1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ግብጽና ሱዳን "ውጤት" ለሚያመጣ ድርድር እንዲዘጋጁ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ

እሑድ፣ ነሐሴ 8 2014

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ "ዩኒት 9" ተርባይን የተሳካ ፍተሻ እና ሙከራ ተጠናቆ 375 ሜጋ ዋት ኃይል ማመንጨት ጀምሯል። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ "የታችኛው ተፋሰስ አገራት በድርድር እና በስምምነት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ከልብ አምነው ለዚያ እንዲተጉ" ጥሪ አስተላልፈዋል። ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል 750 ሜጋ ዋት ደርሷል

https://p.dw.com/p/4FPvS
Äthiopien Guba | Grand-Ethiopian-Renaissance-Talsperre
ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግብጽ እና ሱዳን በታላቁ ኅዳሴ ግድብ ረገድ "በስምምነት ውጤት" ለሚያመጣ ድርድር እንዲዘጋጁ ጥሪ አስተላለፉ። የግድቡ ሁለተኛ ተርባይን ዛሬ ሐሙስ በይፋ ኃይል ማመንጨት መጀመሩን ለማብሰር በተዘጋጀ መርሐ ግብር ላይ ባሰሙት ንግግር ዐቢይ ከድርድር ውጪ ያለ አማራጭ የተጀመረውን "የማያስቆም፤ በከንቱ የሚያደክም" እንደሚሆን ገልጸዋል። 

በመርሐ ግብሩ ላይ ፕሬዝደንት ሣህለ ወርቅ ዘውዴ፣ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ፣ ምክትል ጠቅላይ ምኒስትር ደመቀ መኮንን እና የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ምክትል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል አበባው ታደሰን ጨምሮ ከፍተኛ የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ተገኝተዋል። 

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በዐባይ ወንዝ ላይ የሚገነባው የታላቁ የኅዳሴ ግድብ "ዩኒት 9" ተርባይን "የተሳካ ፍተሻ እና ሙከራ ተጠናቆ" የሚያመነጨው ኃይል ወደ ብሔራዊ ኃይል ቋት መግባቱን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አረጋግጧል። ዛሬ በይፋ ሥራ የጀመረው ዩኒት 9 ተርባይን የሚያመነጨው 375 ሜጋ ዋት ነው። በግድቡ ከተገጠሙ ተርባይኖች ኃይል በማመንጨት ቀዳሚው ዩኒት 10 በተመሳሳይ 375 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ያመነጫል። 

አጠቃላይ ግንባታው ከ83 በመቶ በላይ የደረሰው የታላቁ የኅዳሴ ግድብ የኃይል ማመንጫ ከሁለት እስከ ሁለት ተኩል ባሉ ዓመታት ውስጥ "ግድቡን ሙሉ በሙሉ በማጠናቀቅ በየደረጃው ሙሌት በማከናወን፣ ቀሪ ዩኒቶችን" ለመትከል መታቀዱን ሥራ አስኪያጁ ክፍሌ ሖሮ (ኢንጂኔር) ዛሬ በጉባ በተካሔደው መርሐ ግብር ላይ ተናግረዋል። ኢንጂኔር ክፍሌ ሖሮ የሲቪል ሥራዎች ወደ 95 በመቶ የኤሌክትሮ ሜካኒካል ፍብረካ እና ተከላ 61 በመቶ መድረሱን ገልጸዋል። የውኃ ማስተላለፊያ የብረታ ብረት ሥራዎች በአንጻሩ ወደ 73 በመቶ ከፍ ብሏል። 

የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድን ወደ መድረኩ ከመጋበዛቸው በፊት ባሰሙት ንግግር ያለፉት ሁለት ዓመታት የታላቁ የኅዳሴ ግድብ ግንባታን "ለማሰናከል ከፍተኛ ርብርብ የተደረገበት ወቅት" እንደነበር ገልጸዋል።  "ሥራው በዚህ ፍጥነት እንዳይከናወን ከፍተኛ ተግዳሮቶች ገጥመውን ያቃሉ" ያሉት ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ በበኩላቸው "መስዋዕትነት ተከፍሎ ያቃል። የጸጥታ ተቋማት ብዙ ዋጋ ከፍለዋል" ሲሉ ተደምጠዋል። 

BG Staudämme und Folgen | Grand Ethiopian Renaissance Dam
ግድቡ የሚያመነጨው ኃይል 750 ሜጋ ዋት ደርሷልምስል AMANUEL SILESHI/AFP/Getty Images

በመከናወን ላይ የሚገኘው የግድቡ 3ኛ ዙር ውኃ ሙሌትን በመቃወም ግብጽ ባለፈው ሐምሌ 2014 ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ጥበቃው ምክር ቤት ተቃውሞ አቅርባለች። በዚሁ መቃወሚያ የኢትዮጵያ "የአንድ ወገን እርምጃ ወደፊት ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ" ማስወገድን ጨምሮ ብሔራዊ ደህንነቷን ለመጠበቅ "ሕጋዊ መብት" እንዳላት የግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል። ግብጽ ለጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ አቤቱታ ያስገባችው የኢትዮጵያ መንግሥት የግድቡ ሶስተኛ ዙር የውኃ ሙሌት እንደሚቀጥል ካሳወቀ በኋላ ነው።

ጠቅላይ ምኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን በዛሬው ዕለት ባደረጉት ንግግር ግብጽ እና ሱዳን "በስምምነት ውጤት" ለሚያመጣ ድርድር እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል። በከፍተኛ ግፊት ከግድቡ የሚፈሰው ውኃ "አንድም ቀን ሳይቋረጥ እንዲሔድ የተደረገበት ዋንኛው ዓላማ ሌሎች ወንድሞቻችንን የመጉዳት ሳይሆን" ኢትዮጵያን ያላትን "የማደግ ፍላጎት ለማሳየት የተደረገ" እንደሆነም አስረድተዋል።

"እየፈሰሰ ያለው ውኃ ቢገደብ ባጠረ ጊዜ ውስጥ ውኃ ሊይዝ ይችላል" ያሉት ዐቢይ "ለእነሱ የሚገባቸውን እየለቀቅን እኛ በረዘመ ጊዜ ውስጥ ውኃ የምንይዘው እነሱም ሳይጎዱ፤ እኛም ሳንጎዳ በጋራ ለማደግ ካለን ፍላጎት መሆኑን ተገንዝበው የታችኛው ተፋሰስ አገራት በንግግር፣ በድርድር እና በስምምነት ውጤት ማምጣት እንደሚቻል ከልብ አምነው ለዚያ እንዲተጉ" የሚል ጥሪ አስተላልፈዋል። ዐቢይ በንግግራቸው እንዳሉት "ከዚያው ውጭ ያለው ማንኛውም አማራጭ የጀመርንውን የማያስቆም፤ በከንቱ የሚያደክም" ነው። 

እሸቴ በቀለ 

ኂሩት መለሰ