1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስአፍሪቃ

ጀርመናዊው የስነ ፈለክ ተመራማሪ ራየንሃርት ጌንዝልና ግኝቶቻቸው

ረቡዕ፣ ጥቅምት 4 2013

ስዊዲን ስቶኮልም የሚገኘው የኖቬል ኮሚቴ የዘንድሮውን ሽልማት በፊዚክስ ዘርፍ ለብሪታንያዊው ሳይንቲስት ሮጀር ፔንሮሴ፣ ለጀርመናዊው የስነ-ፈለክ ተመራማሪ ሬንሃርድ ጌንዝል እና ለአሜሪካዊዋ የፊዚክስ ሊቅ አንድሪያ ጌዝ ሰጥቷል። ሊቃውንቱ ሽልማቱን ያገኙት «ብላክ ሆልስ»ተብለው በሚጠሩት የአፅናፈ-ሰማይ ጨለማ ክፍል ባደረጉት ምርምር ነው።

https://p.dw.com/p/3jwDv
Nobelpreis für Physik 2020 Roger Penrose, Reinhard Genzel, Andrea Ghez
ምስል Niklas Elmehed for Nobel Media

 ሽልማቱ «ብላክ ሆልስ»ተብለው በሚጠሩ l,አፅናፈ-ሰማይ ጨለማ ክፍል ምርምር ነው


 የዘንድሮው የፊዚክስ ዘርፍ የኖቤል ሽልማት በጨለማው የአጽናፈ ዓለም ወይም «ዩንቨርስ» ክፍሎች ላይ በተደረገ ምርምር ላይ ያተኮረ መሆኑን ኮሚቴው በስቶክሆልም ያለፈው ሳምንት  ሽልማቱን ሲያስተዋውቅ ገልጿል።ሽልማቱ ለሶስት ሊቃውንት በጋራ የተሰጠ ሲሆን  ሮጀር ፔንሮዝ ጥቋቁር ጉድጓዶች ወይም «ብላክ ሆልስ»  የአጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሀሳብ ቀጥተኛ ውጤት መሆናቸውን አሳይተዋል።ፕሮፌሰር ሬይንሃርድ ጌንዘልና አንድሪያ ጌዝ  ደግሞ «ጋላክሲ» ተብሎ በሚጠራው  የከዋክብት ክምችት ማዕከል ብርሃን በውስጣቸው የማያልፍባቸው ግዙፍና ዕምቅ  ጨለማ ክፍሎች ወይም «ብላክ ሆልስ» መኖራቸውን ያረጋገጠ  ግኝት ሰርተዋል።
 በ1965 የታተመው የፔንሮሴ ምርምር ከአልበርት አንስታይን አጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሀሳብ ወዲህ በዘርፉ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረገ ግኝት የተባለ ሲሆን፤የጌንዝልና የባልደረባቸው ግኝት ደግሞ እንደ ኮሚቴው ገለፃ  «ብላክ ሆልስ»ን በተመለከተ እስካሁን ከተረጉት ምርምሮች ሁሉ በጣም የሚያሳምኑ ማስረጃዎችን የያዘ ግኝት ነው።ፕሮፌሰር ራየንሀርድ ጌንዘልም ለምርምሩ አድናቆት አላቸው።
«በጣም ጠንካራ ቡድን ነው።በ«ብላክ ሆልስ» ላይ በተደረገው ምርምር ስለ ስበት በስፋት  ለማሰላሰል አግዟል። ከዓመታት በፊት ካከበርነው የአጠቃላይ አንፃራዊነት ጽንሰ-ሀሳብ   በ«ብላክ ሆልስ»  በኳንተም ፊዚክስ፣ እና በበርካታ ጎራዎች እንዲሁም በስበት ኃይል ላይ  ምርምር መደረጉ እጅግ በጣም አስደሳች ነው። »

Nobelpreisträger 2020 | Astrophysik | Reinhard Genzel
ምስል Andreas Gebert/Reuters

የስነ-ፈለክ ተመራማሪው ሬይንሃርድ ጌንዘል በጎርጎሪያኑ 1952 በጀርመን ሄሰን  ግዛት ፍራንክፈረት ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ ባድ ሆንቦርግ ፎን ዴር ሆኸ በተባለች ቦታ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በተወለዱበት አካባቢ ተከታትለዋል።በጎርጎሪያኑ ከ1974 ዓ/ም ከፍራይቡርግ ዩንቨርሲቲ በፊዚክስ የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን፣እስከ1978 ባሉት ዓመታት ደግሞ በቦን ዩንቨርሲቲ ሁለተኛና  የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ተከታትለዋል።ተመራማሪው በአሁኑ ወቅት በጀርመን  የማክስ ፕላንክ ንድፈ-ሃሳባዊ የፊዚክስ ተቋም ዳይሬክተር እና በአሜሪካ በርክሌይ የካሊፎርኒያ ዩንቨርሲቲ ፕሮፌሰር ናቸው።ተመራማሪው ስራ የጀመሩት በጀርመን በማክስ ፕላንክ ተቋም ሲሆን፤  በ1980 ዓ/ም ባገኙት የተለዬ ዕድል የኖቬል ተሸላሚው የቻርለስ ቶወንስ ቡድንን ለመቀላቀል ወደ አሜሪካ ካሊፎርኒያ ዩንቨርሲቲ አመሩ።የምርምር ስራቸው የሚጀምረውም ከዚሁ ጊዜ ጀምሮ ነው።
«ወደ እኔ ጉዳይ ስመለስ  ወደ ሌላ የኖቬል ሎሬት ይወስደኛል።እንደ ሁለተኛ አባቴ ከምቆጥረውና  ሁሌም  የቻርለስ  ልጅ  እንደሆንኩ ከሚሰማኝና በ1964 የኖቤል ሽልማትን ካገኘው የስነ-ፈለግ ተመራማሪ  ቻርለስ  ቶኖው ጋር በበርክሌይ  በ1980 ዎቹ ከ40 ዓመታት በፊት አብረን መስራት ጀመርን።ብዙ ትግስት ይጠይቃል።ሁል ጊዜ የተሻለ እና የተሻለ ነገር ለመሞከር ።»
«ብላክ ሆልስ»ን በተመለከተ  በ18ኛው ክ/ዘመን እንግሊዛዊው ሊቅ ጆን ሚሸል እና ፈረንሳዊው ሳይንቲስት ፒሬ ስምዖን ዴ ላፕሌስ፤ በአፅናፈ-ዓለም ውስጥ «ከባድና ጥቅጥቅ ያሉና  ሊታዩ የማይችሉ፤ አካላት አሉ።» የሚል ጥቅል ሃሳብ ያቀርቡ የነበረ ሲሆን። ከአንድ ክፍለ ዘመን በኋላ በ1915 አልበርት አንስታይን አጠቃላይ የአንፃራዊነት ፅንሰ-ሃሳብን ከጊዜና ከቦታ ጋር አጣምሮ አቅርቧል።እስከ 1960 ዎቹ ድረስ ይህ ፅንሰ-ሀሳብ  እንደ ግምትና መላ ምት ብቻ ተደርጎ ይወሰድ ነበር።
በ19 60ዎቹ መጨረሻና በ1970ዎቹ መጀመሪያ  ተመራማሪዎች ወተት መሰሉ የከዋክብት መንገድ ወይም«ሚልኪ ወይ» ሌሎች ክዋክብትንና ዕምቅ ጥቋቁር ጉድጓዶችን ሊይዝ ይችላል የሚል ምናልባታዊ ሀሳብ ቢያቀርቡም ጉዳዩን  በማስረጃ  ማጠናከር አልተቻለም ነበር።ምክንያቱም ይህ  መንገድ  በአቧራ የተሞላ ደመና ነው ተብሎ ይታሰብ ነበር።
እነዚህ አስደናቂ ክስተቶች  በእውነተኛው አፅናፈ-ዓለም ወይም «ዩንቨርስ»አሉ ወይ?የሚለውን ለመመለስ ጆን ሚሸል በ1783 ክዋክብትንና በዙሪያቸው ያለውን እንቅስቃሴ ማጥናት ያስፈልጋል የሚል ሀሳብ የነበረው ቢሆንም በወቅቱ ያንን የሚያደርግ መሳሪያ አልነበረም። 
በ1970ወቹ መጨረሻና  በ1980ወቹ መጀመሪያ ግን ፕሮፌሰር ራየንሀርድ ጌንዝል የተካተቱበት  የቻርለስ ቶወንስ ቡድን  በአቧራማው ደመና ማለፍ የሚችልና  የክዋክብቱን ማዕከል ማየት የሚያስችል መሳሪያ ወይም «ቴሌስኮፕ» ሰሩ።

Schweden Die 3 Physik-Nobelpreisträger 2020
ምስል Fredrik Sandberg/Reuters

በ1990 ደግሞ ጌንዝልና ባልደረቦቻቸው ሌላ አዲስ  የ«ሚልኪ ዌይን» ማዕከል በአጭር የሞገድ ርቀትና እና ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ የማዕዘን ጥራት ለመከታተል የሚያስችሉ አዳዲስ መሣሪያዎችን ማዘጋጀታቸውን ቀጠሉ። በ 1996 ዓ/ም ለ«ሚልኪ ወይ» ቅርብ በሆኑ የከዋክብት እንቅስቃሴ ላይ ሁለት ገለልተኛ ምልከታዎችን በማድረግ መረጃ አቅርበዋል።በእነዚህ  ሁለት ምልከታዎች  እጅግ ግዙፉና ጨለማው ክፍል  «ብላክ ሆል» የተባለው አስደናቂ ክስተት እንደነበረ አሳማኝ ማስረጃ አቅርበዋል።የኖቬል ኮሚቴ አባሉ ፕሮፌሰር ኡልፍ ዳንኤልሰን እንደሚሉት ይህ ህልም የተሳካው ከጆን ሚሸል ንድፈ ሀሳብ ከ200 ዓመታት በኋላ ነበር።
«ይህ ህልም  እውን ከመሆኑ በፊት ከ200 ዓመታት በላይ ወስዷል።  እናም ይህንን ያደረጉት ራየንሃርድ ጌንዘል፣ አንድሪያ ጌንዝና የቡድን አባሎቻቸው ናቸው።የርቀት መመልከቻቸውን 26 ሺህ የብርሃን ዓመታት ወደ ሚርቀው የክዋክብት ክምችት ማዕከላዊ ክፍል አዞሩ። ምክንያቱም ፤ለየት ያለ እንግዳ ነገር እየተከናወነ እንደነበር ጥርጣሬ አላቸውና።ጥቅጥቅ ባለው የአቧራ ደመና ውስጥ  የተደበቀውን «ጋላክሲ »ምስጢሩን ለማወቅ ማየት ነበረባቸው። ያገኙት ነገርም አስደናቂ ነበር።»
ጌንዝልና ባልደረቦቻቸው በዚህ ሁኔታ ምርምራቸውን የቀጠሉ ሲሆን  «አንዳች ነገር ተመለከቱ» ይላሉ ፕሮፈሰር ዳንኤልሰን ።
«በርካታ ከዋክብት በማይታይ አንዳች ነገር ዙሪያ ሲሽከረከሩ ተመለከቱ። እናም አንድ ኮከብ ትኩረታቸውን ሳባ።ኮከቡ በራሱ ዛቢያ ለመዞር 16 ዓመታት አካባቢ ይወስድበታል።ከማይታየው አንዳች ነገር ከ 17 የብርሃን ሰዓታት  ያልበለጠ ርቀት ነበረው።የሂሳብ ስሌቶች እንደሚያሳዩት 4 ሚሊዮን «ሶላር ማስ» እዚያ ተሸሽጓል።ይህ ነገር ከዕምቅ ጥቁር ጉድጓድ  ውጭ ሌላ ማብራሪያ አይኖረውም።» 
በዚህ ምርምር ፕሮፌሰር ራየንሀርት ጌንዘል በ«ጋላክሲ»ዕምብርት ስላለው ጨለማ ቦታ አንዳች ሚስጥር በንድፈ-ሀሳብ ደረጃ ያቀረቡ ሲሆን፤ ይህ ግዙፍና በጣም ዕምቅ  ነገር «ጋላክሲ»ተብሎ በሚጠራው የከዋክብት ክምችት ማዕከላዊ ቦታ ላይ እንደሚገኝ ተመራማሪው ደርሰውበታል።ይህ ግዙፍ  ነገር በተከማቹ ክዋክብት  ወይም «ጋላክሲ» ዕምብርት ላይ በመሆን  የከዋክብትን ምህዋር እንደሚቆጣጠርም በምርምራቸው  አሳይተዋል።ፕሮፌሰሩ ለዚህ የበርካታ ዓመታት ስራቸዉም የአሁኑን የኖቬል ሽልማት ጨምሮ ሰባት የተለያዩ ሽልማቶችን አግኝተዋል።ለዚህም ክብር ይሰማቸዋል።
«ለእኛ በጣም አስገራሚ ነገር ነው። ይህን በፍፁም አልጠበኩም።ለእኔ ፍፁም ክብር ነው። ከቡድኔ ጋር ለነበረው የ30 ዓመታት ሥራም ክብር ነው።»

Physik-Nobelpreis Reinhard Genzel
ምስል Stefan Gillessen/Max-Planck-Instuitut für extraterrestrische Physik/dpa/picture alliance

ተሸላሚዎቹ የታመቁ እና እጅግ በጣም ግዙፍ የሆኑ ነገሮችን በማጥናት አዲስ ነገር አሳይተዋል። ነገር ግን እነዚህ ያልተለመዱ ነገሮች አሁንም መልስ የሚያሻቸው ጥያቄዎችን የሚያጭሩ እና  ለምርምር የሚጋብዙ  ናቸው።ጥያቄው በጥቋቁር ጉድጓዶች  ውስጣዊ አወቃቀር  ብቻ ሳይሆን በእነሱ አቅራቢያ  የስበት ንድፈ-ሀሳብን  እንዴት መሞከር ይቻላል የሚል ጭምር ነው።
እንደ ኖቤል ኮሚቴው ዳንኤልሰን ገለፃ ፣የሬይንሃርድ ጌንዘል እና አንድሪያ ጌዝ ፈር ቀዳጅ ሥራዎች የአንስታይንን በአጠቃላይ አንፃራዊ ፅንሰ-ሀሳቦችን ለመረዳት ለአዲሱ ትውልድ መንገድ ከፍቷል።ለአዳዲስ የንድፈ ሀሳብ ግንዛቤዎችም ፍንጭ መስጠት ይችላል። ምክንያቱም የአጽናፈ ዓለም ምርምር ያልደረሰባቸው ብዙ ምስጢሮች እና አስገራሚ ነገሮች ይኖራሉና።
 «የዚህ አመት ሎሬቶች በአጽናፈ ሰማይ ውስጥ ያለውን በጣም ጨለማ ጥግ  ሚስጥሮች መዳሰስ ችለዋል።ነገር ግን ይህ ወደ መደምደሚያ  የሚመጣ ጀብዱ አይደለም። ይህ  አዲስ ጅምር ነው።ወደ« ብላክ ሆልስ» አድማስ ይበልጥ በቀረብን ቁጥር ተፈጥሮ አዲስ አስደናቂ ነገሮች ይኖሯታል።
ያለፈው ዓመት የፊዚክስ ዘርፍ የኖቬል ሽልማት በ«ቢግ ባንግ» ቅድመ እንቅስቃሴ ንድፈ ሀሳብ ካናዳዊው ሊቅ ጄምስ ፒብልስ እና ከፀሐይ ሥርዓት ውጭ ያሉ ፕላኔቶችን በማፈላለግ ለተሳተፉት ለስዊዝ የሥነ ፈለክ ተመራማሪዎች ሚሸል ማየርና ዲዴር ኮሎዝ ተሰጥቷል።
ከጎርጎሪያኑ 1901 እስከ 2020 ዓ/ም ባሉት ከመቶ በላይ ዓመታት በፊዚክስ ዘርፍ 216 ሽልማቶች የተሰጡ ሲሆን ከነዚህ ውስጥ የዛሬውን ጨምሮ አራቱ ተሸላሚዎች ሴቶች ናቸው። በዋናነት ሽልማት ከወሰዱ አስር ሀገራት መካከል አሜሪካ 95 ጀርመን 27 ብሪታንያ 25 በመውሰድ ከአንድ እስከ ሶስት ያለውን ቦታ ይይዛሉ። ጃፓን ከአስሩ ሀገራት ውስጥ 9 ሽልማቶችን በመውሰድ በሰባተኛ ደረጃ የተቀመጠች ብቸኛዋ የኤስያ ሀገር ነች።


ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሰ