1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግዙፍ የሥዕል ዓዉደ ርዕይ በአዲስ አበባ

ሐሙስ፣ ጥር 12 2014

የሰዉ ልጅ የዕይታ ስርዓት፤ የዕይታ ባህል፤ ካላደገ፤ ከተማ አይፀዳም። የማስታወቅያ፤ የኪነ-ሕንፃ የመሳሰሉት የትኛዉም እይታዊ ጥበብ ጉዳይ አያድግም። ስለዚህ የሰዉ ልጅ  የዕይታ ስርዓት፤ የዕይታ ባህል እንዲያድግ፤ ሥነ-ጥበብ በጣም ጠቃሚ ነዉ። የሰዉ ልጅ ዓይን መሰልጠን አለበት፤ በሥርዓተ ትምህርታችን ሥነ-ጥበብ፤ ሥነ ስዕል፤ ማካተት አለበት።

https://p.dw.com/p/45qoM
Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

ሥርዓተ ትምህርታችን ሥነ-ጥበብን፤ ሥነ-ስዕልን፤ ማካተት አለበት

«የሰዉ ልጅ የዕይታ ስርዓት፤ የዕይታ ባህል፤ ካላደገ፤ ከተማ አይፀዳም። የማስታወቅያ፤ የኪነ-ሕንፃ የመሳሰሉት የትኛዉም እይታዊ ጥበብ ጉዳይ አያድግም። ስለዚህ የሰዉ ልጅ የዕይታ ስርዓት፤ የዕይታ ባህል እንዲያድግ፤ ሥነ-ጥበብ በጣም ጠቃሚ ነዉ። የሰዉ ልጅ ዓይን መሰልጠን አለበት፤ ስለዚህ ሥርዓተ ትምህርታችን ሥነ-ጥበብን፤ ሥነ-ስዕልን፤ ማካተት አለበት። » ያሉን በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር የሚገኘዉ የአለ የጥበብና ዲዛይን ተቋም ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ ናቸዉ።

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

ጥር 3 ቀን 2014 ዓ.ም ማክሰኞ አዲስ አበባ ላይ በሚገኘዉ በግዙፍ «የእንጦጦ የሥነ-ጥበብ ማዕከል» ከሁለት መቶ በላይ የሥነ-ጥበብ ባለሞያዎች ሥራዎቻቸዉን ለዕይታ አቅርበዋል። ለአንድ ወር የሚዘልቀዉ ዓዉደ ርዕይ የሚገኘዉ በእንጦጦ የሥነ-ጥበብ ማዕከል፤ በእንጦጦ ተፈጥሮዋዊ ፓርክ ዉስጥ ነዉ። ወደ ሁለት መቶ ሃያ ገደማ የሚሆኑ አንጋፋና ወጣት የጥበብ ባለሞያዎች በማዕከሉ ለእየታ ያቀረቡዋቸዉ የስዕል ሥራዎች በቁጥር 500 እንደሆነም ተነግሮአል። በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ይህ አይነት ግዙፍ የሥዕል እና የቅርፅ አዉደ ርዕይ በእንዲህ አይነት መልኩ ሲቀርብ ምናልባትም በኢትዮጵያ ታሪክ የመጀመርያ እንደሆነ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ስር የሚገኘዉ የአለ የጥበብና ዲዛይን ተቋም ዳይሬክተር አቶ አገኘሁ አዳነ ተናግረዋል።

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

« እንጦጦ የሥነ-ጥበብ ማዕከል አዲስ የጥበብ ማሳያ አዳራሽ «ጋለሪ» ነዉ። እንደሚታወቀዉ በኢትዮጵያ የሥነ-ጥበብ ታሪክ የሕዝብ ጋለሪ ኖሮን አያዉቅም። እግዚቢሽኑ  ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የተከፈተ፤ ከስዕል ለመለማመድ፤ ከስልል ለመማር፤ ከስዕል ባህል አንዳች ቁም ነገር ለመማግኘት የሚፈልግ ሁሉ በነፃነት የሚገባበት ቦታ ነዉ። በዚህ ሕዝብ የሥነ-ጥበብ ማዕከል፤ ከፍተኛ የሥነ ጥበብ ትምህርት እና ልምድ ካለዉ፤ እስከ ጀማሪ፤ ወጣኒ፤ እስከሚባለዉ ድረስ ከ 210 በላይ ሰዓልያን በዚህ ኤግዚቢሽን ተሳትፈዉበታል። ዓዉደ ርዕዩ ሲከፈት አላማዉ ያደረግነዉ፤ ጥሪ የተደረገላቸዉ ኢትዮጵያዊ ወገኖቻችን እና ኢትዮጵያን ወዳጅ የሆኑ ሰዎች መጥተዉ፤ በዚህ በሥነ-ጥበብ ሥራ ኢትዮጵያ ያለችበትን ዘመን ሁኔታ፤ ብሎም የዘመን መንፈስ እንዲረዱ፤ ሥነ-ስዕል አንድ አጋዥ ጉዳይ ነዉ በሚል ያዘጋጀነዉ ኤግዚቢሽን ነዉ።  በጎርጎረሳዉያኑ 2020 የተመረቀዉ ግዙፉ የሥነ ጥበብ ማዕከል ደግሞ ለሁሉም የሥነጥበብ ሞያተኞች እድል የሚፈጥር ቦታ መሆኑ የማስተዋወቅ ፤ የመጀመርያ ሙከራ የተደረገበት ዝግጅት ነዉ።»  

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU
Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

በእንጦጦ የሥነ-ጥበብ ማዕከል ውስጥ ለአንድ ወር የተከፈተዉ ይህ የሥዕል ኤግዚቢሽን በአለ የሥነ-ጥበብ ት/ቤትና በተዋነይ ስቱዲዮ ትብብር ለእይታ የቀረበ መሆኑን አቶ አገኘሁ አዳነ ተናግረዋል። የስልዕ ኤግዚቢሽኑ ቦታ ሰፊ መሆኑ ብቻ ሳይሆን ፤ ወጣት ሰዓሊያን እየበዙ በመጡባት ኢትዮጵያ ሞያተኛዉ ሞያዉን የሚያስተዋዉቅበት ብሎም የሌላዉንም ልምድ የሚገመግምበት እና ትምህርት የሚቀስምበት ነዉ ያሉን የስዕል አዉደ ርዕዩ አስተባባሪ፤ ማለትም ኤግዚቢሽኑን ኩሬት (curate) ያደረጉት ሠዓሊ ጌታ መኮንን ናቸው።

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

« እንጦጦ ላይ የተከፈተዉ ጋለሪ ግዙፍ ነዉ። ለብዙ ዓመታት እንዲህ ትልቅ የሆነ እና ለጥበቡ ቤተሰብ ክፍት የሆነ አዳራሽ አልነበረንም። ይህ የመጀመርያዉ ቦታ ነዉ። እንደሚታየዉ ኢትዮጵያ ዉስጥ የሰዓሊዉ ብዛት እየጨመረ ነዉ። ብዙ ወጣት ሰዓልያን አሉ።  ኤግዚቢሽኑ የሚገኘዉ ጥበበኞች ስራቸዉን የሚያቀርቡበት፤ ቦታዉ በጣም ብዙ ሰዉ የሚጎበኘዉ ነዉ። ብዙ ቦታ የዚህን ያህል የተመልካች ፍሰት የለዉም። በኤግዚቢሽኑ ላይ የቀረቡት በአብዛኛዉ የቀለም ቅብ ሥራዎች ናቸዉ። የተወሰኑ የቅርፃ-ቅርስ ሥራዎች አሉበት። የተወሰኑ የሐዉልት ስራዎችም አሉ። አብዛኛዉ ግን የቀለም ቅብ ሥራዎች ናቸዉ።» 

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

በኢትዮጵያ የሚገኙ ሠዓሊዎች ሞያቸዉን ሊተገብሩ የሚችሉበት ቦታ ችግር እንዳለ፤ ለሥዕል ግብአት የሚሆን ቁሳቁን ማግኘት ችግር እንደሆነባቸዉ ይናገራሉ።  በአሁኑ ጊዜ ይህ ሁኔታ ተሻሽሎ ይሆን ለሚለዉ ጥያቄ፤ ሠዓሊ ጌታ መኮንን በመቀጠል፤

« እዉነት ለመናገር የመስርያ ቦታ አሁንም ችግር ነዉ። በኢትዮጵያ እንደ ሌላዉ ዓለም አይደለም። ወጣት ሠዓልያን ግን እየተሰባሰቡ አንድ ላይ ቤት እየተከራዩም ቢሆን ጥበብን እንዲያብብ እየታገሉ ነዉ።  ወጣቶች ሞያቸዉን ለማዳበር የሚያደርጉት ትግልና ልፋት ግን የሚደነቅ ነገር ነዉ።»

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

በእንጦጦ ፓርክ ውስጥ የሚገኘዉ የእንጦጦ የሥነ-ጥበብ ማዕከል በአለ የሥነጥበብ ት/ቤትና በተዋነይ ስቱዲዮ ትብብር ለእይታ የቀረበዉ ግዙፉ የሥዕል ኤግዚቢሽን፤ በዉጭ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን እና ትዉልደ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሃገራቸው ለበዓል መምጣትን ምክንያት በማድረግ የተዘጋጀ ልዩ አግዚቢሽን እንደመሆኑ በኮሮና እና በሃገሪቱ ሰሜናዊ ክፍል የተከሰተዉን ጦርነት የተፈጠረውን ሁኔታ፤ የተዳከመውን የጥበብ ቤተሰብ ለማነቃቃት እድሉን የሚፈጥር መድረክ ነዉ። ኤግዚቢሽኑ ብዙዎች እንዲሳተፉበት እድሉን የሰጠ ሲሆን የብዙ ጎብኝዎችን ቀልብ የሳበ እንደሆነም ተመልክቶአል። ለኤግዚቢሽን የቀረቡት ስራዎች፣ በመጠን፣ በቴክኒክና በሃሳብ የተለያዩ እንደመሆናቸው መጠን የኤግዝቢሽኑን ውበትና ሚዛን በጠበቀ መልኩ አዘጋጆቹ (የኤግዚቢሽኑ ደራሲዎች) curators, ብዙ ሰዓታትን ወስደው ይህን ትልቅና አስደማሚ ኤግዚቢሽን ማቅረባቸዉ ተነግሮላቸዋል። ለአንድ ወር የሚዘልቀዉ ዓዉደ ርዕይ ከሰኞ በስተቀር፣ ዘወትር ከጠዋቱ 3 ሰዓት እስከ 10 ሰዓት ክፍት ነው። እስከ ጥር 29 ቀን እንደሚዘልቅም ተመልክቶአል።

Addis Art Show at Entoto park Gallery
ምስል School of Art and Design/AAU

ቃለ ምልልስ የሰጡን በዶቼ ቬለ ስም እያመሰገንን፤ ሙሉዉን ዝግጅት የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን!

አዜብ ታደሰ

ሸዋዬ ለገሠ