1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳግም ተቃውሞ በኦሮሚያና፥ የአትሌቶቹ ዕድሜ

ዓርብ፣ ሐምሌ 14 2009

ሰሞኑን ነጋዴዎች ላይ በተጣለው የቀን ገቢ የግምት ተመን የተነሳ የጀመረው ተቃውሞ በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲቋረጡ አድርጓል። ይኸው ተቃውሞ ሐሙስ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ መከሰቱም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተገልጧል።

https://p.dw.com/p/2gz5P
Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ዳግም ተቃውሞ በኦሮሚያና፥ የአትሌቶቹ ዕድሜ

ሰሞኑን ነጋዴዎች ላይ በተጣለው የቀን ገቢ የግምት ተመን የተነሳ የጀመረው ተቃውሞ በኦሮሚያ የተለያዩ ቦታዎች አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እንዲቋረጡ አድርጓል። ይኸው ተቃውሞ ሐሙስ ዕለት በአዲስ አበባ ከተማ መከሰቱም በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተገልጧል። ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች የሆኑአትሌቶች በሚሳተፉበትየኬንያው ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ላይ ተሳታፊ የነበረው የኢትዮጵያ ቡድን የዕድሜ ጉዳይ በርካቶችን አነጋግሯል። በፌስቡክ በትዊተር፣ በዋትስአፕ ብሎም በሌሎች የመገናኛ አውታሮች በስፋት መነጋገሪያ የሆኑትን አስተያየቶች አሰባስበናል።  

የቀን ገቢ የግምት ተመንን በመቃወም በኦሮሚያ የተለያዩ ከተሞች የተስፋፋው የንግድ ተቋማትን መዝጋትና አገልግሎቶችን ማቋረጥ ድርጊት በአዲስ አበባም ለመከሰት የፈጀበት አራት ቀናት ነው።  ተቃውሞው ሐሙስ ዕለት በአዲስ አበባም መከሰቱ ተሰምቷል። በኮልፌ ሠፈር በተለምዶ ታይዋን በሚባለው የገበያ ሥፍራ የንግድ መደብሮች መዘጋታቸውን የማኅበራዊ መገናኛ አውታር ተጠቃሚዎች ተናግረዋል።

Stadtansicht von Addis Abeba Hauptstadt von Aethiopien
ምስል Imago/photothek

ሠሚር ዓሊ በትዊተር ገጹ «የነጋዴዎች አድማ ተቃውሞ ወደ አዲስ አበባም ገብቷል። ኮልፌ የሚገኙ ሱቆች ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ የሱቅ የመዝጋት አድማ ላይ ናቸው» ሲል ሐሙስ ዕለት ጽፏል።

አቡ ተስፍሽም ትዊተር ላይ ባስነበበው ጽሑፉ፦«ኮልፌ አጠና ተራ ሱቅ መዝጋቱ ማደሙ ተጀምሯል ፖሊስም ነጋዴውን አፍጦ እየጠበቀ ነው» ብሏል።

ዓለማየሁ ተስፋዬ ደግሞዶይቸ ቬለ የፌስቡክ ገጽ ላይ ባሰፈረው መልእክቱ፦ «ዶይቸ ቬለዎች አዲስ አበባ የቱጋ ነዉ አድማውን የተቀላቀሉት አሉባልታ ከምታወሩ እንደ ጋዜጠኛ ለምን ቦታዉ ላይ ሄዳችሁ አትዘግቡም» ብሏል። ሐሩን ራሺድ ለዓለማየሁ በሰጠው መልስ፦ «ኮልፌ እና ታይዋን። የት ነው ያለከው?» ሲል ጽፏል።

ማሜ የሶፊ ልጅ ከሐሩን ጋር ተመሳሳይ መልእክት አስፍራለች። «የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከእለታዊ ግብር ትመና ጋር በተያያዘ የተጀመረውን አድማ ተቀላቀሉ። በሳሪስ፣ አስኮ፣ ኮልፌ፣ አጣና ተራ፣ ዘነበወርቅ፣ ታይዋን ሰፈር ነጋዴዎች ድርጅቶቻቸውን ዘግተዋል። በመርካቶም አንዳንድ መደብሮች ተዘግተው ውለዋል» ስትል አስተያየቷን ሰጥታለች።

እንድሪስ ጋሻው ተፈራ፦«መጥፎው ሲታያችሁ በጎ ሥራውስ ለምን አይታያችሁም? በተግባር እንጅ በወሬ ልማትም ሆነ ጥፋት አይመጣም» ብሏል ተቃውሞው ሐሙስ እለት አዲስ አበባ ኮልፌ አካባቢ እንደነበር በሚገልጠው ጽሑፍ ስር ባኖረው አስተያየቱ።

Äthiopien Oromiya MBO Universität
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

«ግብርና ሕይወት ለናት ሃገር ይከፈላል !! ለፖለቲከኞች ግን ፌሽታ ነው» ያለው ደግሞ አቡ ሞሀመድ ነው።

በጸጉር ሥራ ከሚተዳደር አንድ ግለሰብ በዋትስአፕ የመልእክት መቀበያ ስልካችን ከኢትዮጵያ የደረሰን የጽሑፍ መልእክት እንዲህ ይነበባል። «አንድ ወንበር ነው ያለኝ ፀጉር ነው የምሠራው፤ በቀን 200 ብር ገቢ አሉኝ። ልክ አይደሉም፤ እዴት በዚ ዘመን በግምት ይሠራሉ?» ሲል መንግሥት ያወጣው የቀን ገቢ ግምት አሠራርን ይተቻል። «3 ወበር ያለውን ጓደኛየን ደሞ የቀን ገቢውን 80 ብር፤ 5 ወበር ያለውን ደሞ የቀን ገቢው 120 ብር» ተብሎ መገመቱ ትክክል አለመሆኑን ገልጦልናል።

የተቃጠለ ሚኒባስ ተሽከርካሪ ምስል የሚታይበትን ፎቶ ያያዘው ተገኝ ሳሙኤል ደግሞ፦«አሁን ወያኔ ምንድን ነው የሚያደርገው? በአስቸኳይ አዋጁ ላይ አስቸኳይ አዋጅ ሊያውጅ ይኾንን?» ሲል ጽፏል።

ነጋሳ ቡቤ በትዊተር ገጹ ባሰፈረው ጽሑፍ፦  «በኦሮሚያ ክልል ተቃውሞ ሥራ የማቆም አድማ ቀጥሎ ሻሸመኔ ደርሷል። በሻሸመኔ እና አከባቢው የሚገኙ ከተሞች በክልሉ እና በፌዴራል ፖሊስ ተወረዋል» ሲል ሐሙስ ዕለት ጽፏል።

በአንጻሩ ትናንት ከአምቦ የደረሰን የዘጋቢያችን ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመለክተው ከሆነ ባንኮች፣ ሆቴሎች፣ ምግብ ቤቶች፣ የባጃጅ ታክሲዎችና የህዝብ ማጓጓዣዎች ሥራ ጀምረዋል፡፡ በአምቦ ከተማ ሥራ የተጀመረው ነጋዴዎች ያነሱት ጥያቄ ተመልሶ ሳይሆን የአገልግሎት ማቆም አድማው ለሦስት ቀን የተጠራ ስለነበር መሆኑን የከተማዋ ነዋሪዎች ለዘጋቢያችን መንገራቸውን ገልጦልናል። በከተማይቱ ከመግቢያው ጀምሮ ጦር መሣሪያ የታጠቁ የፌደራል እና የክልሉ ፖሊስ አባላት በየቦታው ቆመው ይታዩ እንደነበር፤ ፖሊሶችን የጫኑ ሦስት ተሽከርካሪዎችም በከተማው እየተዘዋወሩ ቅኝት ሲሠሩ ዘጋቢያችን መመልከቱን ነግሮናል።

Äthiopien Geschäfte streiken wegen Steuergesetz in Oromiya (Ambo)
ምስል DW/Y. Geberegziabeher

ባሳለፍነው ሳምንት የማኅበራዊ መገናኛ አውታሮች መነጋገሪያ ርእስ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል አንዱ የነበረው ኬንያ ውስጥ የተከናወነው የአትሌቲክስ ውድድር ነበር። በውድድሩ ኢትዮጵያን ወክለው የቀረቡት ዕድሜያቸው ከ18 ዓመት በታች ናቸው የተባሉት አትሌቶች የዕድሜ ጉዳይ በርካቶችን አጋግሯል።

የአትሌቶቹን የፊት ገጽታ፤ እንዲሁም የደረት ጸጉር የሚያሳዩ ፎቶዎችን በማያያዝ የእድሜ ማጭበርበር ተከናውኗል ሲሉ የጻፉ በርካቶች ናቸው። የአትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ በሻለቃ ኃይሌ ገብረ-ሥላሴ ፕሬዚዳንትነት መመራት ሲጀምር ለውጥ ይኖራል ብለው የጠበቁ አስተያየት ሰጪዎች የዕድሜ ማጭበርበሩ ጭራሽ መባባሱን ተችተዋል።

ጋዜጠኛ ቆንጂት ተሾመ በፌስቡክ ገጿ ቀጣዩን መልእክት አስነብባለች። «የዕድሜ ማጭበርበር ልክ የተከለከለ ኃይል ሰጪ ንጥረ ነገር እንደመጠቀም ነው» ስትል በእንግሊዝኛ የጻፈችው ቆንጂት፦ «የኛ 18 አመት በታች..በኬንያ የአለም ሻምፒዮና! አፍረናል» በማለት በአትሌቶቹ የዕድሜ ጉዳይ ላይ ተሳልቃለች። «በማጭበርበር ሜዳልያ ለማግኘት ከሚሞክሩ በታማኝነት ተወዳድረው በዜሮ ቢመለሱ  እናመሰግናቸዋለን...ፌዴሬሽኑንም!» ስትል ትዝብት እና ምክሯንም አካፍላለች።

Flash-Galerie Haile Gebrselassie
ምስል AP

የተለያዩ ተቋማትን ኅጸጾች እየተከታተለ ነቅሶ በማሳየት የሚታወቀው እሸቱ ሆማ ቄኖ በአትሌቶቹ የዕድሜ ጉዳይ የፌዴሬሽኑ አመራር ምንም እንዳልተሰማው ጽፏል። «ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ዛሬ ከ18 አመት በታች ተብለው ኢትዮጵያን ወክለው የተሳተፉ አትሌቶችን ቦሌ ኤርፖርት ከዶክተር አሽብር ጋር ሆኖ እየሳቀና እየፈነደቀ ተቀብሏቸዋል። ወጣቶቹ በሰሩት የቡድን ስራ ኩራት የተሰማው መሆኑንም ገልጿል። ሽልማትም አዘጋጅቶላቸዋል» ሲል ጽሑፉን በፌስቡክ ያሰፈረው እሸቱ፦ «አይይይይይ ግን እኮ አብዛኞቹ የቡድኑ አባላት 18ን ከዘለሉ አስራ ምናምን አመት የሆናቸው እንደሆኑ ያለምርመራ ያስታውቃሉ እኮ» ሲል እሱም እንደ ቆንጂት በዕድሜው ጉዳይ ተሳልቋል።

ኬንያ ባስተናገደችው 10ኛው የዓለም ታዳጊ ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያ አራት ወርቅ፣ ሦስት ብር እና አምስት ነሐስ በድምሩ 12 ሜዳሊያዎችን በመያዝ በሜዳሊያ ሰንጠረዥ በአምስተኛ ደረጃ የጨረሰችው፡፡ ደቡብ አፍሪቃ፣ ቻይና፣ ኩባ እና አዘጋጇ ኬንያ ከአንደኛ እስከ አራተኛ ደረጃ በመያዝ ነበር ያጠናቀቁት።

«አዋቂዎችን ከህፃናት ጋር አወዳድሮ በተገኘ ውጤት ኩራት ተሰማኝ ማለት ይደብራል። ደግሞ ራሱ የቡድን መሪው ዱቤ ጅሎ የቡድኑ አባላት እድሜ ማጭበርበራቸውን አምኗል» ያለው እሸቱ ሆማ ጽሑፉን ያጠቃለለው፦«እንደኔ እንደኔ ኢትዮጵያ ያገኘችው ሜዳሊያ ብትቀማ ደስ ይለኛል። የሰው ሃቅ ቀምቶ መጨፈር ነውር ነው» በማለት ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ