1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ፎልክስቫገን ከኢትዮጵያ ሥምምነት ተፈራረመ

ሰኞ፣ ጥር 20 2011

ፎልክስቫገን የኢትዮጵያ ሥራዎች በአራት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ አስታውቋል። የመኪና መገጣጠሚያ ማቋቋም፤ የመኪና ግብዓቶች በኢትዮጵያ እንዲመረቱ ማመቻቸት ዘመናዊ ግልጋሎቶችን ማስተዋወቅና ማሰልጠኛ ማዕከል መክፈት የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው። ስምምነቱ ሲፈረም ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እና የገንዘብ ምኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተገኝተዋል

https://p.dw.com/p/3CL3S
Deutschland Bundespräsident Steinmeier zu Staatsbesuch in Äthiopien
ምስል Office of the Prime Minister Ethiopia 

ፕሬዝዳንት ሽታይንማየር ኢትዮጵያን እየጎበኙ ነው

የጀርመኑ ፎልክስቫገን የመኪና አምራች ኩባንያ ፎልክስ ቫገን ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር እና የገንዘብ ምኒስትሩ አሕመድ ሽዴ በተገኙበት ከኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር የመግባቢያ ሰነድ ተፈራርሟል።

ሰነዱን የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኃላፊ አበበ አበባየሁ እና የኩባንያው የደቡብ አፍሪቃ ቢሮ ኃላፊ ቶስማስ ሼፈር ፈርመውታል።

ኩባንያው በኢትዮጵያ ገበያ በሚሰራቸው ሥራዎች በአራት ጉዳዮች ላይ እንደሚያተኩሩ አስታውቋል። የመኪና መገጣጠሚያ ማቋቋም፤ የመኪና ግብዓቶች በኢትዮጵያ እንዲመረቱ ማመቻቸት ዘመናዊ ግልጋሎቶችን በገበያው ማስተዋወቅ እና የማሰልጠኛ ማዕከል መክፈት የትኩረት አቅጣጫዎቹ ናቸው።

የፎልክስቫገን የደቡብ አፍሪቃ ቢሮ ኃላፊ ቶማስ ሼፈር ኢትዮጵያ በምጣኔ-ሐብታዊ ዕድገቷ እና በሕዝብ ቁጥሯ ለኩባንያቸው ኹነኛ ገበያ ልትሆን እንደምትችል ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ እና ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በኢትዮጵያ ጉብኝት በማድረግ ላይ ከሚገኙት የጀርመኑ ፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋር ተገናኝተዋል። ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ ከጀርመኑ አቻቸው ጋር ባደረጉት ውይይት በኢትዮጵያ እየተካሔዱ ስላሉ ለውጦች ማብራሪያ እንደሰጧቸው ተናግረዋል። 
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እና የአፍሪቃ ኅብረትን ጨምሮ በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ከጀርመን ጋር በትብብር ለመሥራት ዝግጁ መሆኗን ከፕሬዝዳንት ፍራንክ ቫልተር ሽታይንማየር ጋር በኅብረት በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ተናግረዋል።

የጀርመኑ ፕሬዝዳንት በበኩላቸው ኢትዮጵያ በርካታ እንስቶች በመንግሥት ሥልጣን መሾሟን እና ከኤርትራ ጋር ዕርቅ ማውረዷን አድንቀዋል። 
ኢትዮጵያ በኤኮኖሚውም ይሁን በፖለቲካው ዘርፍ ስላሉባት ፈተናዎች ግንዛቤ እንዳላቸው የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አገራቸው ድጋፍ ለማድረግ ፍላጎቷ መሆኑን ጠቁመዋል። 
ኢትዮጵያውያን በተለይም ወጣቶች ከመንግሥት የማሻሻያ እርምጃዎች ፈጣን ለውጥ መጠበቃቸው አይቀርም ያሉት የጀርመን ፕሬዝዳንት ውጤቱን ለማየት ግን ጊዜ እንደሚወስድ አስረድተው ከማኅበረሰቡ ትዕግስት እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል። 

የጀርመን ኢንዱስትሪ ተወካዮች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው የሚያደርጉት ውይይት ሁለቱን አገሮች የሚጠቅም ውጤት ሊያስገኝ እንደሚችልም ተስፋቸውን ገልጸዋል። 
ጌታቸው ተድላ ኃይለ-ጊዮርጊስ
አዜብ ታደሰ