንግስታት እንዳስታወቀው 300 000 ሰዎች ቀያቸውን ጥለው ተሰደዋል። አብዛኞቹም በጎረቤት አገሮች ጥገኝነት እየጠየቁ ነው።
ልደት አበበ
ሒሩት መለሰ