ሃርትስ IV የጀርመን ሥራ ገበያ ና የማህበራዊ ድጎማ ለውጥ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 22 2004በቀድሞው የጀርመን መራሄ መንግሥት ጌርሃርድ ሽሮደር ዘመነ መንግሥት በቮክስ ቫገን ኩባንያ ሃላፊ ፔተር ሃርትስ ተዘጋጅቶ የቀረበው የጀርመን ሥራ ገበያ ና የማህበራዊ ድጎማ ለውጥ 10 አመት ቢያስቆጥርም አሁንም አነጋጋሪ ነው ። አጀንዳ 2010 ወይም ሃርትስ 4 በመባል የሚታወቀው ይኽው መርሃ ግብር ጀርመን አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ ካበቋት ምክንያቶች አንዱ ተደርጎ ይወደሳል ። በሌላ በኩል መርሃ ግብሩ የሠራተኞችን መብት በመጫን በአንፃሩ ለአሰሪዎች ከልክ ያለፈ መብት በመስጠት ይተቻል ። ውዳሴናወቀሳየሚቀርብበትን ይህን አሰራር ከመነሻው ተግባራዊ ማድረግ ያስፈለገበት ምክንያት ምን ነበር ? እዚህ ጀርመን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች በመምህርነት የሚያገለግሉት የምጣኔ ሃብት ምሁር ዶክተር ፈቃዱ በቀለ
ያብራሩልናል ።
አዳዲስ የሥር መስኮችን ለመፍጠር አልሞ ሥራ ላይ በዋለው አጀንዳ 2010 የሥራ ና ሠራተኛ አገናኝ መሥሪያ ቤቶች በአዲስ መልክ እንዲዋቀሩ ተደረጓል ። ሌሎችም ለውጦች ተግባራዊ ሆነዋል ። በሃርትስ 4 ከተካሄዱት ለውጦች ዋነኛው የመንግሥት ወጪን ለመቀነስ የተወሰደው እርምጃ ነው ።
ሃርትስ 4 ተረቆ በቀረበበት እጎአ በ2002 በጀርመን የሥራ አጡ ቁጥር ከ4 ሚሊዮን በላይ ነበር ዛሬ ግን ይህ አሃዝ ወደ 2.8 ሚሊዮን ዝቅ ብሏል ። ለዚህም የሃርት 4 ድርሻ የጎላ መሆኑን አንዳንድ የመስኩ ባለሞያዎች ያስረዳሉ ። ዶክተር ፈቃዱ ግን ይህ የአጀንዳ 2010 ውጤት ብቻ ነው ሊባል አይችልም ይላሉ ።
ከሌሎችም ምጣኔ ሃብታዊ ምክንያቶች ጋር ተዳምሮ ጀርመን በአሁኑ ጊዜ ከሌሎቹ በኢንዱስትሪ ከበለፀጉ አገራት በተሻለ ደረጃ እንድትገኝ አብቅቷታል የተባለው አጀንዳ 2010 በተለያዩ አሉታዊ ገፅታዎቹም ይተቻል ።
ያም ሆኖ ጀርመን ከሌሎች የአውሮፓ ሃገራት ጋር በንፅፅር ሲታይ በተለይ ዝቅተኛ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ያላት አገር ናት ። በኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ከሚገኙት አገራት ለምሳሌ ስፓኝ የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር 50 በመቶ ሲደርስ በኢጣልያ ደግሞ 31 በመቶ ነው ። በፈረንሳይ 16 በመቶ ሲሆን በጀርመን ግን 8 በመቶ ብቻ ነው ። በጀርመን የወጣት ሥራ አጥ ቁጥር ሊያንስ የቻለበትን ምክንያትና ሌሎች አገራት ከጀርመን በአርአያነት ሊወስዱት የሚችሉትን አሰራር ዶክተር ፈቃዱ ይገልፃሉ ።
አጀንዳ 2010 ከድጋፉን ተቃውሞው ጋር ቀጥሏል ። ይህ እቅድ በሌላ መተካት አለበት የሚሉ ሃሳቦች አሉ ።
ዶክተር ፈቃዱ በማጠቃለያው እንዳሉት ደግሞ የጀርመንን የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ከወዲሁ መተንበይ አይቻልም ።
ሂሩት መለሰ
ነጋሽ መሐመድ