1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅሬታ ያስነሳው የድሬዳዋ የመኪና እንቅስቃሴ ገደብ

ረቡዕ፣ መጋቢት 21 2014

በድሬዳዋ "መንገድ ለሰው" በሚል በየሳምንቱ እሁድ ጠዋት በሞተር ተሽከርካሪ ላይ የጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ በበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ያላስገባ ነው በሚል ከነዋሪው ቅሬታ ቀርቦበታል።የከተማዋ መስተዳድር በእንቅስቃሴ ገደቡ የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ማሻሻያ መደረጉን ገልጿል።

https://p.dw.com/p/49F4l
Skyrocketing price of commodities
ምስል Mesay Teklu/DW

ቅሬታ ያስነሳው የድሬዳዋ የመኪና እንቅስቃሴ ገደብ

የድሬደዋ አስተዳደር "መንገድ ለሰው" በሚል በየሳምንቱ እሁድ ከንጋት 12 ሰዓት እስከ ቀን 6 ሰዓት በሞተር ተሽከርካሪ ላይ የጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ በበርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተፅዕኖ ከግምት ያላስገባ ነው በሚል ከነዋሪው ቅሬታ ቀርቦበታል። የመስተዳድሩ መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ለህብረተሰቡ ጠቀሜታ ያበረክታል በሚል ተግባራዊ የሆነው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ማሻሻያ መደረጉን ገልጿል።

"መንገድ ለሰው" በሚል መሪ ሀሳብ ባሳለፍነው ሳምንት  እሁድ በድሬዳዋ ተግባራዊ የተደረገው የተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ገደብ ድንበር ተሻጋሪ ከሆኑ የጭነት ተሽከርካሪዎች እና አምቡላንሶች ውጭ በከተማው ማንኛውም የሞተር ተሽከርካሪ እንቅስቃሴን የሚከለክል ነው ።የከተማዋ ነዋሪ አቶ ወንደሰን ኪዳኔ ውሳኔው ትክክል አይደለም ሲሉ ቅሬታ ሰንዝረዋል። ሌላኛው የከተማዋ ነዋሪም ውሳኔው አስቀድሞ ከህብረተሰቡ ጋር ምክክር ያልተደረገበት በመሆኑ ክፍተቶች ታይቶበታል ብለዋል። የድሬደዋ አስተዳደር የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ብሩክ ፈለቀ ለህብረተሰቡ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ባሉት የሞተር ተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ክልከላ ላይ የተነሱ ቅሬታዎችን መሰረት በማድረግ ማሻሻያዎች እንዲደረጉ መወሰኑን ተናግረዋል።

በየሳምንቱ እሁድ በሞተር ተሽከርካሪ ላይ የተጣለው የእንቅስቃሴ ገደብ በተመረጡ መንገዶች እንዲተገበር የሚል ሀሳብ ቢቀርብም ይህንን ለመተግበር የሚያስችል ሁኔታ አለመኖሩ ተገልጿል። ውሳኔው የተለያዩ ጠቀሜታዎች እንዳሉት በርካቶች ቢስማሙም አተገባበሩን በሚመለከት ያሉ ችግሮች እየታዩ ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል።
መሳይ ተክሉ

ኂሩት መለሰ

ነጋሽ መሐመድ