1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደኢሕዴን ደቡብ ክልልን መታደግ ይችላል?

ሐሙስ፣ ነሐሴ 9 2011

በከረሙ እና አዳዲስ ፖለቲካዊ፤ ኤኮኖሚያዊ እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ሲናጥ የከረመው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) አባላት በሐዋሳ፤ በአዲስ አበባ እና በአዳማ ከተሞች ለውይይት ተቀምጠዋል። የደቡብ ክልልን ጥያቄዎች ለመመለስ በንቅናቄው ተሰራ የተባለው «ሳይንሳዊ ጥናት» ከመወያያ አጀንዳዎቹ መካከል ይገኝበታል። 

https://p.dw.com/p/3NymE
Treffen der Demokratischen Volksbewegung in Südäthiopien
ምስል SNNPR Press Secretariat

የደኢሕዴን ቅርቃር

ዶክተር ካሱ ኢላላና «በክብር ተሰናበቱ» የተባሉትን ጨምሮ የደኢሕዴን አመራሮች ለውይይት በአዲስ አበባ በሐዋሳ እና በአዳማ ተሰይመዋል። የንቅናቄው ሊቀ-መንበር ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል ለክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ እንደተናገሩት የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል የገጠሙት ፖለቲካዊ ፈተናዎች እና የጸጥታው ሁኔታ ዋንኛ የመወያያ ርዕሶች ናቸው።  
በአዲስ እበባ የሚደረገውን ውይይት በምኒስትር ማዕረግ የኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ማዕከል አስተባባሪ አቶ መለስ ዓለሙ፤ የአዳማውን የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተስፋዬ በልጅጌ፤ የሐዋሳውን የደኢሕዴን ፅህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ ይመሩታል። በሶስቱ ከተሞች ለአራት ቀናት በሚደረገው ውይይት ደኢሕዴን ለሰባት ወራት በምሁራን አሰናዳሁት ያለው እና ክልሉ ለገባበት ፖለቲካዊ ቅርቃር መፍትሔ ይሰጣል ተብሎ ተስፋ የጣለበት «ሳይንሳዊ ጥናት» ቀርቧል። 

ሙፈሪያት ካሚል «የክልሉን አደረጃጀት አስመልክቶ በተለያዩ ጊዜያት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች የተነሱ ጥያቄዎች አሉ። ይኸንንም ጥያቄ በተመለከተ በህገ-መንግሥት ማዕቀፍ ውስጥ ሆኖ ድርጅቱ ባለፈው ባካሔደው አስረኛ ድርጅታዊ ጉባኤ ባስቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የክልሉን አደረጃጀት የተመለከቱ ጉዳዮች ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በሀገሪቱ አሉ በተባሉ ዕውቅ ምሁራን የተጠና ጥናት አለ። ይኸንንም ጥናት መሠረት ያደረገ ውይይት የሚካሔድበት መድረክ ይሆናል» ሲሉ ለክልሉ የቴሌቭዥን ጣቢያ በትናንትናው ዕለት ተናግረዋል። 

የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ባለፈው ሳምንት ባከሔደው ስብሰባ «ድጋፍ አደርግለታለሁ» ያለው የደኢሕዴን ጥናት ዛሬ ደቡብ ተብሎ የሚጠራው ክልል ለተነሱበት ጥያቄዎች ሶስት የመፍትሔ ሐሳቦች አቅርቧል።ከጥናት ቡድኑ አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶክተር ከይረዲን ተዘራ «በደቡብ የሚገኙ 56 ብሔረሰቦች አሁን ባለው ሁኔታ ችግሮቻቸውን ፈትተው ክልሉን ቢያስቀጥሉ አንደኛ በጋራ ጉዳዮች ላይ የጋራ አቋም ለመያዝ እና በሀገር የነበረን ተደማጭነት ለማስቀጠል ይረዳል ይላሉ። ክልሉን ማስቀጠል የማይቻል ከሆነ በሁለተኛ አማራጭነት የጥናት ተሳታፊዎቻችን ያስቀመጡት ክልሉን በሁለት እና ከዚያ በላይ ማደራጀት ነው» ሲሉ የጥናት ቡድኑ ያቀረባቸውን ሁለት አማራጮች ገልጸዋል። 
ባለፈው ሐምሌ አጋማሽ ደኢሕዴን ያዋቀረው የባለሙያዎች ቡድን «ሁለቱ አማራጮች ባይሰሩና ወደማንችለው አደጋ ብንገባ ሀገራዊ የደኅንነት ሥጋት ሊመጣ ስለሚችል ሁሉም አካባቢዎች ከላይ በሚመጣ ሳይሆን ውይይት አድርገው ነገሩን በይደር አቆይተን ሀገር ከተረጋጋች በኋላ እንይ የሚለውን አማራጭ ሶስተኛ አማራጭ አድርጎ ጥናቱ አቅርቧል» ሲሉ ዶክተር ከይረዲን ገልጸዋል። 

Treffen der Demokratischen Volksbewegung in Südäthiopien
ምስል SNNPR Press Secretariat

የጥናት ውጤቱ በቀጥታ ለሕዝብ ይፋ ባይሆንም ተመልክተንዋል የሚሉ የክልሉ የለውጥ አራማጆች እና የተቃውሞ የፖለቲካ አመራሮች የሰላ ትችት ይሰነዝሩበታል። ከእነዚህ መካከል ከቤራ የተባለው የሐዲያ የለውጥ አራማጆች እንቅስቃሴ አስተባባሪ ደቦጭ ጎዲሶ (ስማቸው የተቀየረ) አንዱ ናቸው። 

«ማዕከሉን ከትንሽ ጊዜ በኋላ እንደሚወስኑ ነው እየሰማን ያለንው።ከሐዋሳ ውጪ ነው የሚያደርጉት ነው የሚባለው። ያ ማዕከል የት ይሁን የሚባለውን ደግሞ ማዕከላዊ ኮሚቴው ተሰብስቦ ውሳኔ ይሰጣል ይባላል። ግን 55ለ1 የሚለው ነው እነሱ ተስማምተው የወጡት» ሲሉ ይናገራሉ። በአቶ ደቦጭ እና ሌሎች የክልሉ የለውጥ አራማጆች አባባል ደኢሕዴን የሲዳማ ዞን ያቀረበው ጥያቄ በሕዝበ-ውሳኔ ምላሽ ካገኘ በኋላ ቀሪዎቹን 55 ብሔሮች በነበሩበት ለማስቀጠል ከውሳኔ ደርሷል። 

ከሶስቱ አማራጮች ደኢሕዴን ወደ የትኛው እንዳጋደለ በይፋ የተናገረው የለም። አንድ ለንቅናቄው ቅርብ የሆኑ ግን ደግሞ ስማቸውን እንዳይገለፅ የፈለጉ ሰው «በጥናቱ ላይ ከመወያየት በስተቀር አዋጪ ተብሎ የተለየ አማራጭ የለም» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። 

አቶ ደቦጭ ከቤራ የተባለው የለውጥ እንቅስቃሴ የሐዲያ ሕዝብ ደኢሕዴን በሚመራው ክልላዊ መንግሥት ደርሶበታል የሚለውን ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ በደል ለመሞገት ያለመ እንደሆነ ይናገራሉ። የሐዲያ ዞን ምክር ቤት ክልል የመሆን ጥያቄ ያቀረበው ባለፈው ኅዳር ወር ነበር። አቶ ደቦጭ አሁን ደኢሕዴን ያሰራው ጥናትም ሆነ ንቅናቄው «ከሕዝብ ርቆ የሚያደርገው ውይይት» መፍትሔ አያመጣም ሲሉ ፈርጠም ብለው ይናገራሉ። 
ደኢሕዴን ጥናቱ ብቻ ሳይሆን ንቅናቄው ጭምር የከፋ ተቃውሞ ውስጥ ገብቷል። እንደ ሐዲያ ሁሉ የራሱን ክልላዊ መንግሥት የማቆም ውሳሴ ያሳለፈው የዎላይታ ዞን ወጣቶች በቦሎሶ ሶምቤ ከተማ በደኢሕዴን የመሰሉትን የሬሳ ሳጥን በደቡብ ክልል ሰንደቅ አላማ ሸፍነው ቀበረውታል።ለደኢሕዴን ተምሳሌታዊ ቀብር የፈጸሙት የሶምቤ ወጣቶች በዕለቱ ቀይ፣ ቢጫ እና ጥቁር ቀለማት ያሉት አዲስ ሰንደቅ ዓላማ ያውለበልቡ ነበር። ሰንደቅ ዓላማው የዎላይታ ዞን የራሱን ክልላዊ መንግሥት ሲያቆም ሊጠቀምበት የታቀደ ነው። የላጋ የተባለው የዎላይታ ወጣቶች ማኅበራዊ ንቅናቄ መሥራቾች አንዱ የሆኑት አሸናፊ ከበደ 22 ሚሊዮን ዜጎች ካሉት የደቡብ ክልል 17 ሺሕ ገደማውን በማነጋገር የተሰራውን ጥናት ከሚነቅፉ አንዱ ናቸው። ጥናቱ «በአቅጣጫ የተመራ ነው፤ ሳይንሳዊ መሥፈርቶችን አያሟላም» የሚሉት አሸናፊ ደኢሕዴን  «ከሰው ልብ ወጥቷል» ሲሉ ይሞግታሉ።

Treffen der Demokratischen Volksbewegung in Südäthiopien
ምስል SNNPR Press Secretariat

«ደኢሕዴን ከሰው ልብ ወጥቷል፤ በጉልበት መገዛት የማይችል ትውልድ ተፈጥሯል። አሁን በተፈጠረው አንፃራዊ ፕሬስ፤ የኢንተርኔት ነፃነትና የሐሳብ ውይይት፤ የመደራጀት የመነጋገር ዕድሎች ደኢሕዴን ተወዳዳሪ አይደለም። የዕድሜ እንጂ የአስተሳሰብ የስትራቴጂ፤ የፖሊሲ ብስለት እና የህዝብ ተቀባይነት የሌለው ሆኗል» ሲል ይከራከራሉ። 

በመጪው ኅዳር ይደረጋል ተብሎ በሚጠበቅ ሕዝበ-ውሳኔ ይፈታል በተባለው የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ከተቀሰቀሰው ኹከት በኋላ የተቋቋመው የጸጥታ ጥበቃ ዕዝ ዎላይታን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በተካሔዱ ሰልፎች የታዩ ሰንደቅ ዓላማዎችን እና የተለያዩ ምልክቶችን በማገድ በክልሉ እና በንቅናቄው ላይ የተቀሰቀሱ ተቃውሞዎችን ለመቆጣጠር ሞክሯል። 
ንቅናቄው በተለያዩ ዞኖች በሥልጣን ላይ የነበሩ አባላቱን በማገድ በሌላ እስከ መተካት ደርሷል። ደኢሕዴንን በቅርብ የሚያውቁ ሹም ሽሩ ንቅናቄው የገጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ሲውተረተር የተፈጠሩ ተጨማሪ ችግሮች ማሳያ አድርገው ይጠቅሷቸዋል። ለሐዲያ ሕዝብ ጥብቅና ቆሚያለሁ የሚሉት አቶ ደቦጭ ከእንግዲህ በኋላ ደኢሕዴን የደቡብ ክልልን ለማስተዳደር እንደሚቸገር ያምናሉ።
«እንደ አሁኑ በኮማንድ ፖስት አስገድዶ ካልሆነ በስተቀር አይችልም» የሚሉት ደቦጭ አማራጮቹን ከካድሬዎች ይልቅ በሕዝብ ዘንድ ወረድ ብሎ ቢወያይባቸው የሚበጅ መፍትሔ ለማግኘት ይረዳል ሲሉ ተናግረዋል። 

የዛሬው ደኢሕዴን በመስከረም 1985 ዓ.ም. የ«አስራ ስድስት የብሔረሰብ የፖለቲካ ድርጅቶች» ጥምረት ሆኖ በግንባርነት ሲመሰረት ጀምሮ የሚያውቁ ስማቸዉ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የክልሉ የቀድሞ ፖለቲከኛ ንቅናቄው የገጠሙትን ችግሮች መፍታት ለመቻሉ ጥርጣሬ አላቸው። የቀድሞው የደኢሕዴን አባል በክልሉ ከተነሱት የአወቃቀር ለውጥ ጥያቄዎች ባሻገር ንቅናቄው በተለይ በወጣቶች ዘንድ ተቀባይነት ማጣቱ ዋንኛ ፈተና እንደሆነ ይናገራሉ።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ