ሃገራቸዉን በቁጥጥራቸዉ ያደረጉ የአፍሪቃ ባለሥልጣናት
አፍሪቃ ዉስጥ ስልጣን ላይ የሚገኙ ፖለቲከኛ ቤተሰቦቻቸዉን ባለኃብት ሲያደርጉ ይታያል። ወንድ ልጅ የፕሬዚደንትነት ስልጣንን ከአባቱ መዉረሱ፤ ሴት ልጅ ደግሞ የሃገሪቱን አንድ ግዙፍ ኩባንያ በከፍተኛ ተጠሪነት ማስተዳደርዋ፤ ሚስትም መሾምዋ የተለመደ ክስተት ነዉ። ለምሳሌ ያህል በፎቶ ከታች የተዘረዘሩት አፍሪቃዉያን ባለስልጣናት ተጠቃሽ ናቸዉ።
ወንድ ልጄ፤ የግል ጠባቂዬ
ሙሆዚ ካንሩጋባ ለዘመናት ስልጣን ላይ ተንሰራፍተዉ የሚገኙት የዩጋንዳዉ ፕሬዚዳንት የዩዌሪ ሙሲቪኒ ልጅ ናቸዉ። ሙሆዚ ካንሩጋባ የፕሬዚዳንት የዩዌሪ ሙሲቪኒ ልዩ ጠባቂ የሆነዉን የክቡር ዘበኛ ጦር በሜጀር ጀነራል ማዕረግነት ይመራሉ። የፕሬዚዳንት ሙሴቪኒ ሚስት ወ/ሮ ጃኔት በበኩላቸዉ የዩጋንዳ የትምርህት እና የስፖርት ሚኒስትር ናቸዉ። የሙሴቪኒ አማች ሳም ኩቴሳ የዩጋንዳ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ ተሾመዉ እያገለገሉ ይገኛሉ።
ቱጃርዋ የፕሬዚዳንቱ ልጅ
የአንጎላዉ ፕሬዚዳንት የመጀመርያ ልጅ ኢዛቤል ዲሻንቶስ በአፍሪቃ ከሚገኙት አስር ቱጃር ሴቶች መካከል አንዷ ናቸዉ። እኒህ ሴት የአንጎላ የተቅሳቃሽ ስልክ ግልጋሎት ሰጭ ኩባንያ እንዲሁም በተለያዩ የሃገሪቱ ቦታዎች ላይ የሚገኝ የታዋቂዉ ግዙፍ የገበያ አዳራሽ ባለቤትም ናቸዉ። ከዚህ ሌላ ኢዛቤል ዶሻንቶስ «ሶንአንጎል» የተሰኘዉ የመንግሥት የነዳት ዘይት ማዉጫ ኩባንያያን በዋና ተጠሪነት ያስተዳድራሉ። የኢዛቤል ወንድም ጆሴ ፊሎሜኖ በበኩላቸዉ ከአምስት ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚያንቀሳቅሰዉን «FSDEA» የተሰኘዉ የመንግሥት ፈንድ ይመራሉ።
አባቴ የሥራ ድልደላን ይችላሉ
ቴዮድሮ ንጌማ ኦብያንግ ማንጉየ ለኢክዋቶርያል ጊኒ ሁለተኛዉ ምክትል ፕሬዚዳንት ናቸዉ። በሌላ በኩል የፕሬዚዳንቱም ልጅ ናቸዉ። አባታቸዉ ፕሬዚዳንት ቴዮዶሮ ኦብያንግ ንጉማ ምባሶጎ ከጎርጎረሳዊዉ 1979 ዓ.ም ጀምሮ በትረስልጣኑን ጨብጠዋል። የእንጀራ ልጃቸዉም ጋብርኤል ምቤጋ የሃገሪቱ የነዳጅ ዘይት ሚኒስትር ናቸዉ። አማቻቸዉ ካንዲዶ ንሱየ ኦኮሞ እስከ ጎርጎረሳዊዉ 2015 ዓ.ም ጌፔትሮል የተሰኘዉን የነዳጅ ዘይት ኩባንያ አስተዳድረዋል። አሁኑ ደግሞ የሃገሪቱ የስፖርት ሚኒስትር ሆነዉ ተሾመዋል።
መንትዮቹ ከፍተኛ ባለስልጣናት
ጃኔት ዴዜሪ ካቢላ ክዩንጉ የቀድሞዉ የኮንጎ ፕሬዚዳንት ላዉሪንት ካቢላ ሴት ልጅ ናቸዉ። በአሁኑ ወቅት የጃኔት ወንድም ጆሴፍ ካቢላ ኮንጎን በፕሬዚዳንትነት እያስተዳደሩ ነዉ። ወ/ሮ ጃኔት የኮንጎ ፓርላማ አባል ሲሆኑ በሃገሪቱ የአንድ የብዙኃን መገናኛ ባለቤትም ናቸዉ። «ፓናማ ፔፐርስ» የተሰኘዉ ሰነድ እንዳጋለጠዉ ጃኔት በኮንጎ የሚገኝ የተንቀሳቃሽ ስልክ ግልጋሎት መስጫ አጋር የሆነ ግዙፍ ኩባንያ ዋና ተጠሪም ናቸዉ።
ከፀሐፊነት ወደ ቀዳሚዊ እመቤትነት
ግሪስ ሙጋቤ የዚምባቤን በትረ ስልጣን ለረጅም ዘመናት ተቆናጠዉ የሚገኙት የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ሁለተኛ ሚስት ናቸዉ። የሙጋቤና የግሪስ ፍቅር የጀመረዉ ግሪስ የሙጋቤ ፀሐፊ ሆነዉ ተቀጥረዉ ሲያገለግሉ ሳለ ነዉ። ቀዳሚዊ እመቤትነት ግሪስ ሙጋቢ በአሁኑ ወቅት የዚምባቤ ገዥ ፓርቲ ዉስጥ ባለዉ «የሴቶች-ሊግ» ከፍተኛ ተሰሚነት እና ስልጣን ያላቸዉ ሰዉ ናቸዉ። የ 51 ዓመትዋ ግሪስ ሙጋቤ የ 92 ዓመቱ የባለቤታቸዉ የፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ ተተኪና ይሆናሉ ተብሎም ነዉ የሚታሰበዉ።
የቀድሞው የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ዙማ
ንኮሳዛና ድላሚኒ ዙማ የአፍሪቃ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሆነዉ የተመረጡ የመጀመርያዋ ሴት ባለስልጣን ናቸዉ። ዙማ በሃገራቸዉ በደቡብ አፍሪቃ የረጅም ጊዜ የፖለቲካ ስልጣን ልምድ አላቸዉ። ዙማ በፕሬዚዳንት ኔልሰን ማንዴላ የስልጣን ዘመን የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ከዝያም በፕሬዚዳንት ታምቦ እንቤኪ ዘመነ የሃገሪቱ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነዉ አገልግለዋል። በመጨሻ ቀድሞ ባላቸዉ በፕሬዚዳንት ጄኮብ ዙማ ዘመምን የሃገር አስተዳደር ሚኒስትር ነበሩ። አሁን የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚዳንት ለመሆን ተስፋን ሰንቀዋል።
መንግሥት በቤተሰብ አባልነት ሲያዝ
የኮንጎ ሬፓብሊክ ፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሱ-ንጉየሶ ቤተሰቦች በሃገሪቱ ዋንኛ የተባሉትን ኩባንያዎች እና የሃገሪቱን የፖለቲካ የስልጣን ቦታዎች ይዘዉ ይገኛሉ። የፕሬዚዳንቱ ሴት ልጅ ከላዉዲያ(ፎቶ)የፕሬዚዳንቱን አባትዋን የኮሚኒኬሽን ዘርፍ በዋና ተጠሪነት ይመራሉ። የፕሬዚዳንቱ ወንድም በሃገሪቱ ዉስጥ ያሉት በርካታ ኩባንያዎች ባለቤት ናቸዉ። የፕሬዚዳንት ዴኒስ ሳሱ-ንጉየሶ ልጅ ዴኒስ ክሪስታል የአባቱን መንበር ለመረከብ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ ይነገራል።
ፕሬዚደንት ቦንጎ ሁለተኛ
ለ 41 ዓመታት የጋቦንን መንበረ ሥልጣን ተቆጣጥረዉ የዘለቁት አምባገነኑ መሪ ኦማር ቦንጎ ኦኒዲንባ በስልጣን ላይ እያሉ በጎርጎርዮሱ 2009 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል። ከዝያም ልጃቸዉ አሊ ቦንጎ የስልጣኑን ተረከቡ። በጎርጎረሳዊዉ 2016 ዓ,ም በሃገሪቱ በተካሄደ አጨቃጫቂ ምርጫ የሟች ፕሬዚዳንት ልጅ አሊ ቦንጎ 17 ተፎካካሪዎችን ረተዉ ማሸንፈዉ ተነገረና ሁለተኛ ዘመነ ስልጣናቸዉን ቀጥለዋል። በዚህም የቦንጎ ቤተሰቦች የጋቦንን የስልጣን መንበር ከግማሽ ምዕተ ዓመት በላይ ተቆናጠዉ ይገኛሉ።
ልጅየዉም እንደ አባትየዉ
ፋዉሬ ግናሲግቤ ቶጎን ለረጅም ዘመናት የመሩት ፕሬዚዳንት የግናሲግቤ አያዴማ ወደ ሃምሳ የሚጠጉት ልጆች መካከል አንዱ ናቸዉ። ፋዉሬ አባታቸዉ የቶጎ ፕሬዚዳንት ሳሉ እሳቸዉ ሚኒስትር ሆነዉ አገልግለዋል። የፕሬዚዳንት ግናሲግቤ አያዴማ ሲሞቱ ግን ፋዉሬ የአባታቸዉን ቦታ ወረሱ። በኬንያና በቦትስዋና ስልጣን ላይ የሚገኙት የአሁኖቹ ፕሬዚዳንቶች ስልጣናቸዉን የተረከቡትም ከወላጅ አባቶቻቸዉ ነዉ።