1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦርነቱ የማህበራዊ መገናኛቹን ችግር አባብሶት ይሆን?

ዓርብ፣ ኅዳር 18 2013

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት (ሕወሓት) ኃይሎች ጦርነት ከገቡ በኋላ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በጦርነቱ ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች ተበራክተዋል። ጦርነቱ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹን ችግር አባብሶት ይሆን?

https://p.dw.com/p/3lthQ
Äthiopien Addis Abeba Universität Kommunikation Internetsperre
ምስል DW/J. Jeffrey

ጦርነቱ የማህበራዊ መገናኛቹን ችግር አባብሶት ይሆን?

የኢትዮጵያ የፌዴራል መንግስት እና የሕዝባዊ ወያኔ ሓርነት (ሕወሓት) ኃይሎች ጦርነት ከገቡ በኋላ በተለያዩ የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በጦርነቱ ላይ የሚሰጡት አስተያየቶች ተበራክተዋል። የዩናይትድ ስቴትሱ ዋሽንግተን ፖስት እንደዘገበው ከሆነ ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ስለ ትግራይ በትዊተር የሚሰራጩት መልዕክቶች በዚህ ዓመት እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር ከኖቬምበር 4 ወይም ከጥቅምት 25  ቀን አንስቶ እጅጉን ጨምሯል። በቀን አዲስ የሚከፈቱ የትዊተር ገፆች ቁጥርም በአማካይ ከ21 ወደ 245 ከፍ ብሏል። ጋዜጣው የተጠቃሚው ሰው ቁጥር በከፍተኛ ቁጥር መጨመሩን ብቻ ሳይሆን የገለፀው ግጭት ቀስቃሽ እና የጥላቻ ንግግሮችም በፍጥነት እየተሰራጩ እንደሆነ ነው። 
የ 25 ዓመቱ ወጣት ተስፋሁን አብዛኞቹን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የሚጠቀም ሲሆን ቴሌግራም፣ ፌስቡክ እና ኢኒስታግራም የሚያዘወትራቸው እንደሆነ ነግሮናል። የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በቅርቡ እየታዘበ ያለውን ነገር እንዲህ ሲል ይገልፀዋል።« ፖለቲካውን ባላውቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ፍላጎቶች አሉ፤ ነገሮች እንዳይበርዱ የሚፈልጉ አካላት እንዳሉ ግልፅ ነው። እና ብዙ መጥፎ አስተምኅሮቶችም ወደ ህዝቡ ወርደዋል። ተቻችሎ የመኖር እና ብዙ እሴቶች አሁን ላይ በህዝቡ መሀከል የሉም።»
የ 26 ዓመቷ ደራርቱ ጌታቸውም ብትሆን የማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎቹን ችግር ተባባሰ እንጂ አልተሻሻለም ነው የምትለው።
«የማየው ወጣቶች በብሔር ተከፋፍለው የመሰዳደብ አንዱ አንዱን የማንቋሸሽ የማጣጣል አይነት ነው ነገር ነው የምታዘበው ፤ አስታራቂ ነገር አላየሁም፤ በጣም እየተባባሰ እንደሆነ ነው የማስበው»
ወጣት መምህር ታምራት ግን ከሁለቱ ወጣቶች የተለየ አስተያየት ነው ያለው፣«በመንግሥት በተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች የተሰጡ ይመስለኛል። እና ፍርኃት አለ። ሰው እንደሌላው ጊዜ አይመስለኝም። ሰውም አንድ የሆነ ይመስለኛል። እና አልተባባሰም እንደውም እጃቸውን ሰብስበዋል የሚል ግምት አለኝ።»
ከዞን 9 ጦማሪያን አንዱ የነበረው አቤል ዋቤላ በአሁኑ ሰዓት በአንድ የሚዲያ ልማት ድርጅት ውስጥ በአማካሪነት እየሠራ ይገኛል። እሱም እንደ አንድ ብሎገር ማህበራዊ መገናኛ ብዙኃን ላይ የሚንሸራሸሩ ሀሳቦችን በቅርበት ይከታተላል፤ «ያው ማህበረሰቡ ያለበትን ሁኔታ ነው የሚያሳየው።  ... ጦርነት ሲኖር ሁለቱም አካላት በጦርነቱ የበላይነት ለማግኘት የተለያዩ የፕሮፖጋንዳ መልእክቶችን ያሰራጫሉ። ይህንን የሚሰማው የወጣቱ ወይም የማህበረሰቡ አመለካከት የተሳሳተ ይሆንና ያንደኛው አካል መሣሪያ ሆኖ እነዚህ አካላት በጀት መድበው ሰራተኛ አደራጅተው የሚያደርጉትን ስራ ሆይ ሆይ በማለት ያልተገባ ነገሮችን እናያለን። »
ለረዥም ዓመታት በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ የማኅበረሰብ ጥናት መምህር ሆነው ያገለገሉት ዶክተር የራስ ወርቅ አድማሴ በአሁን ሰዓት «ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ» በሚባል መንግስታዊ ያልሆነ የሀሳብ አመንጪ ድርጅት ውስጥ ሥራ አስፈፃሚ ዳሬክተር ናቸው። በተደጋጋሚ ከማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ጋር በተገናኘ የሚፈጠሩት ችግሮች ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚሆን ሳይሆን ዓለም አቀፍ ችግር ነው ይላሉ።  « የቴክኖሎጂው እድገት ለብዙ ሰዎች ትልቅ ኃይል ሰጣቸው። ፊደል የቆጠረ ሁሉ አስተያየቱን ያለ ምንም ገደብ ያለ ምንም ተጠያቂነት ለመስጠት ችሏል። አንዳንዱ አብሮ ዕውቀቱን  ሳያዳብር አስተያየት የመስጠት እድል አገኘ።...ቴክኖሎጂዎች ቀስ ብለው ከመጡ ከአኗኗር ዜብያችን ጋር አብረው እየጎለመሱ ይሄዳሉ አሁን ግን በአለም ላይ በተለይ የኮሚኒኬሽን ቴክኖሎጂው በጣም ፈጣን ከመሆኑ የተነሳ እያንዳንዱ ህብረተሰብ በባህሉ ውስጥ መንገድ ሳያመቻችላቸው እነሱ የሚተዳደሩበትን መንገድ ሳይዘረጋ ከተፍ ይላሉ።»
በኢትዮጵያ የጥላቻ ንግግርን እና የሐሰተኛ መረጃ ሥርጭትን ለመከላከል እና ለመቆጣጠር ይረዳል የተባለ ሕግ ባለፈው የካቲት ወር በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸድቋል። ይሁንና በምክር ቤቱ አዋጁ ቢጸድቅም አሁንም ድረስ ግን አንዳንድ ተጠቃሚዎች አግባብ ያልሆኑ የጥላቻ መልእክቶችን እና መረጃዎችን ከማሰራጨት አላገዳቸውም።

Symbolbild Twitter Konto
ከዚህ ጦርነት ጋር በተያያዘ ስለ ትግራይ በትዊተር የሚሰራጩት መልዕክቶች እጅጉን ጨምሯልምስል picture-alliance/dpa/A. Gombert
Abel Wabella
አቤል ዋቤላ ምስል privat
Facebook Laptop
ምስል picture-alliance/dpa/O. Berg

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ