1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም የተቀሰቀሰው የአፋር እና ሶማሌ አካባቢዎች ግጭት

ዓርብ፣ ነሐሴ 21 2013

በአፋር ክልል ሁለት ዞኖች ተፈጸመ የተባለውን ጥቃት የሶማሌ ክልል አስተባበለ። የአፋር ክልል ከነሐሴ 19 ቀን ጀምሮ በአፋር አርብቶ አደር ላይ ጦርነት ተከፍቶ "ብዙዎችን ለሞት እና ለአካል ጉዳት" እየዳረገ እንደሚገኝ ገልጾ ነበር። ለጥቃቱ "የምሥራቁ ጁንታ" ያለውን ኃይል ከሷል። ሁለቱ ክልሎች በአዋሳኝ አካባቢዎች በተደጋጋሚ ግጭት ገጥሟቸዋል

https://p.dw.com/p/3za0A
Karte Äthiopien Ethnien EN

ዳግም የተቀሰቀሰው የአፋር እና ሶማሌ አካባቢዎች ግጭት

በተለያዩ ጊዜያት አንዱ አንዱን ተወቃሽ በሚያደርግበት ምክንያት የሚቀሰቀሰው የሶማሌ እና አፋር ክልል ተጎራባች አካባቢዎች ግጭት ዳግም መከሰቱን የአፋር ክልል ባወጣው መግለጫ አስታውቋል። የአፋር ብሔራዊ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ባወጣው መግለጫ “የምስራቁ ጁንታ” ያለው ኃይል በአፋር ክልል የተለያዩ ቦታዎች ጥቃት መፈፀሙን እና በዚሁ ሳቢያ በንፁሀን ላይ ጉዳት መድረሱን እንዲሁም የተሽከርካከሪ እና ባቡር ትራንስፖርት መቋረጡን ይገልፃል።  የሶማሌ ክልል መንግስት በበኩሉ “መግለጫው የተሳሳተ እና የተለመደ ነው። እኛ ለምደነዋል” ሲል የመግለጫውን ወቀሳ አጣጥሎታል።

የአፋር ክልላዊ መስተዳድር መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ትናንት ባወጣው መግለጫ  “የምስራቁ ጁንታ ለአሸባሪው ህወሀት ደጀንነቱን በማሳየት በአፋር ክልል በገቢ ረሱ እና አውሲ ረሱ (ዞኖች) በተለያዩ ቦታዎች የተቀናጀ የሽብር ጥቃት በመክፈት በአርብቶ አደሩ ላይ ጭፍጨፋ እየተካሄደ ነው” ብሎ ነበር። የሶማሌ ክልል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ መሀመድ ሮብሌ ለዶይቼ ቬለ በስልክ በሰጡት መረጃ መግለጫውን የተሳሳተና የተለመደ ሲሉ አጣጥለውታል።

በአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን መግለጫ የተሽከርካሪ እና የባቡር ትራንስፖርት ተቋርጧል በሚል የወጣውን መረጃም የተሳሳተ ነው ከትናንት በስትያ ለሰዓታት ተዘግቶ የነበረው መንገድ ክፍት ነው ብለዋል - አቶ መሀመድ።

ከአፋር ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ባይሳካም በአካባቢው ካለ ሁኔታ ጋር በተተያያዘ ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪ የሶማሌ ክልል ልዩ ኃይል የደምብ ልብስ የለበሱ እና መታወቂያቸው የተገኘ አካላት ጥቃት ማድረሳቸውን ገልጠው የፌደራል መንግስት መፍትሄ ማድረግ አለበት ብለዋል።

አስተያየት ሰጪው ከአዋሽ ጅቡቲ በሚሄደው መንገድ በተለይ እንዱፎ በተባለው ቦታ የአፋር ክልል ሰሌዳ ያለው ተተሽከርካሪ እና አፋር ማህበረሰብ እንዳይሄድ እየተደረገ ነው በሚል ለዶይቼ ቬለ የሰጡትን ቅሬታ በሚመለከት ጥያቄ ያቀረብኩላቸው የሶማሌ ክልል ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምክትል ኃላፊ ተከታዩን ብለዋል።

በአፋር ክልል በኩል ትናንት በወጣው መግለጫ ጭፍጨፋ ስለመፈፀሙ ቢገለጥም ትክክለጫውን የአሀዝ እና ሌሎች መረጃዎች ከክልሉ ባለስልጣናት ማረጋገጥ አልተቻለም።

መሳይ ተክሉ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ