1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ፌስቡክን» ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያዋሉ ወጣቶች

ዓርብ፣ ግንቦት 16 2011

«ፌስ ቡክን» የመሳሰሉ ማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ሰዎችን በማቀራረብና ፈጣን መረጃ በመለዋወጥ ረገድ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ።የዚያኑ ያህል ደግሞ የጠብና ጥላቻ ምንጭ መሆናቸዉም ይታያል።ኢትዮጵያ ዉስጥም ማሕበራዊ መገኛ ዘዴዎች የሚያስከትሉት ጠብና መለያየት እየተስፋፋ የመጣ ይመስላል ።

https://p.dw.com/p/3J2kQ
Äthiopien Freiwillige der Sidist Kilo Intellectual Society
ምስል Sidist Kilo Intellectual Society

«ፌስቡክን» ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት ያዋሉ ወጣቶች

 

«ስድስት ኪሎ ኢንቴሌክcቿል ሶሳይቲ» በሚል ስም የሚጠራዉ የበጎ አገልግሎት ክበብ ዓባላት ግን ማህበራዊ መገናኛ ዘዴን በተለይም «ፌስቡክን» ለበጎ ዓላማ ለማዋል እየጣሩ ነዉ።ወጣት ገላውዴዎስ ብሩክና  ናኦል ጌታቸው በሃያዎቹ  መጀመሪያ የሚገኙ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የ4ኛ ዓመት ተማሪዎች ናቸው። ወጣት ገላውዴዎስ ብሩክ የጋዜጠኝነትና የኮሚኒኬሽን፤ ወጣት ናኦል ደግሞ  የፈረንሳይኛ ሥነ-ፅሁፍ  ተማሪዎች ናቸው። ወጣቶቹ በተለያዩ የትምህርት ክፍልና የትምህርት መስክ ላይ ቢሆኑም  የሚጋሩት ተመሳሳይ ዓላማና  ፍላጎት  አላቸው። የበጎ ፈቃድ  አገልግሎት። እናም በዩኒቨርስቲዉ  በሚከናወኑ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች ላይ መሳተፍ ያዘወትራሉ።
ወጣቶቹ  በተገናኙ ቁጥር የሚወያዩባቸዉ እና  የሚከነክናቸዉ በርካታ ችግሮች ነበሩ። የወቅቱ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ባህሪ፤  ዩኒቨርስቲዎች የዕውቀት ማዕከል ከመሆን ይልቅ የብጥብጥ ማዕከል እየሆኑ መምጣት፣ በአጠቃላይ በሀገሪቱ  እየወደቀ መጥቷል የሚሉት «የወጣቶች ሞራል»  ያሳስባቸዋል። እናም  አውጥተው  አውርደው የወጣትነትና የተማሪነት አቅማቸው የሚፈቅደውን  ለማድረግ  ወሰኑ። የዩኒቨርሲቲዉ የ4ኛ ዓመት ተማሪ ከሆነዉ ጓደኛቸው ሙአዝ  ጀማል ጋር  በመሆንም  በችግሩ  ላይ   ጥናት ለማድረግ ተስማሙ። 
ጓደኛሞቹ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎችና በአንዳንድ የመንግስት ተቋማት መጠይቆችን በመበተን ባሳሰቧቸዉ መረጃዎች ላይም መለስተኛ ጥናት አደረጉ። በጥናቱ በርካታ ችግሮች መለየታቸዉንም ወጣት ናኦል ጌታቸዉ ያስረዳል።
«የዩንቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ እያለ ፤የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ተማሪዎች ሆኖ እያለ ፤ለምንድነው ወጣቱ በተለያዩ ልዩነቶች የሚጋጨዉ።እንደ ሀገር ለምንድነዉ «በሞራል »የወደቅነዉ።የሚለውንና ለምንድነው ኢኮኖሚያችን ሊያድግ ልቻለው። ለምንድነው ወጣቱ እጁ ላይ ገንዘብ ያልያዘው። የሚለውን እና ደግሞ አብዛኛው ዩኒቨርሲቲ ተማሪ አካባቢ እንደመሆናችን ተማሪውን ስናየው አብዛኛው የትምህርት ጥራቱን ጨምሮ ተማሪው ብቁ እንዳይሆን አድርጎታል ብለን ነዉ ያየነዉ።ለምንድነዉ ተማሪዉ  ብቁ ያልሆነዉ።የመመረቂያ ፅሁፉን ገዝቶ የሚመረቀዉ። ከሌላ ዩኒቨርስቲ ነው የሚኮረጆው መመረቂያ ጽሑፍን ጨምሮ «አሳይመንት» ተማሪው አይሰራም። ተመርቆ ደግሞ ስራ ፈላጊ ነው። እና ይህ ሁሉ ለምንድነዉ የሚሆነው። ተማሪ ለምንድነው ድንጋይ ያሚያነሳዉ። ቤት የሚያቃጥለው። እንደምታየው አብዛኛው ጊዜ ለዚህ ነገር ተጠቂ የሚሆኑት ተማሪዎች ናቸው። እንደ ፍጆታ እንደማገዶ የሚጠቀሙት ለምንድነው ።እኛስ ምን ማድረግ አለብን የሚለውን ነው ለማጥናት የሞከርነው።» በማለት ነዉ ወጣት ናኦል ጌታቸዉ የተናገረዉ።

Äthiopien Freiwillige der Sidist Kilo Intellectual Society
ምስል Sidist Kilo Intellectual Society

በጥናቱ ውጤት መሰረትም በወጣቶች መካከል ተቀራርቦ መነጋገር እና መወያየት ለችግሩ መፍትሄ ይሆናል የሚል ሀሳብ ያዙ። ይህንን ሃሳባቸዉንም በዩኒቨርሲቲዉ ለሚቀርቧቸዉ ጓደኞቻቸዉ እና ዓላማቸዉን ይደግፋሉ ላሏቸዉ ለዩኒቨርሲቲዉ ማህበረሰብ አባላት አቀረቡ።
በዉይይቱ ማብቂያ «ስድስት ኪሎ ኢንቴሌክቿል ሶሳይቲ» በሚል ስም የበጎ አድራጎት ክበብ መሰረቱ። ወጣቶቹ እንሰራዋለን ላሉት የበጎ አድራጎት ስራ ድጋፍ ለማሰባሰብ በመጀመሪያ የመረጡትም የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በተለይም ፌስቡክን ነበር። በዚህም በርካታ ዓላማቸዉን የሚደግፉ ሰዎች ማፍራታቸዉን ወጣት ገላዉዲዮስ ይገልፃል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም ያገኟቸዉን የዓላማ ተጋሪዎቻቸዉን በመያዝም የመጀመሪያ የበጎ አድራጎት ስራቸዉን ጀመሩት የ3 ተከታታይ ቀናት ዘመቻዎችን በማድረግ ነበር።

እነ ገላውዲዩስ ከአንድ ዓመት በፊት ሶስቱ ሆነዉ የመሰረቱት ክበብ አሁን በርካታ ደጋፊዎችና 13 በየሁለት ሳምንቱ እየተገናኙ የሚመክሩ ቋሚ አባላት አሉት። አባላቱ በዩኒቨርሲቲዉ በትምህርት ላይ ያሉና ገሚሶቹ ደግሞ ተመርቀዉ በስራ ላይ ተሰማርተዉ የሚገኙ ናቸዉ። ወጣት ቤዛዊት ብሩክ ከእነዚህ መካከል አንዷ ነች። 
ቤዛዊት ከ3 ዓመት በፊት ነበር በሳይኮሎጂ የትምህርት ዘርፍ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪዋን የያዘችዉ። ላለፉት ሶስት ዓመታትም በአንድ መንግስታዊ ባልሆነ ድርጅት ዉስጥ በማህበራዊ አገልግሎት ሰራተኝነትና በሥነ-ልቡና አማካሪነት ተቀጥራ እየሰራች ትገኛለች። ቤዛዊት የክበቡን ዓላማ በመደገፍ አባል የሆነችዉ ከ8 ወር በፊት ሲሆን አባላቱን የተዋወቀቻቸዉም በፌስ ቡክ ነዉ።
ወጣቶቹ ለበጎ አድራጎት ስራዎቻቸዉ ጫማ በመጥረግ፣ የሥነ-ፅሁፍ ምሽቶችን በማዘጋጀት እና ከበጎ አድራጊ ግለሰቦች የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፎችን በመቀበል ይሰራሉ። «ዕዉቀት ነፃ ያወጣል» በሚል መርህ የወጣቱን በተለይም የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎችን የንባብ ባህልን ለማዳበር፣ ለትምህርት ቤቶች የመፃህፍት እና የቁሳቁስ ድጋፍ የሚያደርጉበት በትምህርት ላይ ያተኮረ ፕሮጀክትም አላቸው። 
ከዚህ በተጨማሪም በወጣቶች መካከል ተቀራርቦ የመነጋገር ባህል እንዲዳብር የሚያደርጉ በአብሮነት፣ በሰላም፣ ጥላቻን በማስወገድ እና በሰብዓዊ መብቶች እንዲሁም ለተቸገሩ ወገኖች ድጋፍ ማሰባሰብ ላይም የበጎ አድራጎት ስራዎችን ያከናዉናሉ። ወጣቶቹ ለበጎ አድራጎት ስራቸዉ ድጋፍ ለማሰባሰብ የተጠቀሙበትን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴ ከጥላቻ በማፅዳት ወደ መልካም ነገር የመለወጥ ዓላማና ዕቅድ እንዳላቸዉም ወጣት ቤዛዊት ትናገራለች።

Äthiopien Freiwillige der Sidist Kilo Intellectual Society
ምስል Sidist Kilo Intellectual Society

«ያው ቃላት ናቸው ወደ ድርጊት የሚለውጡት። እና እነሱን   መርጠን መጠቀም አለብን ።እዛ ላይ ያሉ ቃላቶች ናቸው ችግር እየፈተጠሩ ያሉት ።እና አብዛኛው ሰው ትንታኔ ይሰጣል ለነገሩ ክብደት ሰጥቶ አይደለም ።ማለትም ብዙ ሰው «በየሶሻል ሚዲያዉ» ይፅፋል ።ከዚያ ነው ወደ መሬት ወርዶ ብዙ ዩኒቨርሲቲዎች ብዙ ቦታዎች እና ከተማዎች እየተበጠበጡ ያሉት።» ካለች በኋላ  ወጣቱን ይህንን  ለመለወጥና  ለማስተካከል   እንችላለን የሚል እምነት አለኝ። እና ጥላቻ ለማስወገድ ቆርጠን ተነስተናል። ጠንካራ በሆነ ፍላጎት እየተንቀሳቀስን ነው። መልካም ቃላትን ወደ መሬት ለማውረድ ።» በማለት ገልፃለች።
በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚሰነዘሩ ጥላቻን የሚሰብኩ ቃላት ተፅዕኖአቸዉ መሬት ላይ በመዉረድ  እያደረሰ ያለዉ ጉዳት አሳሳቢ መሆኑን የሚናገሩት ወጣቶቹ ይህንን ለመከላከልም ተቃራኒ ሀሳብ ይዘዉ ፌስ ቡክ ላይ መጥፎ ቃላት በመለዋወጥ የሚያውቋቸዉን ጓደኞቻቸዉን በመጋበዝም ፊት ለፊት የሚካሄዱ ዉይይቶችን ያዘጋጃሉ። "በእነዚህ ዉይይቶች ፌስ ቡክ ላይ ያለዉ ገፅታ ከነባራዊዉ ሁኔታ የተለዬ መሆኑን ተገንዝበናል" ይላል ወጣት ናኦል።

የክበቡ አባላት በአዳራሽ ከሚያዘጋጁት ዉይይት በተጨማሪ ዘረኝነትን የሚቃወም ፍቅርና ሰላምን የሚሰብኩ ቃላትን በመጠቀምና በተናጠል ሰዎችን በማነጋጋርም የጎዳና ላይ ቅስቀሳዎችንም ያደርጋሉ። የዚህ አይነቱ ቅስቀሳ በኢትዮጵያ ብዙ የተለመደ ባይሆንም ከማህበረሰቡ ያገኙት ምላሽ ግን በጣም ጥሩ እንደነበር ወጣት ገላዉዲዎስ ያብራራል።
እንደ ወጣት ገላዉዲዮስ እምነት እስካሁን ለወጣቶች መፍትሄ የሚፈልጉት ትልልቆቹ በመሆናቸዉ ወጣቱ የመፍትሄ አካል አልነበረም። በመሆኑም ወጣቶች በሚያመቻቸዉ መንገድ በመሰባሰብና በመወያየት የሀገሪቱን ችግር በመፍታት ሂደት ሊሳተፉ ይገባልም ይላል። 
«ወጣቶች በያሉበት በጣም ብዙ ችግር ያለበት አገር ስለሆንን ትንሽ ነገር ማድረግ  እንኳ በጣም  የ«ሶሉሽን» አካል እንደ መሆን ነዉ።  ከክፉ ስራ ጋር  አላለመተባበር ራሱ ትልቅ የ«ሶሉሽን» አካል መሆን ነዉ። እንኳን ትንሽ ርምጃ በመራመድ ስራዎችን መስራት።  ስለዚህ አቅም አለን ወጣቶች በየቦታው ውይይቶችን በማድረግ ነገሮችን በንግግር የመፍታት ባህልን በማዳበር ፣ዝም ብሎ በሰዎች ከመነዳት አቋም በመያዝ የመፍትሄ አካል ለመሆን መሞከር ይቻላል ብዬ አስባለሁ።»በማለት ነዉ የገለፀዉ።

Äthiopien Freiwillige der Sidist Kilo Intellectual Society
ምስል Sidist Kilo Intellectual Society
Äthiopien Freiwillige der Sidist Kilo Intellectual Society
ምስል Sidist Kilo Intellectual Society

ወጣቶቹ በግል በመሰረቱት ክበብ በትርፍ ጊዜያቸዉ የሚንቀሳቀሱ በመሆኑ የሚሰጡት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በአቅምም፣ በጊዜም የተወሰነ በመሆኑ የፈለጉትን ያህል አለመስራታቸዉን ይገልፃሉ። በመሆኑም በቀጣይ በተሻሻለዉ የሲቪክ ማህበራት እና የበጎ አድራጎት ድርጅቶች አዋጅ መሰረት ክበቡን ህጋዊ ሰዉነት ለማሰጠት አቅደዋል። ይህም በቦታና በጊዜ እንዲሁም በአቅም ሳይወሰኑ ሀገራቸዉን በበጎ ፈቃድ ለማገልገል እንደዚሁም ሰፊ ስራ ለመስራት እንደሚያስችላቸው ይናገራሉ። ለዚህም በዝግጅት ላይ መሆናቸዉንም ወጣቶቹ አጫዉተዉናል።

ሙሉ ቅንብሩን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነዉ ያድምጡ።


 ፀሐይ ጫኔ

ተስፋለም ወልደየስ