1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ሲታወሱ

ሰኞ፣ ኅዳር 27 2014

ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው የመጀመርያዉ የፎክሎር ተመራቂና መምህር፤ ኦሮምኛ ቋንቋን ጨምሮ ሰባት ቋንቋዎችን ይናገሩ የነበሩ ናቸዉ ሲሉ በተማሪዎቻቸዉ ይታወሳሉ። ይህንን የቋንቋ ችሎታቸዉን ተጠቅመዉ ብዙ የጥናት ፅሑፎችን አዉጥተዋል። አብዬ ሰይፉ ነበር የምንላቸዉ ሲሉም የቀድሞ ተማሪዎቻቸዉ ያስታዉሱዋቸዋል።

https://p.dw.com/p/43lAY
Äthiopien Der Autor und Poet Seifu Metaferia
ምስል privat

ገጣሚ ሰይፉ መታፈርያ ሲታወሱ

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በቋንቋና ሥነ-ጽሑፍ መምህርነት ለረጅም ዓመታት ያገለገሉት ገጣሚ፤ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው፤ ተወዳጅ መምህር፤ በሥነ- ግጥም አፃፃፋቸዉ ለየት ያሉ መሆናቸዉ ይነገርላቸዋል። በኢትዮጵያ የመጀመርያዉ የፎክሎር መምህር መሆናቸዉን፤እና አብዬ ሰይፉ ስንል እንጠራቸዉ ነበር ሲሉ የቀድሞ ተማሪዎቻቸዉ ይናገራሉ። በአሁኑ ወቅት በጀርመን ሃንቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ እና የቀድሞ ተማሪያቸዉን ነጋሽ መሐመድን ስለገጣሚና፣ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ምን ይሉ ይሆን? ጠይቀናቸዋል።

በሐረር ልዑል ራስ መኮንን አንደኛ ደረጃ ት/ቤት በአዲስ አበባ ተፈሪ መኮንን ከዝያም በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ትምህርታቸዉን የተከታተሉት ሰይፉ መታፈሪያ፤ በአቴና ዩንቨርስቲ (ነገረ መለኮት)፣ በፓሪስ - ሶርቦን (እስልምና-ነክ) ትምርት መከታተላቸዉ የታሪክ ማኅደራቸዉ ያሳያል። በኢትዮጵያ የፎክሎርን ትምህርት ያስተዋወቁት ረ/ፕሮፌሰር ሰይፉ መታፈሪያ፤ ቀደም ሲል በካርቱም ዩንቨርስቲ በእስያና አፍሪቃ ጥናት ተቋም ዉስጥ የመጀመርያዉ ኢትዮጵያዊ የፎክሎር ማለትም በቃል ያለ የማኅበረሰብ ባህል የልማድ እና ሥነ ምግባር ጥናት ተመራቂ መሆናቸዉን በጀርመን ሐንቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ፤ ያስታዉሳሉ።   

የዶቼ ቬለዉ ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ በበኩሉ፤ የሰይፉ መታፈሪያን አስተማሪነት አዉርቶ አይጠግብም። ሰይፉ ይላል በፈገግታ፤ አብዬ ሰይፉ ነበር የምንላቸዉ። ብቻ አብዬ ያልዋቸዉ ከኛ ቀደም ብሎ የነበሩ ተማሪዎች ናቸዉ። እርስ በረስ ስለሳቸዉ ስናወራ አብዬ ሰይፉ እንበላቸዉ እንጂ፤ ራሳቸዉን አብዬ ሰይፉ ብለን መጥራታችንን አላስታዉስም ሲል ጋዜጠኛ ነጋሽ መሐመድ ሰይፉ መታፈሪያን እንደ አስተማሪ እንደጓደኛ እንደ አባት ነበሩ ሲል ይገልፃቸዋል፤ ያስታዉሳቸዋል። ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ኦሮምና ቋንቋን ጨምሮ ሰባት ቋንቋዎችን እንደሚናገሩ፤ ይህንን የቋንቋ ችሎታቸዉን ተጠቅመዉ ብዙ የጥናት ፅሑፎችን ማዉጣታቸዉን የነገሩን፤ በጀርመን ሃንቡርግ ዩኒቨርስቲ የአፍሪቃ እና የኢትዮጵያ ጥናቶች የትምህርት ክፍል መምህር ዶክተር ጌቲ ገላዬ ናቸዉ። ሰይፉ መታፈሪያ በ1984 ዓ.ም ኢህአዴግ ካባረራቸው 42 አንጋፋ ምሁራን መካከል አንዱ እንደነበሩም ተማሪዎቻቸዉ አጫዉተዉናል። ጥቅምት 24 ቀን 2014 ዓ.ም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩት ገጣሚ ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬው ስድስት የታተሙ፤ እና ሦስት ያልታተሙ የግጥም መድብሎች አልዋቸዉ። ረጅም መጣጥፍና በርካታ የጥናት ጽሑፎችንም አበርክተዋል። ሰይፉ መታፈሪያ ፍሬዉ ባለትዳር እና የአራት ልጆች አባት እንዲሁም የአራት ልጆች አያት  ነበሩ። 88 ዓመታቸዉ ነበር። የቀብር ሥነ-ስርዓታቸዉ በስደት በኖሩበት በዩናይትድ ስቴትስ አትላንታ ጆርጅያ ተፈፅሞአል። ነፍስ ይማር! 

አዜብ ታደሰ   

ነጋሽ መሐመድ