1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የጀመሩትን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በፍራንክፈርት ሰልፍ ተካሄደ

እሑድ፣ ሐምሌ 15 2010

በፍራንክፈርት እና አካባቢው የሚገኙ በርካታ ኢትዮጵያውያን በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ አህመድ የሚመራው አዲሱ አስተዳደር የጀመረውን የለውጥ እንቅስቃሴ በመደገፍ በፍራንክፈርት ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ አካሂደዋል ::

https://p.dw.com/p/31suG
Deutschland Demonstration von Äthiopiern in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

 ሰልፈኞቹ ከፍራንክፈርት ዋናው የባቡር ጣቢያ ሃብትባኖፍ በመነሳት በአውሮፓ ማዕከላዊ ባንክ አድርገው የቱሪስቶች እና የሙዚየሞች ማዕከል እንዲሁም ቀደምት የከተማዋ አስተዳደር ሕንጻ ወደሚገኝበት ዶም ሮመር በማቅናት ባለፉት 100 ቀናት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት እና በዲፕሎማሲውም መስክ ከጎረቤት ሃገራት በተለይም ከሶማሊያ ሱዳን ከግብጽ እና ኤርትራ ጋር ለበርካታ ዓመታት ሻክሮ የቆየውን ግንኙነት ለማሻሻል ያደረጉትን አበረታች ጥረት በማመስገን የለውጡ አጋዥ መሆናቸውን በዶክተር ዓብይ አገላለጽ ለፍቅር ለአንድነት እና ለሃገር እድገት በጋራ መደመራቸውን ይፋ አድርገዋል :: ሰልፉን ከሌላው ጊዜ ለየት የሚያደርገውኢትዮጵያውያን ሃይማኖት እና ዘር ሳይገድባቸው በነቂስ ወተው የደስታ ስሜታቸውን በጋራ የገለጹበት የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ ደጋፊዎች የሃይማኖት አባቶች እና ኤርትራውያን ጭምር እጅ ለእጅ ተያይዘው ስለ ሰላም ፍቅር እና አንድነት በጋራ የዘመሩበት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው ያሰሙበት ልዩ መድረክ መሆኑ ነው :: የሃገር ባህል ልብሶችን እና የሁለቱ ሃገራት መሪዎች ምስል የታተሙባቸው ቲ-ሸርቶችን የለበሱ በርካታ የሰልፉ ታዳሚዎች በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሰንደቅ አላማዎች ደምቀው ሲታዩ የብዙሃኑን ቀልብ መሳብ ችለዋል:: ሰልፈኞቹ በሚያቋርጡባቸው አደባባዮች ሁሉ ፍቅርን የሚሰብኩ ሃይማኖታዊ መዝሙሮችን ሙዚቃዎችን እና ልዩ ልዩ መፈክሮችን በማሰማትም የተሰማቸውን ፍጹም ደስታ ሲያንጸባርቁ ታይተዋል:: የሰልፉ አዘጋጅ በፍራንክፈርት የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ዋና አስተባባሪ አቶ ሆህተጥበብ ጌጡ ከ20 ዓመታት በፊት ከ70 ሺህ እስከ መቶ ሺህ የሚገመቱ ዜጎችን የቀጠፈው እና ሰላምም ጦርነትም አልባ የነበረው የሻከረው የኢትዮ-ኤርትራ ግንኙነት በርካታ የሰብዓዊ እና የምጣኔ ሃብት ቀውስ ማስከተሉን ጠቅሰው በሁለቱም ሃገራት መሪዎች ጥረት በሰላም እና እርቅ መቋጨቱ እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል :: በኢትዮጵያ ለ 27 ዓመታት ብሄር ተኮር የነበረው የመንግሥት አስተዳደር ለበርካታ ግጭቶች እና ቀውሶች ምክንያት ሆኖ መቆየቱን የሚያስረዱት የሰልፉ አስተባባሪ አዲሱ የጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የለውጥ አስተዳደር ከልዩነት ይልቅ አንድነትን ከጥላቻ ይልቅ ፍቅርን ከግጭት ሰላምን እና የኢትዮጵያን አንድነት ማዕከል አድርጎ መነሳቱ ከዚህም ሌላ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የጀመረው ጥረት የበርካታ ኢትዮጵያውያንን ትኩረት እና አድናቆት ሊስብ በመቻሉ በጀርመን በተለይም በፍራንክፈርት እና አካባቢው የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ለውጡን ለመደገፍ እና ለማገዝ እንዲሁም እስካሁን የተከናወኑ ጥረቶችን ለማመስገን ይህ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ መዘጋጀቱን ተናግረዋል::

Deutschland Demonstration von Äthiopiern in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade
Deutschland Demonstration von Äthiopiern in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

ሰልፈኞቹም በኢትዮጵያ ተከስቶ የነበረው አስፈሪ ፖለቲካዊ ቀውስ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ የለውጥ አራማጅ ቡድን ባደረገው ፈጣን እና ቀና ርብርብ ተሻሽሎ መታየቱ ለዲሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት መከበር የተደረገው ትግል ፍሬ እያፈራ መምጣቱ እንዲሁም ኤርትራን ጨምሮ ከሌሎችም ጎረቤት ሃገራት ጋር ሰላም እና የኢኮኖሚ ውህደትን ለመፍጠር ባለፉት ሶስት ወራት የተደረጉ ለውጦች እና እንቅስቃሴዎች አበረታች መሆናቸውን ነው የገለጹት :: አዲሱ የመንግስት አስተዳደር ከጀመረው ፈጣን የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ ማሻሻያ እርምጃዎች ጎን ለጎን በቀጣናው ሰላምን ለማስፈን በጀመረው ጥረት በተለይም በኢትዮ-ኤርትር ጦርነት ምክንያት ከ20 ዓመታት በላይ ተለያይተው የቆዩ ቤተሰቦችን ለማገናኘት የተካሄደው ጥረት እንዲሁም በሃገራቱ መካከል የተጀመረው የዲፕሎማሲ የወደብ አጠቃቀም ስምምነት የንግድ ዝውውር እና የምጣኔ ሃብት እንቅስቃሴም በመላው ምሥራቅ አፍሪቃ ምሳሌ እና ታላቅ እመርታን የሚያመጣ በመሆኑ ጥረቱን ከልብ እንደሚደግፉ ነው ያነጋገርናቸው ሰልፈኞች የጠቀሱልን :: ጠቅላይ ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቀነስ በዲያስፖራ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሃገሪቱ በሚካሄደው የልማት የማህበራዊ ኢኮኖሚያዊ እና የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ንቁ ተሳታፊ በመሆን አጋርነታቸውን እንዲያሳዩ ገንዘብ በህጋዊ የሐዋላ አገልግሎት በመላክ እንዲጠቀሙ እንዲሁም የውጭ ምንዛሪ ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል :: የፍራንክፈርት ሰልፈኞችም በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ የገጠማትን የውጭ ምንዛሪ እጥረት ለመቅረፍ እንዲያስችል እና የተጀመረውን የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማጠናከር በሙያቸው እና በአቅማቸው አስፈላጊውን ድጋፍ እናደርጋለን ብለዋል ::

Deutschland Demonstration von Äthiopiern in Frankfurt
ምስል DW/E. Fekade

በጀርመን ፍራንክፈርት ከተማ በደማቅ ሁኔታ የተከናወነውን ሰልፍ ያዘጋጀው የኢትዮጵያውያን የውይይት እና የትብብር መድረክ ከአሁን ቀደምም በኦሮምያ እና በአማራ ክልሎች በዘር ግጭት ምክንያት ለተፈናቀሉ ወገኖች መርጃ ከ 25 ሺህ ዩሮ በላይ በማዋጣት መለገሱ ይታወቃል :: በቅርቡም አጼ ቴዎድሮስ ከወራሪው የእንግሊዝ ጦር ጋር ተፋልመው መቅደላ ላይ የተሰውበትን 150 ኛ ዓመት ምክንያት በማድረግ በምህረት ከእስር የተለቀቁት አቶ አንዱ ዓለም አራጌ የንጉሰ ነገስት አጼ ቴዎድሮስ የልጅ ልጆች እና ቤተሰቦች ታዋቂ ምሁራን እና የፍራንክፈርት ነዋሪዎች የተሳተፉበት ዝክረ-ፕሮግራም በተጨማሪም በተለያዩ የጀርመን ከተሞች የሥነጥበብ እና የውይይት መድረኮችን በማዘጋጀት አድናቆት አትርፏል ::

እንዳልካቸው ፈቃደ