1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ደቡብ ሱዳን፦ ዳግም ወደ ውዝግብ 

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 22 2012

የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ዋነኛ ተቃዋሚዎች ለወራት ባደረጉት ድርድር ከ6 ወራት በኋላ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት የተሰጣቸው የስድስት ወራት ጊዜ ማክሰኞ፤ ኅዳር 2 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ያከትማል። የሪይክ ማቻር ቃል አቀባይ ቡድናቸው ጥምር መንግሥቱ ውስጥ መግባት እችላለሁ ብሎ እንደማያምን በዚሁ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ይፋ አድርገዋል።

https://p.dw.com/p/3SKoa
Sudan, Khartoum: 
Präsident des Südsudan Salva Kiir Mayarditund Oppositionsführer des Südsudan Riek Machar
ምስል picture-alliance/M. Hjaj

ትኩረት በአፍሪቃ

በነጻነት ማግስት በእርስ በእርስ ጦርነት በተጠመዱት ተፋላሚዎቿ ጦስ እንደዘበት ግማሽ ሚሊዮን ግድም ነዋሪዎቿን አጥታለች። በሚሊዮን የሚቆጠሩት ደግሞ ሞት፤ ሰቆቃ እና እንግልትን ፍራቻ ቀዬያቸውን ጣጥለው ተሰደውባታል፤ ደቡብ ሱዳን። ከስድስት ዓመታት የእርስ በእርስ መቆራቆስ በኋላም በደቡብ ሱዳን ዛሬም ግድያ እና ስደት አላባራም። በዓለም አቀፍ ሃገራት ጫና እና በቃጣናው መንግሥታት የማደራደር ጥረት ለስድስት ወራት የተራዘመው የደቡብ ሱዳን የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመሥረት የተሰጠው ቀነ-ገደብ ከአንድ ሳምንት በኋላ ያከትማል። ከዚያ በፊት ግን ጥምር መንግሥቱ ይመሰረታል ብለው እንደማያምኑ የዋነኛው ተቃዋሚ ቡድን መሪ የሪይክ ማቻር ቃል አቀባይ ይፋ አድርገዋል። ውሳኔው በደቡብ ሱዳን ዳግም ውጥረት አንግሷል።

የደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ዋነኛ ተቃዋሚዎች ለወራት ባደረጉት ድርድር ከስድስት ወራት በኋላ የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት የስድስት ወራት ጊዜ የተሰጣቸው ግንቦት ወር ላይ ነበር። ተቀናቃኝ ቡድናቱ እጅ እግሬን ሲሉ ግን ወደ ቀነ-ገደቡ እየተጠጉ ነው። ቀነ-ገደቡ ማክሰኞ፤ ኅዳር 2 ቀን፣ 2012 ዓ.ም ያከትማል። እንዲያም ኾኖ የሪይክ ማቻር ቃል አቀባይ ቡድናቸው ጥምር መንግሥቱ ውስጥ መግባት እችላለሁ ብሎ እንደማያምን በዚሁ ሳምንት ረቡዕ ዕለት ይፋ አድርገዋል። የዛኑ ዕለትም የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር በበኩላቸው ለሕዝብ ንግግር ሲያሰሙ፦ በቀጥታ ስለሪይክ ማቻርን ባይናገሩም፤ ሁሉም ወገኖች ለስምምነቱ በቆራጥነት እየሠሩ መሆኑን ገልጠዋል። ለተቃዋሚዎችም ጥሪ አስተላልፈዋል እንዲህ ሲሉ፦ «እንኳን ደህና መጣችሁ ማለት፤ መራር ጥላቻውን ሁሉ መርሳት እሻለሁ።» 

 የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር የሠላም ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት መዲናዪቱ ጁባ ውስጥ
የደቡብ ሱዳን ፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር የሠላም ስምምነቱ በተፈረመበት ወቅት መዲናዪቱ ጁባ ውስጥምስል Reuters/S. Bol

የአንድነት መንግሥት ምሥረታ ቀነ-ገደቡ ይራዘምልኝ ከሚለው ከደቡብ ሱዳን ዋነኛ ተቃዋሚ ቡድን የረቡዕ ዕለት ጥያቄ በኋላ ተፋላሚዎችን ከመንግሥት ጋር ሲያሸማግሉ የነበሩ ሃገራት ምላሽ ወዲያውኑ የተሰማ ነገር አልነበረም። ድርድሩን ስትደግፍ የቆየችው ዩናይትድ ስቴትስ ከእንግዲህ ቀነ-ገደቡ ይራዘም የሚል ጥያቄ ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተቀባይነት እንደሌለው ግን ቀደም ሲል አሳስባ ነበር። በደቡብ ሱዳን የዩናይትድ ስቴትስ አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ ከስድስት ወራት በፊት በተለይ ከዶይቸ ቬለ (DW) ጋር ባደረጉት ቃለ-መጠይቅ ሀገራቸው ስምምነቱ ገቢራዊ የሚሆንበትን ተጨባጭ ነገር ማየት እንደምትሻ እንዲህ አሳስበው ነበር። 

«ስድስት ወሩን ጥበብ በተሞላበት መንገድ እና በንቃት ይጠቀሙበት። በሽግግር ጊዜው መሠራት የሚገባቸውን ቀሪ ተግባራትን በመላ ያሳኩ። እንደውም ከዚያ ባሻገር ያስቡ።» ከሦስት ወራት በፊት ስምንተኛ ዓመት የነፃነት ቀንዋን ባሰበችው ደቡብ ሱዳን ውስጥ ተፋላሚዎች የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመሥረት እጅግ ተስኗቸዋል። ለግንቦት 12 ቀን፣ 2011 ዓ.ም የያዙት የአንድነት መንግሥት ምሥረታ ቀጠሮ ፈርሶ በስድስት ወራት የተራዘመውም የሚሳካ አይመስልም። ቀነ ገደቡ እንዲራዘም የተጠየቀው በደቡብ ሱዳን ዋነኛ የተቀናቃኞች መሪ ሪያክ ማቻር ጥያቄ ነበር። በወቅቱ አዲስ አበባ ውስጥ በተደረገው ስምምነት ለስድስት ወራት የተራዘመውን ቀነ-ገደብ የምስራቅ አፍሪቃ የልማት በይነ መንግስታት (IGAD) ዕውቅና ሰጥቶት ነበር።

የዋነኛው ተቃዋሚ መሪ ሪይክ ማቻር በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባ
የዋነኛው ተቃዋሚ መሪ ሪይክ ማቻር በደቡብ ሱዳን መዲና ጁባምስል Reuters/S. Bol

ሪያክ ማቻር ባለቀ ሰአት ድጋሚ የስድስት ወራት ቀነ ገደብ እንዲሰጣቸው ካስጠየቋቸው አንገብጋቢ ጉዳዮች መካከል የደኅንነት ጉዳይ ነው። ሪያክ ማቻር በቃል አቀባያቸው በኩል ረቡዕ ዕለት እንዳስታወቁት፦ የሣልቫ ኪር መንግሥት የሠላም ሒደቱን በሚፈለገው መንገድ አላስኬደም ሲሉ ወቅሰዋል። ከአንድ ዓመት በፊት በተፈረመው የሰላም ውል መሠረት ለፕሬዚዳንት ሣልቫ ኪር ታማኝ የኾኑ 83 ሺህ ወታደሮችን  ከተቃዋሚዎች ጋር ማቀላቀል የሚለው ይገኝበታል። ዋነኛ ተቃዋሚው ሪይክ ማቻር እና ከዐሥር በላይ የሚቆጠሩ ተፋላሚ ቡድናት እንዲሁም ዓማጺያን ተመርጠው ሥልጠና ከተሰጣቸው በኋላ በሚመሰረተው የጋር ጦር ሠራዊት ውስጥ እንዲቀላቀሉ ታስቦ ነበር። ኾኖም ሐሳቡ ከሐሳብ መዝለል አልቻለም። በደቡብ ሱዳን የብሪታንያ ዲፕሎማት ክሪስ ትሮት ይኽንኑ ያረጋግጣሉ። «አንዳችም መሻሻል አላሳየም። መስከረም ወር ላይ ስምምነቱ ከተፈረመበት ጊዜ አንስቶ እያሳሳበን ያለው ጉዳይ፦ አኹንም ድረስ የጋራ ጦር ሠራዊት ቢያንስ እንኳን ጥቂት ወታደሮች ያሉበት መመሥረቱን አለማየታችን ነው።» 

ሪይክ ማቻር በመዲናዪቱ ጁባ የሚገኙ ባለሥልጣናት ቃል የገቡትን እየተገበሩ አይደሉም ሲሉም በብርቱ ወቅሰዋል። የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ከመመስረቱ አስቀድሞም የደቡብ ሱዳን መንግሥት በስምምነቱ መሠረት ቃል የገባውን ሊተገብር ይገባዋል ብለዋል። «የፀጥታውን ኹኔታ ማረጋጋት። ከቀዬያቸው ተፈናቅለው በተባበሩት መንግሥታት መጠለያ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ወደ መኖሪያቸው እንዲመለሱ በማስቻል ዳግም ምርታማ እንዲኾኑ ብሎም በእርቀ-ሰላሙ ሒደት ውስጥ ሚናቸው ከፍ እንዲል  ማድረግ።»

ሪይክ ማቻር እና ባለቤታቸው አንጄሊና ቴኒ ወደ መዲናዪቱ ጁባ ሲገቡ፤ እ.ጎ.አ. ጥቅምት 20 ቀን፤ 2018
ሪይክ ማቻር እና ባለቤታቸው አንጄሊና ቴኒ ወደ መዲናዪቱ ጁባ ሲገቡ፤ እ.ጎ.አ. ጥቅምት 20 ቀን፤ 2018 ምስል Reuters/S. Bol

ሪይክ ማቻር ተግባራዊነቱ ተጓቷል ያሉትን የሰላም ሒደት ፕሬዚደንቱ ሣልቫ ኪርም ደግመውታል። እሳቸው ግን እንደምክንያት ያቀረቡት ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለሠላም ሒደቱ ማስኬጂያ የገባውን ቃል አለመጠበቁን ነው። «ስምምነቱን ለመተግበር የበጀት ድጋፍ ችግር ገጥሞታል። የበጀት ድጋፍ የሚባል ነገር የለም። ዩናይትድ ስቴትስ ስምምነቱን ዕውቅና የማትሰጠው ከኾነ ምዕራባውያን ኃይላት ገንዘባቸውን አይከፍሉም።»

በሚሊዮናት ለሚቆጠሩ ደቡብ ሱዳናውያን መከራ እንዲወርድባቸው ሰበብ የኮኑት ኹለቱ መሪዎች፤ ማለትም ሣልቫ ኪር እና ሪይክ ማቻር እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንደሚተያዩ ነው የሚነገረው። አደጋ እንዳይደርስባቸው በመስጋት ስማቸውን የሸሸጉ ታማኝኝ የፖለቲካ እና ወታደራዊ ውስጥ ዐዋቂዎችም በሚባለው ይስማማሉ። ዩናይትድ ስቴትስ በገንዘብ እጥረትም ኾነ በሌላ ምክንያት የደቡብ ሱዳን የሰላም ሒደት ከእንግዲህ ተሰናክሎ ማየት አትሻም።አምባሳደር ቶማስ ሁሼክ ይኽንኑ ሲያስረግጡ፦ «በዚህም አለ በዚያ በተለይ የሰላም ሒደቱን ለማሰናከል መሞከር ሕጋዊ አይደለም፤ እኛም ኾንን ሌሎች በዚያ ጉዳይ ላይ ጥብቅ አቋም ነው ያለን» ብለዋል።

የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት የተሰጠው ቀነ-ገደብ የሚጣስ ከኾነ ዩናይትድ ስቴትስ ማዕቀብ እንደምትጥል በመግለጥ ስትዝት ቆይታለች። ተፋላሚ ኃይላቱ ግን ከዩናይትድ ስቴትስ ዛቻ ይልቅ የተፈራሩት እርስ በእርሳቸው ነው። የሳልቫ ኪር መንግሥት በሀገሪቱ የጎርፍ አደጋ ዘጠኝ ሰዎችን መግደሉን እና 25 ሺህ ሰዎችን ማፈናቀሉን ምክንያት በማድረግ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሐሙስ ዕለት አውጀዋል። ሪይክ ማቻር የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ምስረታው ውስጥ ለመግባት መቸገራቸውን በቃል አቀባያቸው በኩል ይፋ ባደረጉ ማግስት መኾኑ ነው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተነገረው።

ሣልቫ ኪር (ባርኔጣ ያደረጉት) እና ሪይክ ማቻር አዲስ አበባ ውስጥ የተኩስ አቁም  ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ሠነድ ሲለዋወጡ
ሣልቫ ኪር (ባርኔጣ ያደረጉት) እና ሪይክ ማቻር አዲስ አበባ ውስጥ የተኩስ አቁም ስምምነት ከተፈራረሙ በኋላ ሠነድ ሲለዋወጡምስል Reuters/T. Negeri

በጎርጎሪዮሱ 2011 ዓ.ም ሰኔ ወር ነፃነትዋን የተጎናፀፈችዉ ደቡብ ሱዳን በእርግጥ ከነጻነት በኋላ 54ኛዋ አፍሪቃዊት ሃገር መኾን በቅታለች። ወደ እርስ በርስ ጦርነት ውስጥ ለመዘፈቅ ግን ብዙም አልቆየች። እንደ ጎርጎሪዮሱ አቆጣጠር በታኅሣስ ወር 2013 ዓ.ም ፕሬዚደንት ሣልቫ ኪር በወቅቱ ምክትላቸው የነበሩት የዓማጺያን መሪው ሪይክ ማቻር መፈንቅለ-መንግሥት ሙከራ አሢረውብኛል ሲሉ መክሰሳቸው በተቃዋሚ መሪው ማስተባበል ብቻ አልተቋጨም። ኹለቱም መሪዎች ጎሳዎቻቸውን አስተባብረው እርስ በእርስ ሲገዳደሉ ዓመታትን አስቆጥረዋል። እስከ አኹንም ድረስ በሀገሪቱ የእርስ በእርስ ጦርነት የተነሳ ከ400,000 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። ከሀገሪቱ 13 ሚሊዮን ግድም ነዋሪ መካከል አንድ ሦስተኛው ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሏል።

የሪይክ ማቻር ቡድን የብሔራዊ አንድነት መንግሥት ለመመስረት የተሰጠው ቀነ ገደብ በስድስት ወር እንዲራዘም መጠየቁ እና የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ትእግስት መሟጠጥ በደቡብ ሱዳን መንግሥት እና ተፋላሚዎች መካከል ምን ሊያስከትል እንደሚችል ዐይታወቅም። ሊገባደድ ጥቂት ቀናት በቀሩት ቀነ ገደብ ውስጥ ግን የብሔራዊ አንድነት መንግሥቱን ደቡብ ሱዳን ውስጥ ማቋቋም እንደማይቻል ኹኔታዎች ያመላክታሉ። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ