1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግጭት ራስን በምግብ መቻል ላይ ተጽዕኖ አሳርፏል ተባለ

ሰኞ፣ ጥቅምት 24 2012

በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና መፈናቀሎች ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል ባስቀመጠችው ውጥን ላይ ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ዛሬ ለ«DW» እንደተናገሩት በግጭት ምክንያት አርሶ አደሮች ከማምረት ስራቸው ከመስተጓጎላቸው አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል።

https://p.dw.com/p/3SRWL
Äthiopien Addis Abeba | Konferenz Hunger Zero Program
ምስል DW/S. Muchie

ግጭቶች ራስን በምግብ መቻል ላይ ተጽዕኖ አሳርፈዋል ተባለ

በኢትዮጵያ እየተከሰቱ ያሉ ግጭቶች እና ያንን ተከትሎ የሚመጡት መፈናቀሎች ሀገሪቱ በምግብ ራስን ለመቻል ባስቀመጠችው ውጥን ላይ  ተጽዕኖ እያሳደረ እንደሚገኝ የብሔራዊ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ገለጸ። ኮሚሽነር ምትኩ ካሳ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW) እንደተናገሩት በግጭት ምክንያት አርሶ አደሮች ከማምረት ስራቸው ከመስተጓጎላቸው ባሻገር የኢትዮጵያ መንግስት ለሌላ ስራ ማዋል የሚገባውን በጀት ለእርዳታ በማዋሉ አሉታዊ ተጽዕኖ አሳርፏል ብለዋል። 

ከሰሞኑ በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተውን ሁከት ተከትሎ ኮሚሽኑ ከኦሮሚያ ክልል በቀረበለት ጥያቄ መሰረት በሁለት ቦታዎች እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ አቶ ምትኩ ተናግረዋል። መስሪያ ቤታቸው በዶዶላ ለ3366 ሰዎች፣ በሰበታ ደግሞ ለ1100 ሰዎች እርዳታ እያደረገ እንደሚገኝ ያብራሩት ኮሚሽነሩ “በሌሎች ቦታዎች ጥያቄዎች አልቀረቡልንም” ብለዋል። ለተፈናቃዮች እየቀረበ የሚገኘው እርዳታ “የህግ የበላይነትን በማስከበር ዜጎች ወደ ቀደመ ቦታቸው እስኪመለሱ ባሉበት ይቀጥላል” ሲሉም አስረድተዋል።

Karte Dodola Ethipia AM

በኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት 7.8 ሚሊዮን ዜጎች አስቸኳይ የእለት ደራሽ እርዳታ እንደሚቀርብላቸው የጠቀሱት ኮሚሽነር ምትኩ የፌደራል መንግስት በየአመቱ ለእርዳታ ከ8 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል። “ኢትዮጵያ ውስጥ አሁን ረሃብ የለም” የሚሉት አቶ ምትኩ “ረሃብ የሚመጣው ምላሽ ሳይሰጥ ሲቀር ነው” ሲሉ ለዶይቼ ቬለ  ተናግረዋል። በኢትዮጵያ ለተረጂዎች ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎች በመንግስት በኩል እየቀረበ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ በድርቅ በየ10 አመቱ ስትጠቃ እንደነበር የገለጹት ኮሚሽነሩ አሁን ግን ከአየር ንብረት ለውጡ ጋር ተያይዞ በየአመቱ እየተከሰተ መሆኑን አመልክተዋል። “ሃገሪቱ በዚህ ሁኔታ ልትቀጥል አይገባም” ያሉት አቶ ምትኩ “እርዳታ እያቀረብን ስለማንቀጥል የተሻለ አሰራር በመዘርጋት ችግሩን ለመከላከል መጣር ይኖርብናል” ብለዋል። 
ረሃብን ማጥፋት በዓለም አቀፍ ደረጃ የምዕተ አመቱ የልማት ግብ ውስጥ ከተካተቱ እቅዶች አንዱ ነው። ኮሚሽነር ምትኩ የተሳተፉበት፤ ይህንኑ ለማሳካት የሚረዳ አለም አቀፍ ውይይት ዛሬ በአዲስ አበባ ተደርጓል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሰለሞን ሙጬ 

ተስፋለም ወልደየስ
ነጋሽ መሐመድ