1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፕሬዚዳንት መንግሥቱ 30 ዓመታት በስደት

ቅዳሜ፣ ግንቦት 21 2013

ለ 17 ዓመታት ኢትዮጵያን የመሩት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በስደት ዓለም 30 ዓመት ሆናቸዉ። በዚሁ ሳምንት 80 ኛ ዓመታቸዉን ደፍነዋል። መስከረም 2 ፤1967 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዘዉዳዊ አገዛዝ ሲገረሰስ እና ወታደራዊዉ ሥርዓት ወደ ስልጣን ሲመጣ መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄደዉ የጦር ሰራዊት ቡድን ወጣቱን ሻለቃ በመሪነት ሾመ።

https://p.dw.com/p/3u9Xy
Äthiopien Mengistu Haile Mariam Armeeoffizier
ምስል Privat

ያስተማሩ ለገበሪዉ መሪት የሰጡ ለደሃዉ የቆሙ ግን አምባገንን ነበሩ

ለ 17 ዓመታት ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በዚምባቤ በስደት ዓለም 30 ዓመት ሆናቸዉ። በዚሁ ሳምንት 80 ኛ ዓመታቸዉን ደፍነዋል።  መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም የኢትዮጵያ ዘዉዳዊ አገዛዝ ሲገረሰስ እና ወታደራዊዉ ሥርዓት ወደ ስልጣን ሲመጣ መፈንቅለ መንግሥቱን ያካሄደዉ የጦር ሰራዊት ቡድን ወጣቱን የሃረር ሦስተኛ ክፍለጦር የመሳርያ ግምጃ ቤት ኃላፊ፤ ሻለቃ መንግሥቱ ኃይለማርያምን  መሪ አድርጎ አስቀመጠ። በወጣቱ ሻለቃ ይመራ የነበረዉ ቡድን ብዙም ሳይቆይ የማርክሲስት ሌኒንስት ርዕዮተ ዓለም ተከታይ መሆኑን አዉጆ የሶሻሊስት ርዕዮተ ዓለምን ከሚከተለዉ ዓለም ተርታ ተሰለፈ። 

«የሰላም፤ የማኅበራዊ እድገትን፤ የዲሞክራሲ ማስገኛ የሆነዉን እና፤ አማራጭ የሌለዉ ሶሻሊዝም፤ ያብባል ይለመልማል» መፈክርን ያነገቡት፤ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም፤ ብዙም ሳይቆይ በሃገሪቱ በነጭ ሽብርን ቀይ-ሽብር ፍልምያ ወጣት አዛዉንቱ ረገፈ። በሌላ በኩል ደርግ መሪት ለገበሪዉ፤ ለደሃዉ መኖርያ ቤት፤ መሰረተ ትምህርት፤ የዉጭ ሃገር የትምህርት እንድልን በመስጠት ለደሃዉ የቆመ መንግሥት ነበር የሚለዉ  ኢትዮጵያዊ ጥቂት አይደለም።

የቀድሞ ኢ.ሕ.ዴ.ሪ. ምክትል ፕሬዝደንት ሌ/ኮለኔል ፍስሃ ደስታ የቀድሞዉን ጓዳቸዉን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያምን  ከኢትዮጵያ ሸሽተዉ ከወጡበት ከግንቦት ወር በመነሳት ያስታዉሳሉ።  

Äthiopien Mengistu Haile Mariam Armeeoffizier
ምስል Privat

«ኮነሬል መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱበትን የግንቦት ወርን ስናስታዉስ፤ በኢትዮጵያ ብዙ የግንቦት ታሪኮች እንዳሉ አይዘነጋም። ልጅ እያሱ የተሾሙት በግንቦት ወር ነበር፤ ልዑል መኮንን ኃይለሥላሴ የሞቱት በግንቦት ወር ነዉ። መለስ ዜናዊ የተወለደዉ ግንቦት አንድ ነዉ። መንግሥቱ ኃይለማርያም የተወለዱት ግንቦት 19 ነዉ። በመንግሥቱ ስልጣን ዘመን በጀናራሎቹ መፈንቅለ መንግሥት የተካሄደዉ ግንቦት ስምንት ነዉ።  ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም ግን ለየት የሚያደርገዉ ነገር ተፈጥሮአል። እንደሚታወቀዉ ወያኔ ኢህአዴግ በሻብያ ረዳትነት በምዕራብያዉን ድጋፍ እየተጠናከረ መጥቶ ከትግራይ እየለቀቀ ወደ መሃል ሃገር እየገሰገሰ በመጣበት ጊዜ ፕሬዚዳንቱ ሁኔታዉን አስመልክተዉ ሚያዝያ 11 ቀን 1983 ዓ.ም ንግግር አድርገዉ ነበር። ሁኔታዉ ግን በዚህ አልቆመም፤ ተገንጣዮቹ መዲና አዲስ አበባን እየከበቡ ስለሄዱ ህዝቡ ጭንቅ ዉስጥ ገባ። ሃገሪቱ አኬልዳማ ትሆናለች የሚል ስጋትም ነገሰ። ህዝበ ክርስታያኑም ሆነ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ህጻን አዋቂ ሳይል በየአድባራቱ እና በየመስጊዱ ፀሎት ምህላ፤ ዱዓ  ሲያደርግ ነበር። አስቸጋሪ ሁኔታ ላይ ነበረ። ግንቦት 13 ቀን 1983 ዓ.ም የኢትዮጵያ ራድዮ ይህን ዜና ከቀኑ ስድስት ሰዓት ላይ ይፋ አደረገ።

"በልዩ ልዩ ወገኖች የሀገሪቱ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን መዉረዳቸው እንደሚበጅ የታመነበት ስለሆነ፣ይህንኑ በማመዛዘን ፕሬዚዳንት መንግሥቱ ኃይለማርያም በዛሬው እለት ከሥልጣን ወርደው ከኢትዮጵያ ዉጭ ሄደዋል።" 

«ይህ ለብዙዎቻችን ዱብዳ ነበር። በተለይ ህዝቡ ያልጠበቀዉ ሁኔታ ነበር ያጋጠመዉ። ከባድ ጊዜ ስለነበር። እኔ አልፎ አልፎ ጥርጣሪ ቢኖረኝም ይህን ያደርጋሉ ብዬ አልገመትኩም ነበር። ምክንያቱም ሁልጊዜ አንድ ኢትዮጵያ ወይም ሞት ይሉ ስለነበር ነዉ። እኔ ከዚህ ከአንድ ወር ግድም በፊት በመንግሥት ዉሳኔ ከጡረታ ተገልዬ ነበር። ይህ ሁሉ ሲከሰት ጡረታ ላይ ነበርኩ። በዚህ አስቸጋሪ ወቅት ጡረታ ላይ መሆኔ እድለኛ ነበርኩ። በጡረታ የተወገድኩበት ምክንያት ትዉልዴ ከሰሜን ስለሆነ ምናልባት ግንኙነት አለዉ በሚል ጥርጣሪ ይመስለኛል። ይህን የምለዉ አንዳንድ ሃሜት ስሰማ ስለነበር ነዉ»

መንግሥቱ ለኢትዮጵያ አንድነት የቆሙ ለደሃ የቆሙ ሃገር ወዳድ ነበሩ የሚልዋቸዉ የሕግ እና የታሪክ ተመራማሪዉ ዶክተር አልማዉ ክፍሌ በበኩላቸዉ አብረዋቸዉ የሚሰሩት ባለስልጣናት ሸፍጥ መንግሥቱን አምባገንነን አድርጓቸዋል ነዉ የሚሉት።

Äthiopien Armeeoffizier Getu Temegna
ምስል Getu Temegna

«እንደ ታሪክ ተማሪ ኮለኔል መንግስቱን የማያቸዉ ሃገር ወዳድ ናቸዉ ። ቆራጥ ናቸዉ። የተቀበሉትን ሃገር ለማስቀጠል፤ ብዙ ጥረት ያደረጉ ሰዉ ናቸዉ። ግን የፖለቲካ አካሄዱ ችግር ነበረበት። ሃገሪቱ እሳቸዉ እንዳሰቡት ልትጓዝላቸዉ አልቻለችም። ወድያዉ የዓለም አቀፉ ፖለቲካ ተቀየረ። ምዕራባዉያንም ከድዋቸዉ። እሳቸዉም ከምስራቁ ዓለም ጋር ተወዳጁ። በዚህ ሂደት ወቅት በሃገሪቱ ዉስብስብ ነገሮች መፈጠር ጀመሩ። ኢህአፓ መኤሶን፤ ሁሉ ተጨምሮ የሃገሪቱ ፖለቲካ አዘቅት ወረደ። ከዝያም የመገዳደል ፖለቲካ ተቀሰቀሰ። የመጀመርያዉ ስህተት የተፈፀመዉ መንግሥቱ በአማካሪዎቻቸዉ ምክንያት፤ ስድሳዎቹ ሚኒስትሮችን መረሸናቸዉ ነዉ። ይህ እርምጃ ፖለቲካዉን የተወሳሰበ አደረገዉ። ከዝያ የሽግግር መንግሥት ተቋቋሞ ወታደራዊዉ መንግሥት ስልጣኑን ከተቆጣጠረ በኋላ፤ የኢህአፓ የተማሪዎች አመፅ ወደ ነጭ ሽብር እና ቀይ ሽብር ተገባ። ይህ ሁሉ ዉስብስብ ለተገንጣይ ቡድኖች እድል ፈጠረላቸዉ። የኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ግንኙነት ተበላሸ፤ በሃገሪቱ ጎጠኛ በዛ፤ መንግሥትን ያኮረፉ ሰዎች በየቦታዉ ተበራከቱ። አንባገነን ቡድኖች በየቦታዉ ሕግን አጥፍተዉ የራሳቸዉን ሕግ ያመጡ ሰዎች ተፈጠሩ። ወሰን በሌለዉ፤ ገደብ በሌለዉ፤ ስልጣን ተገን በማድረግ መግደል  ማሰር  መፍታት ተጀመረ። ዜጋዉን አሰቃዩት። ከዝያ ነዉ ደርግ ጠፍቶ ለምንጭራቅ አይመጣም የሚል ሰዉ ተፈጠረ። ከዛም ጭራቅ መጣ »  

መንግሥቱ ከአገር ከሸሹ ከ30 ዓመት በኋላ በኢትዮጵያ በክፍልሃገር ሳይሆን በክልል፤ ወደብ አልባ፤ በጎሳ የተከፋፈለች ሃገር ሆነች። የታሪክ እና የሕግ ባለሞያዉ ዶክተር አልማዉ ክፍሌ እንደሚሉት  በኢትዮጵያ የባህር ወደብ አልባ መሆን ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማሪምም ተጠያቂ ናቸዉ። 

የዶቼቬለ የእንጊሊዘኛዉ ክፍል የዚምባቤ ዘጋቢ እንደነገረን ኮለኔል መንግሥቱ የቡና በዚምባቤ የበቆሎ እርሻ አላቸዉ፤ ቀደም ሲል የቡና እርሻን ለማልማት ሞክረዉ ነበር፤ ምርቱ አምርቂ አልሆነላቸዉም። የመኖርያ ቤታቸዉ የሚገኘዉ በሰሜናዊ ሃራሪ ታዋቂ ሰዎች እና ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት በሚኖሩበት እና ከፍተኛ ጥበቃ ባለበት ቦታ ነዉ። በዚምባቤ መንግሥቱ ይኖራሉ ይባላል እንጂ ብዙም ለሕዝብ እና ለመገናኛ ብዙኃን የማይታዩ ናቸዉ ሲል ገልጾአል። በዚህ ሳምንት 80ኛ ዓመታቸዉን የያዙት ኮለኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም የዛሬይቱ ኢትዮጵያን ቢያዩ ምን ይሉ ይሆን ለቀድሞዉ የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝደንት ለሌ/ኮለኔል ፍስሃ ደስታ ያቀረብነዉ ጥያቄ ነበር። መልካም ልደትን ለቀድሞዉ ጓዳቸዉ የተመኙት ሌ/ኮለኔል ፍስሃ ደስታ አጠር ያለች መልዕክትም አስተላልፈዋል።

ሙሉ ቅንብሩን ለማድመጥ የድምፅ ማድመጫ ማዕቀፉን በመጫን ይከታተሉ!

አዜብ ታደሰ