1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጎርጎሪዮሳዊው 2020

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 20 2013

ጎርጎሪዮሳዊው 2020 ዓ,ም ሊሰናበት በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል። ከዚህ ዓመት ሌላ የሰዎች ሕይወት ላይ እንዲህ ያለው ከባድ ጫና ያሳደረ ወቅት ለመጥቀስ ይቻል ይሆን?

https://p.dw.com/p/3nL2V
BdTD China Hongkong Virenschutz aus Plastikflasche
ምስል AFP/A. Wallace

«ዓመቱ ሲቃኝ»

በደቡባዊ ንፍቀ ክበብ ከሚገኙት ሃገራት አውስትራሊያ ተሰናባቹን ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት 2020ን በሰደድ እሳት ታጅባ ነበር የተቀበለችው። ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ከጎርጎሪዮሳዊው 1990 ዓ,ም ጀምሮ በተለያዩ ጊዜያት አውስትራሊያ ውስጥ ከተከሰቱ አውዳሚ ሰደድ እሳቶች በዚህ ዓመት የደረሰው በብዙ እጥፍ ይበልጣል። በመጋቢት  ወር ብቻ እሳቱ ያዳረሰው 186 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር እንደሆነም ተመዝግቧል። ለተደጋጋሚ የሰደድና እሳትና የደን ቃጠሎ የምትጋለጠው አውስትራሊያ በተመዘገበው ታሪኳ መሠረት በጎርጎሪዮሳዊው 2020 የገጠማትን አይነት የዝናብ እጥረትና ድርቀት አይታ አታውቅም። አውስትራሊያ ለሰደድ እሳት እንግዳ ባትሆንም በዚህ ዓመት ግን ደረቃማው የአየር ጠባይ እሳቱን እንዳባባሰው ተነግሯል። 80 ቀናት በፈጀው የደን ቃጠሎም ወደ ሦስት ቢሊየን የሚሆኑ እንስሳት ከየሚኖሩበት ተሰድደዋል ወይም አልቀዋል፣ እጅግ ከፍተኛ የብዝሀ ሕይወት ውድመትም ሀገሪቱ አጋጥሟታል። የአሜሪካዋ ካሊፎርኒያ ግዛትና አጎራባቾቿ፣ የአማዞን ደን መገኛ ብራዚልና ጎረቤቷ ጓቲማላ በተሰናባቹ ዓመት ከባድ የእሳት ቃጠሎ ካጋጠማቸው ተርታ ናቸው። ከአውሮጳም ግሪክና ፈረንሳይ ከደረቁ የአየር ጠባይ ጋር በተገናኘ እሳት ሲያጠፉ ነው ያሳለፉት፤ ከእስያም እነፊሊፒንስ፣ ጃፓን፣ ባንግላዴሽና ኢንዶኔዢያም ከባድ ውሽንፍር የቀላቀለ ዝናብ ቀላል የማይባል ጉዳት ካደረሰባቸው ሃገራት ውስጥ ይጠቀሳሉ። ለፊሊፒንስ ከማዕበልና ውሽንፍሩ ሌላ የፈነዳው እሳተ ጎሞራም በዚህ ዓመት ሌላው የማይዘነጋ ክስተት ነው። አፍሪቃ ውስጥም ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍ ኢትዮጵያን ጨምሮ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን እና ኬንያ ለከባድ ጎርፍ መዳረጋቸው ይታወሳል። ከዚህም ሌላ በዚሁ ዓመት ተጠናክሮ የታየው የበረሃ አንበጣ ወረራ በበርካታ ሃገራት በተለይም በአፍሪቃ ቀንድ  የምግብ እጥረት ሊያስከትል ይችላል የሚለው ስጋትም ተሰምቷል። የአንበጣ መንጋው በኬንያ፣ ዩጋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኤርትራ፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፤ ኢራን፣ የመን፤ ኦማንና ሳውድ አረቢያ ተከስቷል። ከ10 ሃገራት ጋር ተቀናጅቶ ከ1,3 ሚሊየን ሄክታር መሬት በላይ በአንበጣ የተወረረ አካባቢ ላይ የመከላከል ሥራ ሲሠራ መሰንበቱንም የዓለም የምግብና የእርሻ ድርጅት ተገልጿል። በዚህ የመከላከል ሥራም በተለይ በምግብ ዋስትና ከፍተኛ ችግር ባለባቸው ሃገራት ለአንድ ዓመት 18 ሚሊየን የሚሆን ሕዝብ ሊመግብ የሚችል 2,7 ሚሊየን ቶን እህል ከአንበጣው ማትረፍ መቻሉንም ዘርዝሯል። ምንም እንኳን የአንበጣ መንጋውን በመከላከል አዎንታዊ ውጤት መገኘቱ ቢገለፅም የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ግን ወረራው ከማያባራው ከዚህ ፀረ ሰብል ጋር የሚደረገው ፍልሚያ አበቃ ማለት እንዳልሆነ አጽንኦት ሰጥተዋል። ባለፈው ሳምንት ረቡዕ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ወጣው መረጃ ደግሞ በቀጣይም በአፍሪቃው ቀን አካባቢ የአንበጣ ክምችት መኖሩንና ይክም በእርሻ ምርት ላይ በሚያስከትለው ጉዳት በሚሊየኖች የሚገመት ሕዝብን የምግብ ዋስትና ጥያቄ ላይ እንደሚወድቅ አመልክቷል።

የአፋር ክልሉ ጎርፍ
ምስል Allo Yayo
የካሊፎርኒያው እሳት
ምስል Jae C. Hong/AP Photo/picture-alliance

ኢትዮጵያን በተመለከተ የአንበጣው መንጋ ባለፈው ሳምንት በምሥራቅ እና ደቡባዊ ምሥራቅ ኢትዮጵያ አካባቢዎች መከሰቱን ከግብርና ሚኒስቴር የሚመለከታቸውን በማነጋገር የዶቼ ቬለ ዘግቧል።  በተጠቀሱት አካባቢዎች የተከሰተው አንበጣ በኢትዮጵያ የሶማሌ ክልል እና በሶማሊያ አዲስ ተፈልፍሎ ወደ ኢትዮጵያ የገባ መሆኑ ነው የተገለጸው።

ከዚህም ሌላ ከሰሜናዊ ኬንያ የተነሳ የአንበጣ መንጋም በደቡብ ክልል የኦሞ ወንዝን ተከትሎ በሐመር ወረዳ በሚገኙ 13 ቀበሌዎች ላይ መስፈሩም ተሰምቷል። «ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከቻይና ውጭ በኮቪድ 19 የተያዙት ቁጥር በ13 ከመቶ እጥፍ ጨምሯል። በተሐዋሲው ተፅኖ የገጠማቸው ሃገራትም በሦስት እጥፍ አድገዋል። አሁን በመቶ 114 ሃገራት ውስጥ ከ118 ሺህ የሚበልጡ ተይዘዋል፣ 4,291 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። በሺህ የሚቆጠሩ ደግሞ በሆስፒታል ሕይወታቸውን ለማትረፍ እየታገሉ ነው። በቀጣዮቹ ቀናትና ሳምንታት የሚያዙ ሰዎችም ሆኑ የሟቾች ቁጥር እንዲሁም ተሐዋሲው የሚያዳርሳቸው ሃገራት ከዚህ ከፍ እንደሚሉ እንገምታለን። WHO ሁኔታውን በየሰዓቱ እየተከታተለ ሲሆን በስርጭቱና በአስከፊነቱና ለመከላከል ጥረት ባለመደረጉ ጥልቅ ስጋት ገብቶታል። ካካሄድነው ቅኝት በመነሳትም ኮቪድ 19 ወረርሽኝ ተብሎ ሊፈረጅ እንደሚችል አስተውለናል።»

አንበጣ በሐረርጌ
ምስል Mesay Tekelu/DW

ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር ባለፈው መጋቢት ወር ላይ ከቻይና መነሳቱ የሚነገርለት ኮቪድ 19 አሳሳቢ ወረርሽኝ መሆኑን ለመላው ዓለም ያወጁበት መልእክት ነው። ከሰው ወደ ሰው በፍጥነት መዛመቱ የታወቀው ኮሮና ተሐዋሲ የካቲት ወር ላይ በቻይና ተወስኖ ይቀራል የሚል ግምት የነበራቸው ጥቂት አልነበሩም። እናም ጥረቱ ሁሉ የመጀመሪያው ታማሚ ወይም በህክምናው ፔሸንት ዚሮ የሚባለውን መፈለጉ ላይ ትኩረት ተደርጎ ነበር። ደቡብ ኮርያ ላይ 31ኛው በተሐዋሲው የተያዘ ሰው ከተመዘገበና ይኽ ግለሰብም ቢያንስ ከ1,160 ሰዎች ከሚበልጡ ሰዎች ጋር ሳይነካካ እንዳልቀረ ሲነገር ግን ጉዳዩ ለመላው ዓለም የማስጠንቀቂያ ደውል መሰለ። ዋል አደር አለናም  የቻይናን ድንበር አልፎ በሌሎች ሃገራት በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር በገፍ ይዘገብ ጀመር። የመገናኛ አውታሩንም ቀልብ ወሰደው። ከዚያም በየዕለቱ በተሐዋሲው የተያዙና በዚህም ሕይወታቸው ያለፈ ሰዎች ቁጥርን የሚመለከተው ዜና ግንባር ቀደም ሆነ። በተለይም አውሮጳ ውስጥ ቱሪስቶች የሚያዘወትሯቸው የጣሊያን እና ስፔን ግዛቶች በከፍተኛ ፍጥነት የሰው ልጅ እንደቅጠል መርገፉ ተመዘገበባቸው። ይኽን ሃገራት የአየርም የየብስም ድንበሮቻቸውን እንዲዘጉ በማስገደዱ በቱሪዝም ዘርፉ ላይ ከፍተኛ ኪሳራ መድረሱ ዛሬም ድረስ እየታየ ነው። ቁጥሩ በየዕለቱ ከፍተኛ ለውጥ ቢያሳይም ዛሬ ባለው መረጃ መሠረት በመላው ዓለም በተሐዋሲው የተያዘው ሕዝብ 81 ሚሊየን 193,995 ደርሷል፤ ከእነዚህ ውስጥ 45 ሚሊየን 917,258ቱ ከህመማቸው አገግመዋል። 1, ሚሊየን 772,325 ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል። በአሁኑ ወቅት በሟቾች ቁጥር ብዛት ዩናይትድ ስቴትስ ቀዳሚ ስትሆን ወረርሽኙ በተከሰተበት ወቅት ክፉኛ የተጎዳችው ጣሊያን ደግሞ በአውሮጳ አሁንም በሟቾች ቁጥር መብለጧ ተመዝግቧል። በተለይም የሰሜኑን ንፍቀ ክበብ የክረምት ወቅት አስታክኮ የተስፋፋው ይኽ ተሐዋሲ ብሪታንያ ላይ አይነቱን ለውጦ መከሰቱ ሌላ ተጨማሪ ስጋት አስከትሏል። ኮቪድ 19 ወረርሽኝ መሆኑ ታውጆ መስፋፋቱን ለመግታት የተደረገው ጥረት የሰዎች እንቅስቃሴና የዕለት ከዕለት ሥራዎች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ አሁን በመላው አውሮጳ ቀጥሏል። በዚህ መሀል የመድኃኒት ኩባንያዎች ለመከላከያ  ይሆናል ያሉትን ክትባት ለማቅረብ ሲጣደፉ የአፍሪቃ ሃገራትን ጨምሮ በባህላዊ መንገድ መድኃኒቱ አለን የሚሉም ብቅ ብቅ አሉ። የማዳጋስካር ፕሬዝደንት ሀገራቸው ፍቱን የኮሮና መድኃኒት በባህላዊ ቅመማ ማዘጋጀቷን ቢያውጁም የዓለም የጤና ድርጅት፤ አፍሪቃ ውስጥ አሉ የተባሉት እንዲህ ያሉት መድኃኒቶች ተፈትነው ደረጃ ሊወጣላቸው እንደሚገባ አሳስቧል። ኢትዮጵያም ወረርሽኙ ወደ ሀገር መግባቱ በይፋ በተነገረ ሰሞን መድኃኒቱን ለማቅረብ ዝግጅት ላይ መሆኗ ቢነገርም ከአንድ መግለጫና መድረክ ሳይዘል በዚያው የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል። ኢትዮጵያ ውስጥ በተሐዋሲው የተያዙት ቁጥር እስከ ትናንት 123,145 ሲሆኑ ከ109 የሚበልጡት ማገገማቸውን የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል። 1,912 ደግሞ ሕይወታቸውን አጥተዋል። የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ዕለት በማኅበራዊ መገናኛ ገጻቸው የፅኑ ሕሙማን መታከሚያ ክፍሎች መጣበባቸውን በመጠቆም ዜጎች ራሳቸውን ከተሐዋሲው ለመከላከል ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ እንዳይዘናጉ መክረዋል።

Spanien | Coronavirus | Impfstart
ምስል Alvaro Calvo/Government of Aragon/Getty Images
ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም የዓለም የጤና ድርጅት ዳይሬክተር
ምስል Christopher Black/WHO/AP/picture alliance

ወደ አውሮጳ ስንመለስ ካለፉት ሁለት ሳምንታት ወዲህ እውቅና ያገኙት ክትባቶች ይሰጡ ጀምሯል። ቀዳሚዋ ብሪታንያ  ስትሆን ለተሐዋሲው ይበልጥ የተጋለጡ ለተባሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያዳረሰች ነው። በአውሮጳ ሕብረት አባል ሃገራት ደግሞ ከትናንት በስተያ አንስቶ ክትባቱ ቀርቧል፤ መሰጡትም ተጀምሯል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ኅብረተሰቡ ኮቪድ 19 ከወትሮው እንቅስቃሴው የሚያግደው እንቅፋት በመሆኑ የሚገላገልበትን መፍትሄ የመሻቱን ያህል ለመከተብ ያሳየው ተነሳሽነት ሌላ ስሜት ፈጥሯል። ላለ መከተብ ከሚያንገራግሩት አንዳንዶች የክትባቱ ፈጥኖ መድረስ ፍቱንነቱን እንዲጠራጠሩ ሲያደርጋቸው በሌላ ወገን በሰው ዘረመል ላይ ይፈጥራል በሚል የሚናፈሰው ለውጥ ስጋት እንደሆነባቸው መናገራቸውን የጀርመን የሀገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን መወያያ አድርገውታል። አንዳንዶች ከዚህ አልፈውም ዓለም እንደሳምባ ምች ማለትም ኒሞኒያ ያሉ ብዙም ሳይወራላቸው በመቶ ሺህዎችን የሚፈጁ በሽታዎችን ተቋቁሞ ኖሯልና ኮቪድ 19 ተሐዋሲንም ከመሸሽ ይልቅ ብንላመደው ሰውነታችን ራሱን የመከላከያ ዘዴ ሊገነባ ይችል ነበር ሲሉም ይሞግታሉ። ያም ሆነ ይህ ወረርሽኙ ዓመቱን እንዳጠላበት ለቀጣዩ 2021 ሊያስረክብ ተቃርቧል።  ስሙን አግንኖና ሰዎችን ስጋት ውስጥ የከተተው ይህ ወረርሽኝ በቀጣዩ ዓመት የት ይሄድ ይሆን የሚለውን ለማየት ዕድሜ በመመኘት እናብቃ። እናንተም በያላችሁበት ተገቢውን ጥንቃቄ ከማድረግ አትዘናጉ።

ሸዋዬ ለገሠ

ማንተጋፍቶት