1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጊኒ ዎርም እየጠፋ ይሆን?

ማክሰኞ፣ ሐምሌ 10 2010

በጎርጎሪዮሳዊው 1980ዎቹ ዓመተ ምህረት ውስጥ የጊኒ ዎርም በ21 ሃገራት ውስጥ ተስፋፍቶ ይገኝ እንደነበር መረጃዎች ያመለክታሉ። ያኔ በበሽታው የተያዙት ሰዎች ቁጥር 3,5 ሚሊየን ገደማ ነበር። እናም በሽታውን ለማጥፋት ዘመቻ ተጀመረ።

https://p.dw.com/p/31cck
Parasit Guinea-Wurm
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Bazemore

መጥፋቱን ለማረጋገጥ ለሦስት ዓመታት ምንም ታማሚ መገኘት አይኖርበትም

ከብዙ ዓመታት ጥረት በኋላ የዛሬ ሁለት ዓመት ማለትም በጎሪዮሳዊው 2016ዓ,ም ጊኒ ዎርም ወይም የጊኒ ትል በመባል የሚታወቀው በሽታ ከብዙዎቹ አካባቢዎች ጠፍቶ በሦስት ሃገራት ብቻ እንደሚገኝ የሚያመለክቱ መረጃዎች ይፋ ሆኑ። ባለፈው ዓመት ደግሞ በቻድ፣ ኢትዮጵያ እና ደቡብ ሱዳን። በሽታውን የማጥፋት ጥረቱ ቀጥሎም ኢትዮጵያ  ውስጥ ከአንድ ዓመት ከመንፈቅ በፊት በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እጅግ መቀነሱ ተሰማ። በተለይም የጊኒ ትል ተጠቂዎች ቁጥር በከፍተኛ ደረጃ ቀንሶ ጥቂት ሰዎች ብቻ ተጠቂዎች መሆናቸው ሲሰማ፤ ትሉ ከተገኘባቸው 25 ሰዎች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ የቀሩት ሦስት ብቻ መሆናቸው ታላቅ ዜና ሆነ። ቀሪ 16ቱ ቻድ ውስጥ 6ቱ ደግሞ ደቡብ ሱዳን እንዳሉ ነው በወቅቱ የተሰማው።

የበሽታዎች መቆጣጠሪያ ማዕከል መረጃዎች እንደሚሉትም በእዚህ ጊዜ የጊኒ ዎርም ለወትሮው ይገኝባቸው በነበሩ ሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ሆነ እስያ ውስጥ አልታየም። በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ ላለፉት ስድስት ወራት ማለት ነው በሰው ላይ ይህ ትል አልታየም።

ኢትዮጵያ ውስጥ የጊኒ ዎርም ወይም የጊኒ ትልን ፈፅሞ ለማጥፋት በሚደረገው ጥረት ለረዥም ዓመታት በመሳተፍ ላይ የሚገኘው የካርተር ማዕከል ተጠሪ ዶክተር ዘርይሁን ታደሰ ከዚህ ቀደም ለዶይቼ ቬለ በገለፁት መሠረት በሽታው በደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ውስጥ ይገኝ ነበር። በሽታው የሚተላለፈውም የጊኒ ትልን በሚያስከትል እጭ የተበከለ የኩሬ ውኃ በመጠጣት መሆኑንም ዘርዝረዋል። የዓለም የጤና ድርጅት መረጃዎች እንደሚጠቁሙት በጎርጎሪዮሳዊው 2017 ኢትዮጵያ ውስጥ በ5 የተለያዩ መንደሮች በሽታው የተገኘባቸው 15 የሚሆኑ ሰዎች መኖራቸው ተመዝግቧል። በዚያም ላይ 4 የጊኒ ትል የተገኘባቸው ዝንጀሮዎች እንዲሁም 11 ውሾች መኖራቸውንም ዘርዝሯል። ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ላይ የወጣው መረጃ ደግሞ ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ጎርጎሪዮሳዊ ዓመት የጊኒ ዎርም ሰዎች ላይ እንዳልተገኘ፤ ሆኖም ግን ዘጠኝ የሚሆኑ ውሻዎች በሽታው እንደተገኘባቸው ያመለክታል። በጤና ጥበቃ ሚኒስቴር የጊኒ ዎርም መከታተያ ዘርፍ ኦፊሰር መሆናቸውን የገለፁልን ወ/ሪት መቅደስ ንጉሤም ይህንኑ ያረጋግጣሉ።

«ያው እስካሁን ድረስ በ2015/17 አስራ አምስት የሚሆኑ የሂውማን ኬዝ ዘገኝቷል። እናም በ2018 እስከ ጁን ድረስ ምንም ዓይነት የሰው ኩዝ የለም ወደ ዘጠን የሚጠጉ የዶግ ኢንፌክሽን አሉ እኔ እስካለኝ መረጃ ድረስ ማለት ነው።»

እሳቸው እንደሚሉት አንድ ሰው በጊኒ ትል የተበከለ ውኃ ቢጠጣ ወዲያው ወይም በአጭር ቀናት ውስጥ የሚታይ ምልክት አይኖርም። በዚህ ምክንያት ነው ላለፉት ወራት ሰዎች በበሽታው መያዛቸን የሚያመላክቱ ነገሮች ባለመታየታቸው የተመዘገበ ነገር የሌለው። ከዚህ ቀደም የዓለም የጤና ድርጅት እንደሚለው ከበሽታው ምልክት ጥርጣሬ ጋር በተያያዘ በጎርጎሪዮሳዊው 2016 ዓ,ም 13,443 ሰዎች በ24 ሰዓት ውስጥ ምርመራ ተደርጎላቸው ነበር። በያዝነው ጎርጎሪዮሳዊ ዓመትም በተመሳሳይ 5044 ሰዎች የበሽታው ጥርጣሬ ኖሮ በ24 ሰዓት ውስጥ 99 በመቶው ምርመራ ተደርጎላቸዋል። 160 መንደሮች አሁንም በክትትል እና ቅኝት ሥር መሆናቸውን ከኢትዮጵያ አገኘሁ ያለውን መረጃ ጠቅሶ በድረ ገፁ የዓለም የጤና ድርጅት ይፋ አድርጓል። ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉት ወ/ሪት መቅደስ ባለፈው ዓመት አንድ ሰው በጊኒ ትል የተበከለ ውኃ ጠጥቶ ከሆነ ትሉ ወደአንጀቱ ገብቶ መፈልፈል መጀመሩን ለማረጋገጥ ከ12 እስከ 14 ወራት መቆየት እንደሚኖርበት ነው ያመለከቱት። አሁን ባለበት ሁኔታ ከኢትዮጵያ በሽታው ጠፍቷል ለማለት አይቻልምም ባይ ናቸው።

Parasit Guinea-Wurm
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Bazemore

«የመተላለፊያ መንገዱ ኬዝ የሚፈጀው አንድ ሰው ከተያዘ በ12 ወር ነው። አንድ ሰው በጊኒ ዎርም የተበከለን ውኃ ከጠጣ የበሽታውን ምልክት የሚያሳየው ከ12 ወራት በኋላ ነው እና በዚያ መካከል ያለውን ምንም አይነት ምልክት አያሳይም እና ለተከታታይ 12 ወራትን የሚፈልገው ለዚህ ነው ማለት ነው። አንድ ዓመት ዜሮ ሪፖርት እያደረግን መታገስ ያለብን በዚህ ምክንያት ነው።»

ክትትል እና ቅኝቱ ተጠናቅሮ የሚቀጥልበት የራሱ ምክንያት አለው። ከዚህ ቀደም በበሽታው የተያዙ ጥቂት ሰዎች ጊኒ ትል የሚገኝበት አካባቢ ነዋሪዎች ሳይሆኑ ከሌላ ስፍራ ለሥራ የሄዱ ናቸው።  ከሦስት ወራት ወዲህ ደቡብ ሱዳንም በጊኒ ትል የተያዘ ሰው ስለመኖሩ አልተመዘገበም። ባለፈው ዓመት በሽታው ከተገኘባቸው ሃገራት አንዷ ስለሆነችው ቻድ ግን እስካሁን የወጣ አዎንታዊ መረጃ የለም። ከእንስሳት ወደ ሰዎች በሽታው የመተላለፉ ጉዳይም ጥናት እየተደረገበት በመሆኑ ጥንቃቄው መቀጠል እንደሚኖርበት ይታመናል።

ሸዋዬ ለገሠ

አዜብ ታደሰ