1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጦርነቱ በአስቸኳይ ይቁም፦ ዩናይትድ ስቴትስ

ማክሰኞ፣ ጥቅምት 15 2015

ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ለሰላም ዕድል እንዲሰጥ ጠየቀች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ፣ ትናንት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ጦርነቱ በአፋጣኝ ቆሞ ተፋላሚ ኃይላት በደቡብ አፍሪቃ በሚካሄደው የሰላም ውይይት በቁም ነገር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

https://p.dw.com/p/4IfZu
USA Ned Price
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይምስል Olivier Douliery/AP Photo/picture alliance

ኔድ ፕራይስ ዩ ልዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተዋል

ዩናይትድ ስቴትስ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚካሄደው ጦርነት በአስቸኳይ ቆሞ ለሰላም ዕድል እንዲሰጥ ጠየቀች። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ፣ ትናንት ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ፣ ጦርነቱ በአፋጣኝ ቆሞ ተፋላሚ ኃይላት በደቡብ አፍሪቃ በሚካሄደው የሰላም ውይይት በቁም ነገር እንዲሳተፉ ጥሪ አቅርበዋል።

የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ትናንት ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ የተመለከቱ ልዩ ልዩ ጥያቄዎች ቀርበውላቸው ምላሽ ሰጥተውባቸዋል። ከእነዚህም መኻከል የኢትዮጵያ ጦር በትግራይ ክልል በቀጠለው ግስጋሴ የመዲናዋን የተወሰነ ክፍል መቆጣጠሩን ማስታወቁን አስመልክቶ ዐሳባቸውን እንዲሰጡ ተጠይቀዋል። ኔድ ፕራይስም፣ጦርነቱ በአስቸኳይ ቆሞ በደቡብ አፍሪቃ ለሚካሄደው የሠላም ንግግር ዕድል እንዲሰጥ ጥሪ አቅርበዋል። "ውጊያው ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ፣ግልጽ አድርገናል።ጦርነቱ መቆም አለበት።በደቡብ አፍሪቃ በሚጀመረው ንግግር፣ለሰላም ዕድል መሰጠት አለበት።"

ጦርነቱ በአፋጣኝ እንዲቆም የጠየቁት ቃል አቀባዩ፣ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ፣ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችና ጭካኔዎችን ለመከላከል የፌዴራልና የትግራይ ክልል ባለሥልጣናት በሰላም ንግግሩ በቁም ነገር እንዲሳተፉ ጠይቀዋል። ኤርትራም ከሰሜን ኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ለቅቃ እንድትወጣ አሳስበዋል።

USA Ukraine-Russland-Konflikt | Pressesprecher Ned Price
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይምስል Tom Brenner/AP Photo/picture alliance

ለቃል አቀባዩ ሌላው ቀርቦላቸው የነበረው ጥያቄ፣ዩናይትድስቴትስና ሌሎች የአውሮፓ ሃገሮች፣በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ያደርጉታል የተባለውን ጣልቃ ገብነት እና ጫና እንዲያቆሙ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በተካሄዱ የተቃውሞ ሰልፎች መጠየቃቸውን የተመለከተ ነበር። አንዳንድ ሰልፈኞች፣ ዩናይትድስቴትስ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አታከብርም በማለት፣የሚወነጅሉ ባነሮችን ስለማንገባቸው የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት የሚሰጠው ምላሽ ምንድን ነው? የተባሉት ቃል አቀባዩ ፣ውንጀላዎቹ ሙሉ በሙሉ የተሳሳቱ ናቸው ብለዋል። "በርግጥም እነዚያ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ የተሳሳቱ ናቸው።የዩናይትድስቴትስ ጥቅም የኢትዩጵያ ሕዝብ ፍላጎት ነው።ሰላም ሲመለስ ማየት፣ግፍ ሲቆም ማየት፣ሉዓላዊ የሆነች መላ ኢትዮጵያን ማየት ነው።ለዚህም ነው በአፍሪቃ ህብረት የሚመራውን ውይይት የደገፍነው።"

ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን በነጩ ቤተመንግስት ፊት ለፊት፣የውጭ ጫናን ለመመከት እና የምዕራባውያንን ጣልቃ ገብነት በመቃወም ሰሞኑን ያሰሙትን ጥያቄና መልዕክት አግኝታችኋል? ተብለው የተጠየቁት ኔድ ፕራይስ ቀጣዩን መልሰዋል። "በመጀመሪያ ደረጃ፣በኢትዮጵያ ውስጥና በዓለም ዙሪያ ካሉ ኢትዮጵያውያን፣ከፍ ያሉ እና ግልጽ መልዕክቶችን ሰምተናል።የእኛ ልዩ መልዕክተኛ ላለፉት ሳምንታት በአዲስ አበባ ከተለያዩ አካላት ጋር በመገናኘት ሰፋ ያለ ጊዜ አሳልፈዋል።በርግጥም እዚህ አሜሪካን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ ንቁ ኢትዮጵያውያን ዲያስፖራ ማኀበረሰቦች አሉ።" 

የኢትዮጵያ ሕዝብ ብጥብጡን ለማስቆም፣ ሰብዓዊ ዕርዳታ ለመስጠት፣የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስመለስና ጭካኔ የተሞላበት የሰብዓዊ መብት ረገጣን የማስቆም ምኞታቸውን ለማሳካት በምንችለው መንገድ እንዳቻል ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እየተገናኙ መሆናቸውንም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።

USA | PK Ned Price
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይምስል Manuel Balce Ceneta/AP Photo/picture alliance

ደቡብ አፍሪቃ የሰላም ውይይቱን ማዘጋጀቷን እናደንቃለን ያሉት ኔድ ፕራይስ፣ውይይቱን በማመቻቸት፣የአፍሪቃ ህብረት ከፍተኛ ተወካይ ኦሌሴጉን ኦባሳንጆ፣የቀድሞ የደቡብ አፍሪቃ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ምላንቦ ንጉካ እና የቀድሞ ኬኒያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬኒያታን ለመደገፍ ዝግጁ ነን ብለዋል። ለዚህም የአሜሪካ የአፍሪቃ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣በአፍሪቃ ህብረት የሚመራውን ውይይት፣ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት እና ከምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ ድርጅት ማለትም ኢጋድ ጋር ለመሳተፍና ጦርነቱ በአስቸኳይ እንዲቆም የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ደቡብ አፍሪቃ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ለተቸገሩ ኢትዮጵያውያን ሁሉ ሰብዓዊ ርዳታ ለማድረስ፣ተጨማሪ የሰብዓዊ መብት ረገጣዎችንና አሰቃቂ ድርጊቶችን ለመከላከልና ኤርትራ ከሰሜን ኢትዮጵያ እንድትወጣ ማድረግ ጥቅሞቻችን ናቸው በማለትም ቃል አቀባዩ አስረድተዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ