1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዳኛ ደብዳቢዎቹና «እምቢ ለሚድሮክ»

ዓርብ፣ ሚያዝያ 26 2010

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርታዊ ጨዋነቱን እየለቀቀ ሥርዓት አልበኝነትን ማንጸባረቅ ከጀመረ ሰነባብቷል። በአጥፊዎች ላይ ይኽ ነው የተባለ ብርቱ ቅጣት ሲፈጸም ስለማይስተዋልም በኳስ ሜዳ ሥርዓት አልበኝነቱ እየተባባሰ መምጣቱን በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ገልጠዋል።

https://p.dw.com/p/2x8PU
Shakiso Town
ምስል Yidnekachew Gashaw

የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ቅኝት

በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እና መከላከያ እግር ኳስ ቡድኖች መካከል በነበረው የእግር ኳስ ግጥሚያ የወልዋሎ ቡድን ተጨዋቾች የመሀል ዳኛውን መደብደባቸው የብዙዎች መነጋገሪያ ኾኗል። የሚድሮክ የወርቅ ማምረቻ ፈቃድ መታደስ የቀሰቀሰው ቁጣም ሌላኛው ርእስ ነበር።

የሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኩባንያ በለገደንቢ ለወርቅ ማምረቻ የተሰጠው ፈቃድ መታደሱ ቁጣ አጭሯል፤ ተቃውሞም ቀስቅሷል። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዎች የሚድሮክ የወርቅ ማውጣት ተግባር እንዲቀጥል መፈቀዱን የሚገልጽ ደብዳቤን በማያያዝ አስተያየቶችን ሰጥተዋል።  የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ የእግር ኳስ ቡድን ተጨዋቾች እና የቡድን መሪው ከመከላከያ ጋር የነበረውን ጨዋታ የመሩት ዳኛን አባርረው መሬት ላይ በመጣል ድብደባ ሲፈጽሙ የሚያሳይ የቪዲዮ ምስል መታየቱ የሳምንቱ ዐቢይ መነጋገሪያ ኾኗል። አስተያየት ሰጪዎች፦ «እብሪት እና ማን አለብኝነት ተንሰራፍቷል»፤ እንዲሁም «በወልዋሎ ሲኾን ጉዳዩ ተጋነነ እንጂ ቀድሞም የነበረ ነው» በሚል ለሁለት ተከፍለው ተከራክረዋል። የኢትዮጵያ እግር ኳስ መልኩን እየቀየረ በመምጣቱ አፋጣኝ መፍትኄ ያሻዋል የሚሉም በርካቶች ናቸው። 

Symbolbild Erstliga Fußball FC Arsenal
ምስል picture-alliance/Back Page Images

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ስፖርታዊ ጨዋነቱን እየለቀቀ ሥርዓት አልበኝነትን ማንጸባረቅ ከጀመረ ሰነባብቷል። በአጥፊዎች ላይ ይኽ ነው የተባለ ብርቱ ቅጣት ሲፈጸም ስለማይስተዋልም በኳስ ሜዳ ሥርዓት አልበኝነቱ እየተባባሰ መምጣቱን በርካታ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ተጠቃሚዎች ገልጠዋል።

ታዋቂው የስፖርት ጋዜጠኛ ፍስሃ ተገኝ ትዊተር ገጹ ላይ የወልዋሎ ተጨዋቾች ዳኛውን ሲደበድቡ የሚያሳየውን ቪዲዮ በማያያዝ በእንግሊዝኛ ባሰፈረው ጽሑፉ ድርጊቱን ፦ «እጅግ አናዳጅ ቅጽበት» ሲል ገልጾታል።  «ዳኛው ተግባራቸውን በፈጸሙ በወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ እግር ኳስ ቡድን መሪ ተጠቁ» ሲልም አክሏል። ድብደባ ፈጻሚዎቹንም፦ «እድሜ ልካቸውን ከእግር ኳስ እና እግር ኳስ ነክ ጉዳዮች አግዷቸው። ሌላም ቅጣት ጨምራችሁ ቅጧቸው» ብሏል።

ሌላኛው የአልጀዚራ እንግሊዝኛ ቋንቋ ጋዜጠኛ ሐምዛ ሞሐመድ እዛው ትዊተር ላይ ባሰፈረው አስተያየቱ የቢቢሲ እንግሊዝኛ ቋንቋ ገጽ የቪዲዮ ምስልን አያይዟል። «በኢትዮጵያ ፕሬሚየር ሊግ ተጨዋቾች አወዛጋቢ ውሳኔ ያስተላለፉ ዳኛ ላይ ጥቃት ሰነዘሩ» ከሚለው የሐምዛ ጽሑፍ ጋር የተያያዘው ቪዲዮ ተጨዋቾቹ ዳኛውን ሲደበድቡ ይታይበታል። ሐምዛ፦ «የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን  የሊጉ ጨዋታዎችን በአጠቃላይ ለሌላ ጊዜ » ማስተላለፉንም አብሮ ጠቅሷል።

«በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ 22 ሳምንት መከላከያ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ያደረጉት ጨዋታ በስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ሳቢያ ተቋረጠ፡፡» በሚል ርእስ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ፌስቡክ ገጽ ላይ ከተያያዘው ቪዲዮ ሥር ቶፊቅ ረዲ ቀጣዩን አስተያየት አስፍሯል።

Symbolbild Fußball Tor Netz
ምስል Fotolia/somkanokwan

«እኔ በበኩሌ መቀሌ፣ ወልዋሎ፣ አፄዎች፣ ወልዲያ፣ ደሴ፣ ጅማ አባጅፉርወላይታ ዲቻ የሚባሉ የእግር ኳስ ቡድኖች በሙሉ በአሁን ሰአት ለሀገራችን የሚያስፈልጉ ስያሜዎች አይመስለኝምእንደ በፊቱ መብራት ኃይልቡና፣ ጊዮርጊስ፣ በተለያዩ ካምፓኒዎች የሚሰየሙ የእግር ኳስ ቡድኖች የተሻሉ ስያሜዎች ናቸው ብዬ አስባለው። የእግር ኳስ ክለቦች እኮ ህዝቡ ካለ መረዳት ብሄር ተኮር እየሆኑ ነው፤ የግሌ ምልከታ ነው» ብሏል። 

ሰዉ ሁሉ ይንበረከክልሻል በሚል የፌስቡክ ስም የቀረበው ሌላኛው መልእክት ደግሞ እንዲህ ይነበባል። «የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን ከብሄር ፖለቲካ ተፅዕኖ ካልፀዳ። ፌደሬሽኑ ከስህተቱ ይታረማል ብለን ግዜ እንስጥ ብለን እንጅ ፊፋ ስፖርቱን በሚጎዳ መድሎ ላይ ቀልድ አያውቅም።»

ሶከር ኢትዮጵያ ዶት ኔት በትዊተር ገጹ፦ «የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የፕሪምየር ሊግ ክለቦች የምክክር መድረክ» በሚል ርእስ በምክክሩ የተሰጡ ዋና ዋና ሐሳቦችን በተከታታይ በጽሑፍ አስፍሯል።  ከጽሑፍ መልእክቶቹ መካከል፦ «የዳኞች ማኅበር እስከ ግንቦት 20 ያቋረጠበት ምክንያት አልገባኝም። ቀኑን የመረጠው ከማን ነፃ ለመውጣት አስቦ ነው?»  እንዲሁም «ጨዋታው እግርኳስ መሆኑ እየተረሳ ነው።» እና « ውድድሩ ዘንድሮ በሰላም እንዲጠናቀቅ መጣር አለብን።» የሚሉ ከተወያዮች የተሰጡ አስተያየቶችን አያይዟል።

«የአማራ እና ትግራይ ክለቦች እርስ በእርስ በየሜዳቸው እንዳይጫወቱ የተወሰነበት ምክንያት ግልፅ አይደለም። በችግሮች ላይ ርምጃ እንደመውሰድ ክልል ከክልል ህዝብ ከህዝብ እንዳይገናኝ መደረጉ አግባብ አይደለም።» ከፋሲል ከተማ የሚል የሶከር ኢትዮጵያ ትዊተር መልእክትም በምክክሩ ከተሰጡ ዋና ዋና ሐሳቦች ስር ይገኛል።

ብሩክ ኢት በሚል የትዊተር ገፅ የሰፈረው ጽሑፍ፦ «ወልድያ እና ወልዋሎ ነጥብ ሊቀነስባቸው ይገባ ነበር። ነገር ግን ማንም ዘረኛ ወጠጤ ፌስቡክ ላይ ስለጮኸና ደብዳቤ ስለላከ የቀልድ ቅጣት ይቀጣል። ሁሌም እንዲህ እየኾነ ይሽከረከራል» በሚል ይነበባል።

Symbolbild Rote Karte Fußball Sport
ምስል picture alliance/DeFodi

ዳዊት ከበደ በትዊተር ጽሑፉ፦ «ዳኛ በተጫዋች ሲመታ አዎ ስህተት ነው አዲስ ክስተት ግን አይደለም። የወልዋሎ ጥፋት "ትንሿ ነገር ከምትጋነንበት" ማህበረሰብ መውጣቱ ብቻ ነው!! በጨዋታ መሀል ወደ ተመልካችን ሄደው ቡጢ የሚሰነዝሩን እነ ሪ ካንቶናን አያደነቅክ ወልዋሎ ላይ አትዝመት!» ብሏል።

«ወልዋሎ አ.ዩ. ተደባዳቢውን የቡድን መሪ አቶ ማሩ ገብረጻድቅን ማሰናበቱን አሳውቋል። መሆን ያለበት ውሳኔ ነው። በቀጣይ ደግሞ ዳኛውንና የመከላከያ ተጫዋቾች ላይ ድብደባ በፈጸሙት ተጫዋቾቹ ላይም ክለቡ እርምጃ እንደሚወስድ እንጠብቃለን» ያለችው ጋዜጠኛ ቆንጅት ናት በትዊተር ገጿ።

ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን እያጣቀሱ የዳኛ ድብደባ ድርጊቱን በተለያየ መልኩ የገለጡ በርካቶች ናቸው። የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ የሰፈረው አስተያየት እና ክርክሩ መስመሩን ስቶ ወዳልተፈለጉ አቅጣጫዎችም ሲነጉድ ተስተውሏል። በዛ መሀል ግን ጉዳዩን በቀልድ መልክ ጎነጥ ያደረጉም አልጠፉም። መጨረሻቸው በጠብ እና በግርግር የሚቋጩ አንዳንድ የሠፈር ጨዋታዎችን በማስታወስ ይመስላል ፋንታሁን ተሾመ ትዊተር ላይ በአጭሩ ቀጣዩን ብሏል።  «ወልዋሎ ከመከላከያ ገንዘብ አስይዘው ነው እንዴ የተጫወቱት?»

በቀልድ መልክ በተሰነዘረው ሌላኛው የትዊተር መልእክት ወደ ቀጣዩ ርእሰ-ጉዳያችን እንሻገር። እንዲህ ይነበባል መልዕክቱ፦ «እግር ኳስ ከጥሎ ማለፍ ወደ ገድሎ ማለፍ ተሸጋግረዋል!!»

Shakiso Town
ምስል Yidnekachew Gashaw

የሼክ መሐመድ አል-አሙዲ ንብረት የሆነው ሚድሮክ ኩባንያ ወርቅ ማምረቻ ፍቃድ መታደስ ከማዕድን ማውጫው አቅራቢያ በምትገኘው ሻኪሶ ውጥረት አንግሶ ቆይቷል።  ሚድሮክ የወርቅ ማምረቻ ፈቃዱ መታደሱን የሚገልፅ ደብዳቤ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች በስፋት ተዘዋውሯል። ደብዳቤው በቀድሞው የኢትዮጵያ የማዕድን፣ የነዳጅ እና የተፈጥሮ ጋዝ ሚኒስቴር ሚንስትር አቶ ሞቱማ መቃሳ ተፈርሞ የወጣ እንደኾነ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚዎች ጠቅሰዋል።

ናይጮ ዋቆ ትዊተር ገጹ ላይ በእንግሊዘኛ ባስነበበው ጽሑፉ፦ «የሚድሮክ የሻኪሶ የወርቅ ማዕድን ማውጫ ክስተት የሚያስተምረን ኦሕዴድ ኅብረት እንደሌለው ነው» ብሏል።  «ሞቱማ መቃሳ፤ እድሳቱን የፈቀዱት ግለሰብ የኦህዴድ አባል ነናቸው። ስለምን ፈረሙ? ስለምንድንስ ነው እኚህን ሰው ማንም ምንም ያልጠየቃቸው?» ሲል ጽሑፉን በጥያቄ ቋጭቷል።

ጄ ቦንሳ የተባለ የትዊተር ተጠቃሚ በበኩሉ፦ «የሚድሮክ በለጋ ዳምቢ የማምረት ሥራ ፈቃድ ዕድሳት የኦሮሞ ሕዝብ በኦህዴድ ላይ ያለውን እምነት አናግቷል። ምናልባትም ሊጠገን በማይቻል መልኩ» ብሏል።

«ነገሮች ከቁጥጥር ውጪ ከመኾናቸው በፊት የፌዴራሉ እና የኦሮሚያ መንግሥት ሰዉ በሚድሮክ የላጋ ዳምቢ ወርቅ ማውጫ የገባውን ሥጋት በተመለከተ መልስ ሊሰጥ ይገባል።» የድሪባ መገርሳ አስተያየት ነው።

Shakiso Town
ምስል Yidnekachew Gashaw

ሔድራ ሁሴን በፌስቡክ በሰጠው አጭር አስተያየት፦ «ባለቤቱም ታስሯል ሰምቶ ይሆን ይህን ነገር?» ሲል ጠይቋል። «መነጠቅ አለበት»  ካሊድ ካሊድ ለሚድሮክ ታደሰ የተባለውን የወርቅ ማምረት ፈቃድ በተመለከተ የሰጠው የፌስቡክ አስተያየት ነው።

እታፈሩ አዲ በሰጠችው የፌስቡክ አስተያየት የዛሬውን ጥንቅር እናሳርግ። «በፍጹም መታደስ የለበትም። ባርነት እዚህ ጋር ያብቃልን። በደርግ ጊዜ ጓድ መንግሥቱ የዚህ ትውልድ ንብረት ነው ብሎ ነበር»  ያለችው እታፈሩ  «እናንተም ጠብቁት እኔም አስከብርላችኋለሁ ይኼ ጊዜውን ይጠብቃል፤ የትውልድ አደራ ነው እያሉ እንድንጎበን ይደረግ ነበር። ተራራ ሙሉ ወርቅ ለግለሰብ ሰጥቶ ማስበዝበዝ ይኼ የታሪክ ተወቃሽ መንግሥት እንደኾነ መታወቅ አለበት፤ ባርነት ይብቃን።»

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አርያም ተክሌ