1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዶ/ር መረራና 114ቱ እስረኞች ተፈቱ፤ «ሌሎቹስ»?

ዓርብ፣ ጥር 11 2010

«ሌሎቹስ እስረኞች መች ይፈታሉ»? በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የበርካቶች ጥያቄ ነው። የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀ-መንበር ዶ/ር መረራ ጉዲናን ጨምሮ 115 እስረኞች ከትናንት በስትያ ከእስር መለቀቃቸውን የሚመለከቱ አስተያየቶች ተበራክተዋል፤ በትዊተር፣ በፌስቡክ እና በዋትስአፕ የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል።

https://p.dw.com/p/2r7Cv
Äthiopien Gudina Freilassung
ምስል DW/G. Tedla Hailegiorgis

115 እስረኞች ተፈቱ፤ «ሌሎቹስ» የሚል ጥያቄ አጭሯል

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግሬስ ሊቀ-መንበር ዶክተር መረራ ጉዲና ረቡዕ የካቲት 9 ቀን 2010 ዓም ከ115 እስረኞች ጋር የመለቀቃቸው ዜና በርካቶችን ያስደሰተውን ያህል ሌሎቹስ የሚል ጥያቄም አጭሯል። ገዢው ፓርቲ ኢሕአዴግ «የተሻለ ሀገራዊ መግባባትን ለመፍጠር»፤ ብሎም «የዲሞክራሲ ምኅዳሩን ለማስፋት» በሚል እስረኞችን መፍታት መጀመሩን በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች በበጎ መልኩ ተመልክተውታል። በዛው መጠን ደግሞ መንግሥት የፖለቲካ እስረኞችን በአጠቃላይ እንዲፈታ የሚደረገው ውትወታ እስረኞችን እፈታለሁ ሲል ከተናገረበት ካለፉት ሁለት ሳምንት አንስቶ አሁንም ድረስ እየተስተጋባ ነው። ይህንኑ በተመለከተ በማኅበራዊ የመገናኛ አውታሮች የተሰጡ አስተያየቶችን አሰባስበናል። 

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ የፍርድ ሒደታቸው በመታየት ላይ የሚገኙ የ528 ተጠርጣሪዎች ክስ በመጀመሪያ ዙር እንዲቋረጥ መወሰኑን ሰኞ እለት መግለጡን ተከትሎ ነበር 115ቱ እስረኞች ረቡዕ እለት የተለቀቁት። የእስረኞቹ መለቀቅ በተለይ የዶክተር መረራ ጉዲና ከቤተሰብ እና ከወዳጅ ዘመድ መገናኘታቸው ከፍተኛ መነጋገሪያ ኾኗል። 

ዶክተር መረራ ጉዲና ከእስር የመለቀቃቸው ነገር የማይቀር መሆኑን የተገነዘቡ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ወደ ቂሊንጦ ሲሄዱ የሚታይበትን ምስል በመለጠፍ ከእስር መለቀቃቸውን ቀደም ብለው ገልጠዋል። በእለቱ ዘጋቢዎቹን በየቦታው አሰማርቶ ከዋናው ስቱዲዮም ሲከታተል የቆየው ዶይቸ ቬለ ዶክተር መረራ ወደ መኖሪያ ቤታቸው አመሻሹ ላይ መድረሳቸውን ዘግቧል፤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎችም መረጃዎችን ሲያስተላልፍ ቆይቷል። በዶይቸ ቬለ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች የተሰጡ አስተያየቶችን ወደ በኋላ ላይ እናቀርባለን። በቅድሚያ በተለያዩ ሰዎች የተሰጡ አስተያየቶችን እናስቀድም። 

Facebook User Symbolbild
ምስል Reuters/D. Ruvic

ቶሎሳ ኢብሳ፦ «ለህዝብ ብሎ ስቃይ መከራ የተቀበለው ህዝብም በዝህ መልኩ ነው ዶክተር መረራ ጉዲና የተቀበለው በ1 ሰዓት ውስጥ በሬውን አርዶ ደግሶ በፍቅር አቀባበል አድርጎለታል» ሲል ፌስቡክ ላይ ጽፏል። የተለያዩ ፎቶግራፎችንም አያይዟል። በሬ ታርዶ፤ ሙዳ ሥጋው በትሪ ተዘርግቶ፤ ሻሽ የመሰለ ነጭ ጥቅል እንጀራው በሰፊ ሳህን ተቆልሎ፤ ጠረጴዛው ላይ መጠጥ እና የላስቲክ ውሃ ተደርድሮ ይታያል። ተስፋዬ ሰለሞን «ሲያንሳቸው ነው» ሲል ጽፏል። «የሀገሬ ሰው ወዳጁን በፍቅር ማከም ይችልበታል!» ያለው ደግሞ እያሱ ተስፉ ነው። 

ጺዮን አሸናፊ፦ «በጣም ደስ ይላል የህዝብ ፍቅር» ብላለች። ጋዜጠኛ ካሣሁን ፌስቡክ ላይ፦ «ዶክተር መረራ አምቦ ወይም መላው ኦሮሚያ ብቻ ሳይሆን ከጎንደር እስከ አርባምንጭ፣ ከኢታንግ እስከ ሐረር ወገናቸው ዘንባባ አንጥፎ የሚቀበላቸው ንጉሥ» ሲል አወድሶ ጽፏል። 

ዶ/ር መረራ ለእስር የተዳረጉት በ2009 ዓም የአውሮጳ ኅብረት ብራስልስ ከተማ ውስጥ ባዘጋጀው ስብሰባ ላይ ተካፍለው እንደተመለሱ ነበር። ስብሰባውን የጠሩት የኅብረቱ የምክር ቤት አባል አና ጎሜሽ ስብሰባ የጠሩበትን ፖስተር ትዊተር ላይ አያይዘው ቀጣዩን ጽፈዋል። «በዚህ ፖስተር ነበር ዶክተር መረራ ጉዲና ጥቅምት 30 ቀን 2009 ዓም የአውሮጳ ምክር ቤት ውስጥ የተሳተፉበትን ስብሰባ የጠራሁት። ያም ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ ለእስር ዳረጋቸው። ዛሬ በስተመጨረሻ ከእስር ተፈትተው በሺህዎች የሚቆጠሩ ሁሉም የፖለቲካ እስረኞች ነጻ እንዲወጡ የሚደረገው ጥሪን በመቀላቀላቸው እፎይታ ተሰምቶኛል» ብለዋል። ዶክተር መረራ ጉዲና፦ «ትግላችን በሠላማዊ መንገድ እንቀጥላለን» የሚል መልእክት በኦሮሚኛ ቋንቋ ማስተላለፋቸውን የሚገልጠውን የቪዲዮ መልእክት በርካቶች ተቀባብለውታል። 

Äthiopien  Dr Mererra & Medrek
ምስል DW/Yohannes G. Egziabher

በዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ፦ የዶክተር መረራ እና ሌሎች እስረኞች መፈታታቸውን በተመለከተ የተሰጡ አስተያየቶች በይበልጥ ያተኮሩት ሌሎች እስረኞችም ይፈቱ የሚለው ላይ ነው። ልያ አህመድ፦ «እንኳን ደስ ያለን እንኳን ደስ ያላቹ ብዙ የኅሊና እስረኞችን እንዲፈቱልንም እየተመኘን» ብላለች። ሞሐመድ ሁሴን፦ «እንኳን ደስ አላችሁ ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ» የሚል አስተያየት ሲያሰፍር፤ ሻም ዓሊ ደግሞ፦ «እኳን በሰላም ከትነሹ እስር ቤት ወደ ትልቁ እስር ቤት ተዛወራችሁ፤ እሰይ የሰውን መፈታት ሰማን አገሪቱ መቼ ነው ከታሰረችበት እስርቤት የምትፈታው?» ሲል ጠይቋል። «ከትንሹ እስር ቤት ወደ ትልቁ እስር ቤት እኛ ወዳለንበት እንኳን ተቀላቀላችሁን» የታደሰ ይመር አስተያየት ነው።

«ወያኔ ትንሽ ሰጥቶ ብዙ መውሰድ ልማዱ ነው። ዶ፡ር መረራ ጉዲናን ጥቂት እስረኞችን መፍታቱ የዲሞክራሲ አራማጅ አያሰኘውም። በአሁኑ ሰአት ከመቶ ሺሕ ሕዝብ በላይ ታስረዋል። አብሶም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በወያኔ እስረኛ ስለሆነ ሕዝቡ ሁሉም ከወያኔ ሊፈታ ይገባል» ያለው አማረ ቢሻው ነው። አህመድ ጀማል፦ «ሁሉም የፖለቲከኛ እስረኞች ሊፈቱ ይገባል፤ ለህዝብ ነው የታሰሩት መንግስት የህዝብን ድምፅ ካከበር ሁሉንም ይፍታ» ሲል አስተያየት አስፍሯል።  

Symbolbild Twitter
ምስል imago/xim.gs

«ሀሉም ኢትዮጵያውየን አንድ ላምስት ታስረዋል ይፈቱ» በዛይዳ ገብረጻዲቅ፣ «ሁሉም ሊፈቱ ይገባል» በኢማና አዶና፤ እንዲሁም «ሁሉም የፐለቲካ እስረኞች ይፈቱ» በመረም አደም የተሰጡ አስተያየቶች ናቸው። ፀሐይ አበጋዝ፦ «ሌሎችም እንዲፈቱ አሁንም ልንጮህ ይገባል» ስትል፤ «ወንድወሰን ብሩ፦«አንዱአለም አራጌስ ታላቁ ሰው መቼ ነው የምትፈቱት?» ሲል ጠይቋል። «የሙሥሊም መፉትሄ አፈላለጊ ይፈቱ» የኪሮስ፤ «ኢሀዲጎች እረ ተፋቱን» የይማም መሐመድ፤  እንዲሁም «ሁሉም እስኪፈቱ ትግሉ ይቀጥላል» የታዴ ብሩ አስተያየቶች ናቸው። 

በሒውማን ራይትስ ዎች የኢትዮጵያ አና የኤርትራ ጉዳይ አጥኚ ፌሊክስ ሆርን ረቡዕ እለት በትዊተር ገጻቸው አንዲህ ሲሉ ጽፈዋል፦ «ዶክተር መረራ ቀድሞውንም መታሰር ባይገባቸውም ቅሉ፤ ዛሬ መለቀቃቸውን መመልከት ድንቅ ነው። በፖለቲካ አመለካከታቸው እስር ቤት የሚገኙ ታሳሪዎችም በአፋጣኝ ሊፈቱ ይገባል።»

«ዋው ደስ ይላል እስረኞች መፈታታቸው የቀሩትንም እግዛብሄር ያስፈታቸው» ከጀርመን የደረሰን የዋትስአፕ መልእክት ነው። «ዜናቹን መከታተል አልቻልንም ዶ/መረራ ጉዲና በመፈታታቸው እጅግ በጣም ደስ ብሎናል» ሌላ የዋትስአፕ መልእክት ነው፤ የተላከው ከኢትዮጵያ። ተጨማሪ የዋትስአፕ መልእክቶቻችሁ በቅዳሜው የአድማጮች ማኅደር ተካቷል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ነጋሽ መሐመድ