ሙኒክ ጥቃት፥ 10 ሰው ተገደለ
ቅዳሜ፣ ሐምሌ 16 2008በጀርመን የሙኒክ ከተማ የገበያ አዳራሽ ትናንት ጥቃት በማድረስ 9 ሰው የገደለው የ18 ዓመት ጀርመናዊ ኢራናዊ ወጣት ራሱን ማጥፋቱን ፖሊስ አስታወቀ። የ18 ዓመቱ ጥቃት አድራሽ ዴቪድ አሊ ሶንቦሊ ከገበያ አዳራሹ የሚወጡትን ሰዎች በዘፈቀደ እየተኮሰ ሲገድል የሚያሳይ ምስል በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች ተለቀዋል። ፖሊስ የሙኒክ ከተማን ትናት ማምሻውን ሙሉ ለሙሉ ተቆጣጥሮ ቆይቷል። ማንኛውም ሰው እንዳይንቀሳቀስም ታግዶ ነበር። የጀርመን ፖሊስ የትናንቱ ጥቃት የደረሰበትን ምክንያት ለማጣራት ምርመራ እያደረገ ነው።
ጥቃቱን ያደረሰው የጀርመን እና የኢራን ጣምራ ዜግነት ያለው የ18 ዓመት ወጣት መኾኑን ፖሊስ አስታውቋል። በኦሎምፒያ የገበያ አዳራሽ ከማክዶናልድ ፊት ለፊት በመሸሽ ላይ የነበሩ ዘጠኝ ሰዎችን በዘፈቀደ እየተኮሰ ከገደለ በኋላ ቆየት ብሎ ራሱን ማጥፋቱን ፖሊስ ገልጧል። ከሟቾቹ መካከል ከአንድ የ45 ዓመት ጎልማሳ በስተቀር ሁሉም ከ14 እስከ 20 ዓመት የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ወጣቶች መሆናቸው ይፋ ኾኗል። በትናንቱ ጥቃት 27 ሰዎች የመቁሰል አደጋ ደርሶባቸዋል። ሦስቱ አሳሳቢ በሆነ ደረጃ ላይ ይገኛሉ። ተጠርጣሪው ጥቃት አድራሽ ጀርመን ውስጥ በኖረባቸው በርካታ ዓመታት ከዚህ ቀደም አንዳችም የወንጀል ድርጊት ስለመፈጸሙ የሚያሳይ መረጃ እንደሌለ ፖሊስ አስታውቋል። የትናንቱ ጥቃት የሽብር ጥቃት ይሁን አለያም በዘፈቀደ የተደረገ ግድያ ፖሊስ በማጣራት ላይ ይገኛል። መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሀገሪቱን የፌዴራል የደኅንነት ካቢኔ ለአስቸኳይ ስብሰባ ጠርተዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ