1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ዳሳሽ መዳፎች» በሰሎሞን ሙጬ

ሐሙስ፣ መስከረም 28 2013

ሄኖክ ስዩም፣ግለሰቡ ነገሮችን በግልፅ፣ ያለይሉኝታ ከራሱ የኑሮ ውጣ ውረድ በመነሳት ሁሉንም ነገሮች በመጸሐፉ አስፍሯል ይላል። ሄኖክ የዚህ ዓይነት አፃፃፎች ምናልባትም እጅግ ጥቂት በሆኑ ልምድ ባላቸው ደራሲያን የሚደፈር ዓይነት እንደሆነ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን በመጥቀስ አነፃፅሮ አስተያየቱን ሰጥቷል።

https://p.dw.com/p/3jeI7
Solomon Muchie I Portrait
ምስል Solomon Muchie/DW

“ምሳሌ መሆን አለብኝ ብየ ነው የራሴን የህይወት ገጠመኝ የፃፍኩት”ሰሎሞን ሙጬ

ደራሲው ከአዲስ አበባ ለዶቼቬለ የአማርኛው ክፍል የሚዘግበው ወጣቱ ሰሎሞን ሙጬ ነው። ሰሎሞን በ30ዎቹ መጀመሪያ የእድሜ ክልል ላይ ነው የሚገኘው። ያለፈባቸውን የህይወት ውጣውረዶችና በትምህርትና በሥራ ሂደት ያጋጠሙ ፈተናዎችን ያካተተና 318 ገፆች ያሉት ዳሳሽ መዳፎች የሚል መጽሐፍ አሳትሞ ሰሞኑን ለገበያ አቅርቧል። አንባቢያን እንደሚሉት የመጽሐፉ የአፃፃፍ ስልት ከተለመደው የአፃፃፍ ዘዴ ወጣ ያለና የተለየ ነው፡፡ ይህን አስተያየት ከሰጡ አንባቢያን መካከል የቱሪዝም ጋዜጠኛ የሆነው ሄኖክ ስዩም አንዱ ነው። ሄኖክ እንደሚለው ግለሰቡ ነገሮችን በግልፅ፣ ያለይሉኝታ ከራሱ የኑሮ ውጣ ውረድ በመነሳት ሁሉንም ነገሮች በመጸሐፉ አስፍሯል ይላል። 

Buch I Solomon Muchie
ምስል Solomon Muchie/DW

እንደ ሄኖክ ግንዛቤ የዚህ ዓይነት አፃፃፎች ምናልባትም እጅግ ጥቂት በሆኑ ልምድ ባላቸው ደራሲያን የሚደፈር ዓይነት እንደሆነ ደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔርን በመጥቀስ አነፃፅሮ አስተያየቱን ሰጥቷል። የአሀዱ ራዲዮና ቴሌቪዥን ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥበቡ በለጠ መጽሐፉ የተፃፈበትን መንገድ ግልፅነት፣ ድፍረትንና አንባቢን መያዝ የሚያስችል ቋንቋን ተጠቅሞ የተፃፈ እንደ አንድ የፊልም ታሪክ ቀልብ የሚይዝ ነው ሲሉ የመጽሐፉን የአፃፃፍ ዘዴ አድንቀዋል።
ደራሲው ሰለሞን ሙጬ መጽሐፉን እንደዚህ ግልፅና ባልተለመደ መንገድ የፃፈበትን መንገድ ሲናገር “ የሚያሳስበኝ የኔ ዘመን ወጣቶች ጉዳይ ነው፣ ወጣቱ ራሱን ርቆታል፣ ሸሽቶታል፣ ራሱን ይፈራዋል እንዲህ ነኝ የሚል ወጣት አጣለሁ፣ የሚያስመስለው፣ የሚዋሸው ወይም ደግሞ ቀባብቶ የሚያልፈው ወጣት በዝቶ ይታየኛል አገር የሚረከብ ትውልድ በዚህ መንገድ ከታነፀ ነገ አደጋ ነው የሚሆነው፣ ምሳሌ መሆን አለብኝ ብየ ነው የራሴን የህይወት ገጠመኝ የፃፍኩት ባቅሜ ትንሽ ነገር ላድርግ ብየ ነው የሞከርሁት” ብሏል። 
የመጽሐፉ ይዘት ፖለቲካን፣አኗኗርን፣ የህይወት ውጣ ውረድን የሚያሳይ የትውልድ ማስተማሪያ እንደሆነ ነውአቶ አቶ ጥበቡ በለጠ ካነበቡት ተነስተው የገለጹት፡፡ 
ኢትዮጵያ ውስጥ በወጣትነት እድሜ የሚጽፉ ሰዎች ማየት ብዙም የተለመደ እንዳልሆነ የተናገረው ሄኖክ ይህ መጽሐፍ ለትውልዱ ትልቅ አስተማሪና ተሞክሮ የሚወሰድበት ነው ብሏል፡፡ 
“ዳሳሽ መዳፎች” ምናልባትም በዚህ የወጣትነት የእድሜ ክልል የተፃፈ ሁለተኛው መጽሐፍ ሊሆን እንደሚችል የጠቀሱት አቶ ጥበቡ ከዚህ በፊት ተመስገን ገብሬ የሚባል በ20ዎቹ የእድሜ ክልል የነበረ ጋዜጠኛ “ሕይወቴ” በሚል መፃፍ ማሳተሙን አስታውሰዋል፡፡ 
ለዓመታት የተሰበሰበ መረጃን መልክ ለማስያዝ፣ ቅርፅ ለመስጠትና ለማሳተም በሚደረገው ሂደት በርካታ ሰዓታትን ይወስዳል፣ ታዲያ ይህን ማድረጉ ከስራ ጋር ከባድ አልነበረም? ስል ለሰለሞን ጥያቄ አንስቼለት ነበር፡፡

Buch I Solomon Muchie
ምስል Solomon Muchie/DW

 

“በእርግጥ ስራው ቀላል ነበር ባይባልም ያለኝን ሰዓት በአግባቡ በመጠቀሜ ብዙ ጫና አልተፈጠረብኝም” ብሏል ሰለሞን 
ስለመጽሐፉ አሉታዊም አወንታዊም አስተያየቶች እየተሰጡት እንደሆነ የተናገረው ሰለሞን ወደፊትም እውነትን ከመጻፍ ወደኋላ አልልም ብሏል፡፡ 

 

ዓለምነው መኮንን

ነጋሽ መሐመድ