1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ጀርመን፣ ኢትዮጵያና የፀጥታ ኃይላትን የማሰልጠኑ ድጋፍ ጉዳይ

ረቡዕ፣ የካቲት 22 2009

የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ከአምስት ወር በፊት ኢትዮጵያን በጎበኙበት ወቅት ለኢትዮጵያ ፖሊስ ስልጠና በሚሰጥበት ጉዳይ ላይ ተባብረው ለመስራት ተስማምተው ነበር። ይኸው የአቅም ግንባታ ርዳታ ስምምነት በወቅቱ ምን ላይ ይገኛል? ለዶይቸ ቬለ ጥያቄ  የጀርመን የውጭ ጉዳይ እና የሀገር አስተዳደር ሚንስቴሮች በጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

https://p.dw.com/p/2YTl4
Äthiopien Polizei
ምስል imago/Xinhua

በኦሮሚያ እና በአማራ ክልሎች በተካሄዱ ተቃውሞዎች  ወቅት የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይላት በተቃዋሚዎች አንፃር የወሰዱትን እርምጃ የጀርመን መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል ባለፈው ጥቅምት ወደ ኢትዮጵያ በተጓዙበት ጊዜ በጥብቅ በመንቀፍ፣ ለውዝግቡ በውይይት መፍትሔ እንዲያገኝለት ማሳሰባቸው አይዘነጋም። የመብት ተሟጋቾች እንዳስታወቁት፣ በተቃውሞው ወቅት በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ሰዎች ተገድለዋል። በኢትዮጵያ የስድስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ ከታወጀ ከሁለት ቀን በኋላ ሀገሪቱን የጎበኙት ጀርመናዊትዋ መራሒተ መንግሥት የኢትዮጵያ ፀጥታ ኃይላት እርምጃ ተመጣጣኝ ሊሆን እንደሚገባው እና ሰው መሞት እንደሌለበት አሳስበው፣ ይህን በተመለከተ  የጀርመን ፌዴራል ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ከኢትዮጵያ ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ጋር ተባብሮ ለመስራት ያለውን ዝግጁነት ገልጸዋል። ይህን ተከትሎ  የኢትዮጵያ መንግሥት ለፀጥታ ኃይሎቹ፣ የሚያጋጥሙ የፀጥታ ችግሮችን በአግባቡ መፍታት የሚችሉበት ርዳታ፣ በዚሁ መስክ ሰፊ ተሞክሮ አላት ከሚላት ጀርመን እንዲደረግለት ጥያቄ ማቅረቡን የጀርመን ውጭ ጉዳይ እና ሀገር አስተዳደር ሚንስቴሮች አስታውቀዋል። 
« መራሒተ መንግሥት ዶክተር አንጌላ ሜርክል እጎአ ጥቅምት፣ 2016 ዓ.ም  ያደረጉትን ጉብኝት ተከትሎ ከኢትዮጵያውያኑ በኩል በአውሮጳውያኑ ዓመት ማብቂያ ላይ ለኢትዮጵያ ፖሊስ በ« ክራውድ ኮንትሮል ማኔጅመንት» ማለትም፣ ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብበት ጊዜ የሚፈጠር መጨናነቅን የመቆጣጠር ስልትን በተመለከተ ሰፋ ያለ የአቅም ግንባታ ርዳታ እንዲደረግለት ለውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ጥያቄ ቀርቦዋል። ኢትዮጵያ በዚሁ የርዳታ ፕሮዤ አማካኝነትም ከጀርመን ፖሊስ አመራር አባላት ጋር ሀሳብ ለመለዋወጥ ይቻል ዘንድ ወደ ጀርመን አንድ የመረጃ ማሰባሰቢያ ጉዞ የሚደረግበት ሁኔታ እንዲመቻች ጠየቀች። »
በሚኒስቴሮቹ የጋራ መግለጫ መሰረት፣ የኢትዮጵያ ጥያቄ በጀርመናውያኑ ዘንድ ተቀባይነት አግኝቶ፣ ይህን ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችለው ሀሳብ ቀርቦ እንደነበር ተመልክቶዋል።
« የጀርመን  ሀገር አስተዳደር ሚንስቴር ይህንን ጥያቄ ተቀብሎ፣  የጀርመን ፌዴራል ፖሊስ ዋና መስሪያ ቤት ጥር፣ 2017 ዓ.ም  ማብቂያ በሚያካሂደው የመረጃ ማቅረቢያ ዝግጅት ላይ የፌዴራል ፖሊስ ስራ(ተግባር) የሚለውን አመለካከቱን ለማሳየት ሀሳብ አቀረበ። በዚሁ ዝግጅትም ላይ ሕዝብ በብዛት በሚሰበሰብበት ጊዜ የሚፈጠር መጨናነቅን በመቆጣጠር ስልት ላይ የሀሳብ ልውውጥ ሊደረግ የሚችልበት አጋጣሚ መኖሩንም ጠቁሟል። የኢትዮጵያ ወገን ሀሳቡን አልተቀበለውም።  በአሁኑ ጊዜ አጠቃላይ ርዳታ ሊሰጥ የሚቻልበትን  ጉዳይ እየተፈተሸ ነው። »        
መራሒተ መንግሥት አንጌላ ሜርክል እና  የኢትዮጵያ መሪዎችበአዲስ አበባ ባካሄዱት ውይይታቸው ከፀጥታ ጉዳዮች ጎን፣ ወደ አውሮጳ የሚደረገውን ስደት መቆጣጠር እና የአፍሪቃ ህብረት የሚያካሂዳቸውን የሰላም ማስከበሪያ ተልዕኮዎች ማጠናከር በሚቻልባቸው የጋራ ጉዳዮች ላይ በሰፊው መምከራቸው የሚታወስ ነው።

Afrika Kanzlerin Merkel in Äthiopien
ምስል picture-alliance/dpa/M. Kappeler

አርያም ተክሌ

አዜብ ታደሰ