መድኃኒት የተላመደው የሳንባ ነቀርሳ በኢትዮጵያ
ሐሙስ፣ መጋቢት 15 2003ለበሽታው ህክምና በሚሰጥበት በብቸኛው የቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል በዚህ በሽታ ላይ ክትትል የሚያደርገው ቡድን መሪ ዶክተር ዳንኤል መረሳ ለዶቼቬለ እንዳስረዱት ፣ ባለፉት አንድና 2 ዓመታት ፤ ሁለት መቶ ታካሚዎች መድኃኒት ማግኝት ችለዋል ። የተወሰኑ ደግሞ ህክምና ለመጀመር ተራቸውን እየተጠባበቁ ነው ። የሳንባ ነቀርሳ መንስኤ የሆነው TB bacilus በጀርመናዊው ሳይንቲስት በዶክተር ሮበርት ኮኽ ከታወቀ ዛሬ 129 ዓመት ቢሞላውም አሁንም በርካታ ሰዎች በበሽታው ህይወታቸው ማለፉ አልቀረም ። ከዛሬ 2 ዓመት በፊት እንኳን በዚህ በሽታ ቁጥራቸው 1.7 ሚሊዮን ሰዎች ሞተዋል ። ከተወሰኑ ዓመታት ወዲህ ደግሞ መድኃኒት የተላመደው የሳንባ ነቀርሳ በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንደሚባለው ሆኖ በሽታውን ለመከላከል ብሎም ለማጥፋት በተጀመረው ጥረት ላይ ተጨማሪ ዕንቅፋት ሆኗል ። ዛሬ የሚታሰበውን የዓለም የሳንባ ነቀርሳ ቀን ምክንያት በማድረግ የዓለም የጤና ድርጅት ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው በመጪዎቹ 5 ዓመታት መድኃኒት በተላመደው ሳንባ ነቀርሳ የሚያዙ ከ 2 ሚሊዮን በላይ አዳዲስ በሽተኞች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል ። የዚህ ችግር ተጠቂ በሆነችው በኢትዮጵያም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባል ህሙማን እንዳሉ ዶክተር ዳንኤል መረሳ በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል በበሽታው ላይ ክትትል የሚያደርገው ቡድን መሪ ለዶቼቬለ አስረድተዋል ። ድምፅ እንደ ዓለም ጤና ድርጅት መድኃኒት በተላመደው ሳንባ ነቀርሳ የተያዙ ህሙማን ቁጥር ከ3 ዓመት በፊትወደ 440 ሺህ ይደርስ ነበር ከነዚህም 150 ሺው ህይወታቸው አልፏል ። ዶክተር ዳንኤል እንደሚሉት ችግሩ የዚህ ዓይነቱ የሳንባ ነቀርሳ መድኃኒት ዋጋ መወደድና ህክምናውንም ቀላል አለመሆኑ ነው ። ያም ሆኖ ዶክተር ዳንኤል እንደሚሉት በኢትዮጵያ መድኃኒቱን ለህሙማን ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ ነው ። ድምፅ በርካታ የሳንባ ነቀርሳ ህሙማን በሚገኙባት እንደ ኢትዮጵያ በመሳሰሉ ሀገራት በሽታውን ለመከላከል የሚደረገውን ጥረት ለማሳካት ተጨማሪ የገንዘብ እርዳታ ያስፈልጋል ። አለበለዚያ ግን እስካሁን የተገኘው ውጤት ወደ ኃላ ተቀልብሶ የኃሊት ጉዞ መጀመሩ የማይቀር እንደሚሆን የዓለም የጤና ድርጅት ያስጠነቅቃል ። ባለሞያው ዶክተር ዳንኤል ደግሞ ህብረተሰቡ በሽታውን መከላከል ላይ እንዲያተኩር ይመክራሉ ። ድምፅ
ሂሩት መለሰ
አርያም ተክሌ