1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ሲቋረጥ ጅንካ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ታገዱ

እሑድ፣ ታኅሣሥ 19 2012

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የ3ኛ አመት ተማሪ ከሞተ በኋላ ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት እንዲቋረጥ ተወስኗል። ተማሪዎች ሻንጣዎቻቸውን ሸክፈው ከቅጥር ግቢው ወጥተዋል፤ በተማሪዎች መካከል ተመሳሳይ የብሔር ግጭት ፈተና የገጠመው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረዋል ያላቸውን ተማሪዎች እስከ ሁለት አመት ከትምህርት ማገዱን አስታወቋል።

https://p.dw.com/p/3VT08
Äthopien, Dire Dawa University
ምስል DW/M. Teklu

አንድ የሶስተኛ አመት ተማሪ በትናንትናው ዕለት ከዚህ ዓለም በሞት ከተለየ በኋላ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት ማቋረጡን አስታወቀ። ዩኒቨርሲቲው የባንኪንግ እና ፋይናንስ ትምህርት ክፍል ተማሪ የነበረው ወጣት መሞቱን ቢያረጋግጥም ስለ ምክንያቱ ግን በግልፅ ያለው ነገር የለም።

አንድ ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ የዩኒቨርሲቲው መምህር ሕይወቱ ያለፈው ተማሪ «መማሪያ ክፍል አካባቢ ከተደበደበ በኋላ ወድቆ፤ ተወርውሮ ተገኝቷል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። የተማሪው መሞት በተሰማበት በትናንትናው ዕለት በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ ግጭት እንደነበር የዶይቼ ቬለ የድሬዳዋ ወኪል መሳይ ተክሉ ዘግቧል። ግጭቱ ከቅጥር ግቢው ተሻግሮ በአካባቢው በሚገኙ የመኖሪያ ቤቶች ላይ ድንጋይ እስከ መወርወር ደርሶ ነበር።

ዩኒቨርሲቲው ለተማሪዎች ባሰራጨው ማሳሰቢያ የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ሴኔት ላልተወሰነ ጊዜ ትምህርት እንዲቋረጥ መወሰኑን አስታውቋል።

ዩኒቨርሲቲው «ሰኞ ታኅሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊጀመር የነበረው ትምህርት ባጋጠመን ወቅታዊ ችግር ምክንያት በዩኒቨርሲያችን ትምህርት ማስቀጠል የሚያስችል ሁኔታ የለም» ብሏል። በውሳኔው መሠረት የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ለተማሪዎች ከታኅሳስ 20 ቀን 2012 ዓ.ም. በኋላ ምንም አይነት አገልግሎት አይሰጥም።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉት መምህር «እስከ ዛሬ ተማሪዎች እቃቸውን ይዘው መውጣት አልተፈቀደላቸውም ነበር። ከዚያ በኋላ እቃዎቻቸውን ይዘው መውጣት ጀምረዋል። ቤት ያላቸው ወደዚያ ሔደዋል። ወደ አገራቸው እየተመለሱ ያሉ ልጆችም አሉ። በእምነታቸው የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አማኝ የሆኑ ብዙዎቹ በግቢው አቅራቢያ በሚገኘው ስላሴ ቤተ-ክርስቲያን ተጠልለው ይገኛሉ» ሲሉ ተናግረዋል።

«በተማሪዎች መካከል በብሔር ምክንያት በተፈጠሩ አለመግባባቶች ከዚህ በፊት አንድ ልጅ እንደሞተ ይታወቃል» የሚሉት መምህር ታኅሳስ 18 ቀን 2012 ዓ.ም. የተማሪ ሕይወት በድጋሚ የቀጠፈው ድርጊት «ከዚያ ጋ የተገናኘ ነው ተብሎ ይታሰባል» ሲሉ ጥርጣሪያቸውን ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

በተማሪዎች መካከል ተመሳሳይ የብሔር ግጭት ፈተና የገጠመው የጂንካ ዩኒቨርሲቲ ግጭት ለመቀስቀስ ሞክረዋል ያላቸውን ተማሪዎች እስከ ሁለት አመት ከትምህርት ማገዱን አስታወቋል። አስተዳደራዊ እርምጃ የተወሰደባቸው በዩኒቨርሲቲ ቅጥር ግቢ በሚገኙ ተማሪዎች መካከል የብሔር ማንነትን መሰረት ያደረገ ግጭት ለመፍጠር ሙከራ ያደረጉ መሆናቸውን የጅንካ ዩኒቨርሲቲ የኮምዩንኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ዘርጋው ማንአርጎ ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል።

«የመጀመሪያ ደረጃ ጥፋተኛ የሆኑትን አምስት ተማሪዎች ለሁለት አመት ከትምህርት እንዲታገዱ፤ በሁለተኛ ደረጃ ጥፋተኛ ሆነው የተገኙ ተማሪዎች ደግሞ ሰባት ናቸው። እነዚህን ሰባት ተማሪዎች ለአንድ አመት ከትምህርት ገበታቸው እንዲታገዱ» መወሰኑን አቶ ዘርጋው ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል።  አቶ ዘርጋው እንዳሉት በተባባሪነት የተከሰሱ ሌሎች ዘጠኝ ተማሪዎች «ከባድ የፅሁፍ ማስጠንቀቂያ እንዲሰጣቸው» ተወስኗል።

አቶ ዘርጋው እንደሚሉት ባለፈው ጥቅምት 30 ቀን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ግቢ በተማሪዎች መካከል በሙዚቃ ምርጫ ሳቢያ ከተፈጠረ አለመግባባት በኋላ አሁን ቅጣት የተጣለባቸው ተማሪዎች የተቆራረጡ የፌሮ ብረቶችን ወደ ግቢው ይዘው ገብተዋል፤ ለተማሪዎች የተዘጋጁ ምግቦችንም ደፍተዋል።

በዩኒቨርሲቲው ውሳኔ ከትምህርት ከታገዱት መካከል ሁለቱ የሁለተኛ አመት ተማሪዎች ሲሆኑ የተቀሩት የመጀመሪያ አመት ተማሪዎች ናቸው።በጂንካ ዩኒቨርሲቲ እርምጃ በተወሰደባቸው ተማሪዎች ሁከት ለመፈጠር ሙከራ ቢደረግም ትምህርት አለመቋረጡን አቶ ዘርጋው ጨምረው ገልጸዋል።

የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲን ጨምሮ የ45 የኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ተማሪዎች በቅጥር ግቢያቸው እና ከቅጥር ግቢያቸው ውጪ አደጋዎች እየገጠሟቸው በመሆኑ የመንቀሳቀሻ ሰዓታቸውን መገደቡን የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር አስታውቆ ነበር። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ለ45ቱ ዩኒቨርሲቲዎች በፃፈው ደብዳቤ ተማሪዎች ከንጋት 12 ሰዓት በፊትና ከምሽቱ 1 ሰዓት በኋላ ከቅጥር ግቢዎቻቸው ውጪ እንዳይገኙ ትዕዛዝ አስተላልፏል። ተማሪዎች ከምሽቱ 4 ሰዓት በኋላ ከመኝታ ክፍሎቻቸው ውጪ መቆየት እንደማይችሉ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ወስኗል።

መሳይ ተክሉ

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

እሸቴ በቀለ