1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኤኮኖሚአፍሪቃ

የንፁሕ የመጠጥ ዉኃ እጥረት በድሬዳዋ

ሐሙስ፣ ሚያዝያ 17 2016

የምስራቅ ሀገሪቱ የአገልግሎት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው ድሬደዋ የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ሽፋን የፍላጎቱን ሃምሳ በመቶ እንኳን እንደማይደርስ የሚያነሳው የመስተዳድሩ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን "ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም" ህብረተሰቡ ለገጠመው ችግር ዋንኛ ምክንያት መሆኑን ገልጿል

https://p.dw.com/p/4fC09
የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት ለዉኃ በቀን እስከ 100 ብር ድረስ ለማዉጣት ይገደዳሉ
ከድሬዳዋ ነዋሪዎች ከግማሽ የሚበልጡት ንፁሕ የመጠጥ ዉኃ ስለማያገኙ ከሌላ አካባቢ የሚጓጓዝ ዉኃ ለመግዛት ተገድደዋል።ምስል Mesay Teklu/DW

የንፁሕ የመጠጥ ዉኃ እጥረት በድሬዳዋ

በድሬደዋ እየተባባሰ የመጣው የንፁህ የመጠጥ ውኃ ችግር መፍትሄ እንዲፈለግለት ነዋሪዎች ጠየቁ።ከኢትዮጵያ ትላልቅ ከተሞች አንዷ የሆነችዉ ድሬዳዋ ከሐምሳ ከመቶ የሚበልጠዉ  ነዋሪዋ ንፁሕ የመጠጥ ዉኃ አያገኝም።የመስተዳድሩ ውሀና ፍሳሽ ባለስልጣን በፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም እንዲሁም ካልሺየም ባይካርቦኔት በተለምዶ "ጨው" በሚባለው ንጥረ ነገር ሳቢያ የውሀ ማስተላለፊያ መስመሮች በመደፈናቸው የችግሮቹ  መኖር "የሚታወቅ ነው" ባይነዉ።ባለስልጣኑ መፍትሄ የተባሉ ተግባራትን በመዘርዘር በየጊዜው በደምብ እየተሰራ ያልተሄደ እንደሆን "ችግሮቹ በዘላቂነት የሚቀጥሉ ናቸው" ብሏል።

 

የከተማዋ ነዋሪ የሆኑት አቶ እሸቱ በከተማይቱ  የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦቱ ላይ ያለውን ችግር ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪም በተመሳሳይ ችግሩ ከፍተኛ መሆኑን ገልፀዋል።የአስተዳደሩ ውሀ እና ፍሳሽ አገልግሎት ባለስልጣን ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ሙሴ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ምላሽ "ችግሮቹ የሚታወቁ" መሆናቸውን ገልፀዋል ።በየጊዜው የተወሰኑ ከመስመር የሚወጡ የውሀ ጉድጓዶች ተጨምረው ችግሩ ተባብሶ እንደነበር ያነሱት ኃላፊው መፍትሄው ላይ በደምብ እየተሰራ ካልሄደ "ችግሮቹ በዘላቂነት የሚቀጥሉ ናቸው" ብለዋል።

 

የምስራቅ ሀገሪቱ የኢደስትሪ ማዕከል በሆነችው ይሄንኑ ተከትሎ በየጊዜውም እየጨመረ ላለው የውሀ ፍላጎት አለመሟላት መፍትሄው ምንድነው በሚል ለአቶ መሀመድ ላቀረብነው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰተዋል።በከተማዋ አንድ ባለ ሃያ ሊትር ጀሪካን ውሀ ከአስር እስከ አስር ሃያ ብር በውሀ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ ለሚቀርብ አራት ሺህ ሊትር ውሀ ሁለት ሺህ ብር ድረስ እንደሚከፈል ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

የውሀ ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም 

 

የምስራቅ ሀገሪቱ የአገልግሎት እና የኢንዱስትሪ ማዕከል በሆነችው ድሬደዋ የንፁህ መጠጥ ውሀ አቅርቦት ሽፋን የፍላጎቱን ሃምሳ በመቶ እንኳን እንደማይደርስ የሚያነሳው የመስተዳድሩ ውሀ እና ፍሳሽ ባለስልጣን "ፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም" ህብረተሰቡ ለገጠመው ችግር ዋንኛ ምክንያት መሆኑን ገልጿል።በዚህ ረገድ ባለስልጣኑ ባለው አቅም የሚያመርተውን ውሀ "በፍትሀዊነት" ለማዳረስ ጥረት እያደረግኩ ነው ብሏል።አስተዳደሩ በሁለት ቢሊየን ብር ወጪ መልካ ጀብዱ ተብሎ በሚጥራው አካባቢ እያከናወነ ያለው የአዳዲስ ውሀ ጉድጓዶች ቁፋሮ ችግሩን ባይፈታም በማቃለል ረገድ ተስፋ የሚጣልበት ነው ያሉት አቶ መሀመድ ሌሎች የመፍትሄ ጥረቶችም እየተከናወኑ ነው ብለዋል።

አቶ መሐመድ ሙሴ እንደሚሉት ፍላጎትና አቅርቦት ካልተጣጣሙ የዉኃ ችግር መቀጠሉ አይቀርም
የድሬዳዋ ከተማ የዉኃና ፍሳሽ ባለሥልጣን የበላይ ኃላፊ መሐመድ ሙሴምስል Mesay Teklu/DW

 

ተጨማሪ አቅም ለመፍጠር በአሁኑ ሰዓት "የመልካ ፕሮጀክት" በሚል እየተከናወነ ያለ ፕሮጀክት መኖሩን  የጠቀሱት ኃላፊው ፕሮጀክቱ የበጀት እክል ሳይገጠመው የቀጠለ እንደሆን በመጪው አመት ሲጠናቀቅ ለችግሩ ጥቂት አስተዋጽኦ ያበረክታል የሚል እምነት እንዳላቸው ተናግረዋል። ይሁን እንጂ ችግሩን በተገቢው መንገድ መፍትሄ እንዲያገኝ የፌደራልም ሆነ የከተማው መስተዳድር ትኩረት ሰጥተው መስራት እንደሚገባ ጠቁመዋል።

 

የባለስልጣኑ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ ሙሴ ለዶይቼ ቬለ እንደነገሩት በከተማዋ የውሀ አቅርቦት እና ፍላጎት አለመጣጣም ካለው ችግር ባለፈ ካልሺየም ባይካርቦኔት በተለምዶ "ጨው" በሚባለው ንጥረ ነገር ሳቢያ የውሀ መስመሮች መደፈናቸው ችግሩን አባብሶታል ብለዋል።

 

ለከተማይቱ የውሀ አቅርቦት የሚውለው የከርሰ ምድር ውሀ ጨዋማነት ሳቢያ በየዓመቱ ሃያ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን የውሀ ማስተላለፊያ  መስመር በጨው ሳቢያ በመደፈን እንደሚቀየር የጠቀሱት ኃላፊው በቀጣይ ይህም መፍትሄ ካልተበጀለት አስቸጋሪ ሆኖ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።በከተማዋ የሚታየው የውሀ አቅርቦት ችግር በፈጠረው አጋጣሚ በከተማዋ በውሀ ማቅረብ ላይ የተሰማሩ ጋሪዎች እና የውሀ ቦቴዎች እንዲበራከቱ ማድረጉን አስተውለናል።

አንድ ጀሪካን ዉኃ 10 ብር ይሸጣል።ለአንድ ቤተሰብ በቀን እስከ 100 ብር ድረስ ይወጣል
ለድሬዳዋ ሕዝብ የመጠጥ ዉኃ ከሚጓጓዙና ከሚሸጡ መኪኖች አንዱምስል Mesay Teklu/DW

 

በተለያዩ ቦታዎች ግለሰቦች ከቆፈሯቸው የውሀ ጉድጓዶች ውሀን የሚያቀርቡ አካላት አንድ ባለ ሃያ ሊትር ጀሪካን  በአምስት እስከ ሃያ ብር ሁለት ሺህ ሊትር ውሀ ላመጣ  የውሀ ማጓጓዣ ተሽከርካሪ እስከ ሁለት ሺህ ብር ይከፈላል።በየቦታው የመሰል ውሀ ጉድጓዶች መበራከት የከርሰ ምድር ውሀ ሀብት አጠቃቀሙን አይጎዳም ወይ በሚል ከዶይቼ ቬለ ጥያቄ የቀረበላቸው የባለስልጣኑ ስራ አስኪያጅ አቶ መሀመድ "ተፅዕኖ " እንዳለው ገልፀው ማስተካከያ ለማድረግ ከሚመለከተው ተቋም ጋር እንደሚሰራ ተናግረዋል።

እንደ ስራአስኪያጁ እምነት "የፍላጎት እና አቅርቦት አለመጣጣም ፣ የውሀ መስመሮችን ለሚደፍነው ጨው መፍትሄ ማድረግ ካልተቻለ ችግሩ የሚቀጥል ነው።

መሳይ ተክሉ

ነጋሽ መሐመድ

አዜብ ታደሰ