1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ከእስር ተለቀቀ

እሑድ፣ ጥቅምት 5 2010

ላለፉት ሶስት ዓመታት በእስር ላይ የቆየው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ዛሬ ከዝዋይ ፌደራል ማረሚያ ቤት ከእስር ተለቀቀ፡፡ ጋዜጠኛው የተለቀቀው ሙሉ የእስር ጊዜውን አጠናቆ ነው፡፡  

https://p.dw.com/p/2lrsB
Temesgen Desalegn freigelassen
ምስል DW/T. Desalegn

ጋዜጠኛ ተመስገን የእስር ጊዜውን የጨረሰው ባለፈው አርብ ቢሆንም ከማረሚያ ቤቱ ኃላፊዎች እንደማይለቀቅ እንደተነገራቸው ቤተሰቦቹ ገልጸው ነበር፡፡ ተመስገንም ይህንኑ በመቃወም ትላንት የረሃብ አድማ አድርጓል፡፡ ጥቅምት 3 ቀን 2010 ዓ.ም መፈታት የነበረበት ጋዜጠኛ ለምን በተባለበት ቀን እንዳልተለቀቀ ከእስር ቤቱ ያገኘውን ምላሽ ዛሬ ለዶይቸ ቬለ እንዲህ ሲል ተናግሯል።

«እነሱ ምንም አይነት ምክንያት የላቸውም፡፡ ፍርድ ቤት ሶስት ዓመት ቢፈርድብህም እኛ ብንፈልግ አስር ዓመት እናቆየሃለን የሚል መልዕክት ለማስተላለፍ ነው ከፍርድ ቤት ትዕዛዝ ውጭ ለሁለት ቀን ያቆዩኝ፡፡ ስትወጣ በሚኖርህ እንቅስቃሴ ላይ ለማሸማቀቅ እና ለማስፈራራት ሆነ ብለው ያደረጉት ሴራ ነው፡፡ ዛሬ ውጣ አሉኝ፡፡ ‘ለምንድነው የምወጣው ሁለት ቀን አልፎኛል’ ብል ‘አይ ጨርስሃል፣  ብትወጣ ይሻላል’ ሲሉኝ ያው እስር ቤት ውስጥ አልወጣም ስለማትል ለቅቄ ወጣሁኝ» ብሏል  ተመስገን፡፡

ጆሮ እና ወገቡን እንደሚያመው የተናገረው ተመስገን "ለጊዜው ህክምና ላይ አተኩራለሁ" ብሏል። ጋዜጠኛ ተመስገን ለእስር የተዳረገው አሁን በህትመት ላይ በሌለው “ፍትህ” ጋዜጣ ላይ ዋና አዘጋጅ በነበረበት ወቅት በጻፋቸው እና ባሳተማቸው ጽሁፎች ከተከሰሰ በኋላ ነበር፡፡ በጋዜጠኛው ላይ የቀረበቡት ክሶች የሀገሪቱን መንግሥት በሀሰት የመወንጀል፣ ስም የማጥፋት፣ የሀሰት ወሬዎች በመዘገብ እና በማሰራጨት የህዝብን አስተሳሰብ ማናወጽ እንደዚሁም ህዝብ እንዲያምጽ በመገፋፋት ግዙፍ ያልሆነ የማሰናዳት ተግባር ፈጽሟል የሚሉ ነበሩ፡፡ የተመስገንን ክሶች ሲመለከት የቆየው ፍርድ ቤት ተመስገንን በአንደኛው ክስ ብቻ ጥፋተኛ ነው ብሎ የሶስት ዓመት እስራት እንደፈረደበት የሚታወስ ነው፡፡ 

ተስፋለም ወልደየስ

ልደት አበበ